Friday, July 17, 2020

ኢትዮጵያን ከግጭትና ከውድመት ነፃ ለማድረግ ይህ ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት!

(July 17, (ሪፖርተር, (ርዕሰ አንቀጽ))--በቅርቡ በደረሰው ድንገተኛና ያልተጠበቀ ሁከት በርካቶች ሲሞቱ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ በአርሲ ነገሌ፣ በዝዋይ፣ በሻሸመኔና በተለያዩ ሥፍራዎች ከበርካታ ንፁኃን ግድያ በተጨማሪ፣ በግለሰቦችና በመንግሥት ንብረት ላይ የደረሰው ውድመት በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡

የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ምክንያት በማድረግ የተፈጸሙት ነውረኛ ድርጊቶች፣ ከበስተጀርባቸው ውስብስብና ረቀቅ ያሉ ተልዕኮ እንደነበራቸው በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ ራቅ ካሉ ሥፍራዎች ወጣቶችን በተሽከርካሪዎች በማጓጓዝ ከተሞች ላይ በማሰማራት ተፈጽመዋል የተባሉት አውዳሚ ድርጊቶች፣ ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ መንገድ ተፈጽመዋል፡፡ ጉዳዩ በሕግ የተያዘና በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉበት ስለሆነ፣ ዝርዝር ውስጥ መግባት ለጊዜው አስፈላጊ አይደለም፡፡

ነገር ግን ተመሳሳይ የሆኑ አስደንጋጭ ድርጊቶች እየተፈጸሙ በርካቶች መገደላቸው፣ ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው፣ ንብረቶቻቸው ወድመው ባዶ እጃቸውን መቅረታቸውና ለሥነ ልቦና ጉዳት መዳረጋቸው መቀጠሉ ማብቃት አለበት፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ በሰላማዊ መንገድ መፍታት በሚቻልበት አገር ውስጥ፣ ሌላ ዓላማ ከሌለ በስተቀር ኃይል ተመራጭ አይደለም፡፡ ነገር ግን ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚሰጥ አስተሳሰብና ድርጊት ሳይኖር፣ ግድያና ውድመት መፍትሔ የሚመስላቸው ይበረክታሉ፡፡ እየሆነ ያለውም ይህ ነው፡፡ መንግሥት ሕግ ከማስከበር ጎን ለጎን ለዴሞክራሲና ለልማት የሚያነሳሱ ተግባራት ላይ እያተኮረ፣ ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ምድር ነውረኛ ድርጊቶች እንዳይከሰቱ ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡

ኢትዮጵያ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፋ እዚህ የደረሰች አገር ናት፡፡ ከኢትዮጵያ ታሪክ የሚያመዝኑት በጦርነት ውስጥ የታለፈባቸው በርካታ ኩነቶች ናቸው፡፡ ከዘመነ መሳፍንት ወዲህ ያለችው ኢትዮጵያ አብዛኛውን ጊዜዋን ያሳለፈችው ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን ስትከላከል ነው፡፡ ለዘመናዊ ሥልጣኔ በር ከፋች ነበር የተባለው የተማከለ መንግሥት ምሥረታም ሆነ የአገረ መንግሥት ግንባታ ጅማሬዎች፣ በውስጥም በውጭም ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለባቸው ውጊያዎች ተካሂደውባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያን አሁን የያዘችውን ቅርፅ አግኝታ እንደ አገር መቆም የቻለችው፣ እንደ ማንኛውም አገር ግዛትን አካሎ ዳር ድንበርን ለማስከበር በተደረገ ተጋድሎ ነው፡፡ በአሜሪካም፣ በአውሮፓም፣ በእስያም ሆነ በሌላ ሥፍራዎች እንደተከናወነው ሁሉ በኢትዮጵያም የሆነው የአገር ምሥረታ ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ተገቢ የሚባል መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡

ለዘመናት አብረው የኖሩትም በዚህ የጋራ ማንነት ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚነዙት የፈጠራ ታሪክ ወይም ማስረጃ አልባ ትንተና ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ እዚህ የደረሰችው በአራቱም ማዕዘናት በሚኖሩ ልጆቿ ተጋድሎና መስዋዕትነት ነው፡፡ አንዱ የሌላው ጨቋኝ ሆኖ ሳይሆን ክፉና ደጉን እኩል በመጋራት ነው፡፡ እርግጥ ነው ከሁሉም ማኅበረሰቦች ውስጥ የወጡ ገዥዎች ነበሩ፡፡ አንዱ በዳይ ሌላው ተበዳይ ሆኖ የሚቀርበው ትርክት ግን ሕዝቡን ለመከፋፈል እንጂ አንዳችም እውነት የለውም፡፡ ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማቆም በተደረገው ጥረት የአንዱን ሚና አጉልቶ የሌላውን ለማንኳሰስ የሚደረግ ጥረትም ተቀባይነት የለውም፡፡

ከበርካታ አገሮች ታሪክ መገንዘብ እንደሚቻለው አገር የሚቀናው በኃይል ወይም በስምምነት ነው፡፡ የአንድ አገር ዳር ድንበር ተከብሮ ሰላምና ደኅንነቱ የሚረጋገጠው፣ በአካባቢው ካሉ ተገዳዳሪዎች ተመጣጣኝ ወይም የበለጠ ኃይል መገንባት ሲቻል ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ከአካባቢው ተገዳዳሪዎች ጋር ከተቻለ በስምምነት ካልሆነ ደግሞ በኃይል ራስን መከላከል ይቻላል ማለት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን ውስጣዊ ስምምነትና አንድነት ሊኖረው የግድ ይላል፡፡

የአገር ክብርና ፍቅር በሁሉም ዜጎች ዘንድ እኩል ተቀባይነት ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ሊኖር ስለሚችል፣ ልዩነትን እንደ ፀጋ በመቀበል በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አቋም ማራመድ ይቻላል፡፡

ከአገር ክብርና ህልውና የሚቀድም አጀንዳ ማራመድም ሆነ በዜጎች መካከል መጠራጠርና አለመተማመን የሚፈጥር ድርጊት ውስጥ መገኘት፣ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ማበርና የአገርን ህልውና መፈታተን ነው፡፡ ልዩነት ለውስጣዊ የፖለቲካ ፉክክር ማራመጃ እንጂ አገርን ለጠላት ዒላማነት ማመቻቺያ ባለመሆኑ፣ ከዚህ ገደብ እየታለፈ የሚፈጸሙ ጥፋቶች በከፍተኛ ወንጀል የሚያስጠይቁ ናቸው፡፡ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አመራሮች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን የሚመሩ ግለሰቦችና ሌሎችም ራሳቸውን ከአገር በላይ ሲያደርጉና አገርን ችግር ውስጥ ሲከቱ፣ የሚጠየቁበት አሠራር ከሌለ አስቸጋሪ ነው፡፡ ራስን ከአገርና ከሕግ በላይ ማግዘፍ ሥርዓተ አልበኝነት ለማስፈን ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡

በዚህ በኩል አሉታዊ ሚና በመጫወት ላይ ያሉ ኃይሎች አገር ለማፍረስ ሲረባረቡ በግላጭ ተስተውለዋል፡፡ ‹ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች አንድ ላይ ይበራሉ› የሚለውን ዕድሜ ጠገብ አባባል በመሻር ጭምር፣ በፍፁም ሊመሳሰሉ የማይችሉ ኃይሎች ‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው› ተባብለው አገር ለማተራመስ የሚቻለውን ሁሉ እያደረጉ ናቸው፡፡

ለሥልጣንና ይዞት ከሚመጣው ጥቅም በላይ በመረማመድ የታሪካዊ ጠላቶች ወኪል እስከ መሆን ያደረሳቸው ይህ ትብብር፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ይዞት የሚመጣው በረከት ሳይሆን መርገምት መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ከሥልጣኑ በሕዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል ተገርስሶ ጥጉን እንዲይዝ የተደረገው ኃይልና በዚህ ኃይል ሲቀጠቀጥ በነበረው ሌላው አካል፣ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ የማይጠቅም ግድያና ውድመት ሲፈጸም ትዕግሥትን ከመፈታተን አልፎ ላልተገባ ድርጊት የሚያነሳሳ መሆኑ የታመነ ነው፡፡

ነገር ግን ስህተትን በስህተት ለማረም መጣደፍ አስፈላጊ ስላልሆነ፣ በተቻለ መጠን ሕጋዊ መንገዶችን እስከ መጨረሻው ጥግ ድረስ በመጠቀም ፍትሕ ማስፈን ይገባል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ኃይል በመጠቀም ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የሚነሳሱ ካሉ፣ መንግሥት ተመጣጣኝ ዕርምጃ በመውሰድ ማስታገስ ይኖርበታል፡፡ በሕግ የተሰጠው ኃላፊነቱም ነው፡፡ እርግጥ ነው በሕግ ከለላ ሥር ያሉ ተጠርጣሪዎች በተገቢው መንገድ ተይዘው የሕግ ሒደቱ መቀጠል አለበት፡፡ ሕግ የሁሉም ነገር የበላይ እንደሆነ በተግባር ማሳየትም አስፈላጊ ነው፡፡ ቅሬታዎች ሲኖሩም ሕጉ በሚፈቅደው መጠን ማስተናገድም ይገባል፡፡ ይህንንም ለሕዝብና ይመለከተናል ለሚሉ ወገኖች በሙሉ በግልጽ ማሳየት የግድ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ሁሉንም ነገር ለፍትሕ አካሉ በመተው፣ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ተግባርን አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ ነው፡፡

በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሰላም የመኖር መብት አላቸው፡፡ ማንኛውም ዜጋ በኢትዮጵያ ውስጥ በመረጠው ሥፍራ የመኖር፣ የመሥራት፣ የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት ተፈጥሯዊና ሕጋዊ መብቱ ከወረቀት ጌጥነት ባለፈ በተግባር መረጋገጥ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ በተከሰቱ ሁከቶችና ውድመቶች ሳቢያ በርካቶች ሲገደሉ፣ ሲዘረፉና ሲፈናቀሉ የኢትዮጵያም ገጽታ ተበላሽቷል፡፡ ለበርካቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ኢትዮጵያዊያን ንብረቶቻቸው ወድመው ከፍተኛ ኪሳራ አጋጥሟል፡፡ የውጭ ባለሀብቶች ሳይቀሩ የውድመት ሰለባ ሆነዋል፡፡

ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የግጭትና የሞት አፍ ማሟሻ ሆናለች፡፡ ግጭቶች ባጋጠሙ ቁጥር ኢንተርኔት እየተዘጋ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ጭምር ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን አቅቷቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለማሳሰብ እንደ ሞከርነው እነዚህ በታሪካዊ ጠላቶች ጭምር የሚቀነባበሩ ግጭቶች ዋነኛ ዓላማቸው፣ የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት በማጥፋት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ደንብረው እንዲወጡ መገፋፋት ነው፡፡ ይህንን ዓለማ የሚያስፈጽሙላቸው ደግሞ በሕዝብ ነፃነትና መብት ስም የተደራጁ ኃይሎች ናቸው፡፡ የድርጊቶችን ቅደም ተከተልና ውስብስብነት በአንክሮ ለሚከታተል ማንም ጤነኛ ሰው ይህ የተንኮል ድር መነሻው የት እንደሆነ አይጠፋውም፡፡

ምክንያቱም በተደጋጋሚ የሚፈጸሙት ነውረኛ ድርጊቶች፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ አስነስቶ አገርን ለማፍረስ የሚደረግ ሴራ አካላት ከመምሰል አልፈው እውነት ሆነዋልና፡፡ አሁንም ወጣቶችን ለዚህ የጥፋት ድርጊት በማነሳሳት ከተሞችን በማውደም፣ የእርስ በርስ ጦርነት ለማስነሳት ነበር የተፈለገው ቢባል ሊገርም አይገባም፡፡ እውነቱ እንደዚያ ስለሆነ፡፡

ኢትዮጵያውያን አገራቸው በርካታ ችግሮች ያሉባት መሆኑን በመገንዘብ በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ተባብረው ከተነሱ እነዚህ ችግሮች እንደ ጉም በንነው ይጠፋሉ፡፡ ጊዜያቸውን አላስፈላጊ በሆኑ አሉባልታዎች፣ ሐሜቶችና አፍራሽ ድርጊቶች ላይ ከማባከን መቆጠብ አለባቸው፡፡ አሁንም አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር የሚያጋጩ የመርዝ ፕሮፓጋንዳዎች እየተረጩ ነው፡፡

እነዚህ ዘመን ያለፈባቸው ኋላቀር ፕሮፓጋንዳዎች የሚረጩት አገር ለማሳደግ ሳይሆን፣ አገርን ለማፈራረስ እንደሆነ በመገንዘብ ለአንድነት ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሲሆኑ አንፀባራቂውን የዓድዋ ጀግንነት በዚህ ዘመን እንደሚደግሙ ስለሚታወቅና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑ ስለታመነበት፣ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያውያንን የሚከፋፍሉትና የሚያፋጁት በውስጥ ተላላኪዎች አማካይነት እንደሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡ ባለፈው ሰሞን የተፈለገውም ይህንን አንድነት በመበተን ኢትዮጵያዊያንን በብሔርና በሃይማኖት ጭምር እርስ በርስ ለማባላት ነበር፡፡ ከአሁን በኋላ በታሪካዊ ጠላቶች ረቂቅ ሴራ ላለመበለጥ አንድነትን ማፅናት የግድ ይላል፡፡

ምንጫቸው የማይታወቅ ከፋፋይና በታኝ ወሬዎችንና አሉባልታዎችን በማስወገድ፣ በንቁ አዕምሮ የታሪካዊ ጠላቶችን አፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎች ማምከን ያስፈልጋል፡፡ ዘወትር እየተታለሉ እነሱ ወጥመድ ውስጥ መውደቅ ማብቃት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የምትጠናከረው በልጆቿ አንድነት ብቻ እንደሆነ በተግባር ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን ከግጭትና ከውድመት ነፃ ለማድረግ ይህ ትውልድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት መተማመን ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment