Sunday, July 14, 2019

በግለሰቦች የመኖሪያ ቤቶች የኪራይ ዋጋና የውል ስምምነቶች ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የሚስችል ረቂቅ ሕግ ተዘጋጀ

(14 July 2019, (ሪፖርተር))--በግለሰቦች በኪራይ የሚቀርቡ መኖሪያ ቤቶች ልማትና አቅርቦት፣ የኪራይ ውልና የኪራይ ዋጋን ለመቆጣጠርና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ለመወሰን የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ማዘጋጀቱን፣ በቀጣዩ ዓመት ፀድቆ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ታወቀ፡፡

ከሳምንት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የሥራ አፈጸጸም ሪፖርታቸውን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የከተማ የቤት ኪራይ ዋጋንና ኪራይ ውሎችን መንግሥት መቆጣጠር ካልጀመረ የከተማ ነዋሪዎች ባልተገባ የዋጋ ግሽበት ከወርኃዊ ገቢያቸው አመዛኙን እንደሚያሳጣቸው መናገራቸው ይታወሳል፡፡

 ሪፖርተር ያገኘው ይህ ረቂቅ የሕግ ሰነድ እንደሚያስረዳው ማንኛውም ግለሰብ ለራሱና ለቤት ፈላጊዎች በኪራይ ለማቅረብ ቤት መገንባት እንደሚችል፣ ለኪራይ የሚሆኑ ቤቶችን የሚያቀርብ ግለሰብ ነባር ይዞታውን ተጠቅሞ ወይም የከተማ አስተዳደሩ ለዚሁ አገልግሎት በጨረታ የሚያቀርበውን መሬት ወስዶ ቤት መገንባት እንደሚችል ይገልጻል፡፡

ለግለሰብ መኖሪያነት የሚያገለግል ማንኛውም ቤት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ሆኖ ቢያንስ አንድ ክፍል የሆነ፣ በግል ወይም ከሌሎች ነዋሪዎች ጋር በጋራ የሚጠቀምበት መፀዳጃ፣ የገላ መታጠቢያና የምግብ ማብሰያ ክፍልና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን ያሟላ መሆን እንደሚኖርበት በአስገዳጅነት ተካቷል፡፡

በግለሰቦች አማካይነት በኪራይ የሚቀርቡ መኖሪያ ቤቶች የኪራይ ተመን በካሬ ሜትር እንደሚወሰን፣ ይህንንም የከተማ አስተዳደሮች በጥናት ላይ ተመሥርተው በሚያወጡት ደንብ እንደሚወስኑ ይገልጻል፡፡

 ይህ ቢሆንም አከራዮች ወቅታዊ የዋጋ ግሽበትን መሠረት በማድረግ የኪራይ ዋጋ ማስተካከል እንደሚችሉ፣ ነገር ግን አከራዩ ቀድሞ የነበረውን የኪራይ ውል ስምምነት ሲያድስም ሆነ ከአዲስ ተከራይ ጋር ውል ሲፈጽም የሚያደርገው የዋጋ ጭማሪ፣ ቀደም ሲል ከነበረውን የኪራይ ዋጋ ከአሥር በመቶ በላይ መሆን እንደማይችል በረቂቅ ሕጉ በአስገዳጅነት ተመልክቷል፡፡

ሁለትና ከዚያ በላይ ክፍሎችን ወይም ሙሉ ግቢ ለኪራይ የሚያቀርብ አከራይ ከሆነ፣ የኪራይ ውሎቹ አንድ ቅጂ ከአከራዩና ተከራዮቹ ሕጋዊ መታወቂያ ቅጂ ጋር ተያይዘው የሚመለከተው የከተማ አስተዳደር ቢሮ መቀመጥ እንደሚኖርበት ያስረዳል፡፡

ማንኛውም የአከራይ ተከራይ ውል ሲፈጸም በፍትሐ ብሔር ሕጉ ስለውል የተጠቀሱት ጠቅላላ ድንጋጌዎችን ማሟላት እደንደሚኖርበት፣ በተከራዩ ፍላጎት እስካልሆነ ድረስ የውል ዘመኑ ከስድስት ወራት ማነስ እንደሌለበት፣ እንዲሁም ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በስተቀር አከራዩ ከተከራዩ ከሦስት ወራት ለበለጠ ጊዜ ቅድመ ክፍያ መጠየቅ እንደማይችል ረቂቁ ይደነግጋል፡፡

በውል ስምምነቱ መሠረት አንድ የውል ዘመን ሳይጠናቀቅ አከራዩ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደማይችልም ይገልጻል፡፡ ረቂቁ በአከራዮች ላይ የተለያዩ ግዴታዎችን የሚጥል ነው፡፡ ማንኛውም ቤት አከራይ ግለሰብ ቤት ፈላጊዎችን በፆታ፣ በዕድሜ፣ በብሔር፣ በአካል ጉዳት ወይም በሃይማኖት መድልኦ ሳያደርግ እኩል ማስተናገድ እንደሚጠበቅበት፣ አከራዩ ቤቱን ካከራየ በኋላ የቤቱን ደኅንነት ለመከታተል ካልሆነ በቀር ያለ አከራዩ ዕውቅና ቤት ውስጥም ሆነ ግቢ ውስጥ መግባት እንደማይችልና በተከራዩ ግላዊ ሕይወት ውስጥም ጣልቃ መግባት እንደማይችል ይደነግጋል፡፡

ከከተማ አስተዳደሩ ለግለሰብ የሚከራዩ ቤቶችን ለመገንባት የተዘጋጀ ቦታ በጨረታ ወስዶ ለኪራይ እንዲውሉ የገነባቸውን ቤቶች ያለ ከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ ከአሥር ዓመት በፊት ወይም በውሉ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ በፊት የቤቱን አገልግሎት መቀየር እንደማይችል፣ የአከራይነት ፈቃድ የማውጣትና ስለአከራይነቱ መረጃ መስጠት፣ እንዲሁም የኪራይ ውሉን ለከተማ አስተዳደሩ ወይም ሥልጣን ለተሰጠው አካል ማስመዝገብ እንደሚኖርበት ይገልጻል፡፡

የከተማ አስተዳደሮች ተግባርና ኃላፊነትን በተመለከቱ ድንጋጌዎች ደግሞ የሚከራይ ቤት ለመገንባት የሚያስፈልግ መሬት በጨረታ የማቅረብ፣ በጨረታ በወሰዱት መሬት ላይ ወይም በነባር ይዞታቸው ላይ ግንባታ ለሚያካሂዱ ግለሰቦች ዲዛይን ማፅደቅ፣ የግንባታ ፈቃድ መስጠት፣ እንዲሁም በሕንፃ አዋጁ መሠረት የግንባታ ቁጥጥር ማድረግ፣ ከአንድ ቤት በላይ ወይም አፓርትመንት ቤቶችን ለሚያከራዩ ግለሰቦች የአከራይነት ፈቃድ መስጠትና የአከራይ ተከራይ የውል ስምምነትና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን አደራጅቶ መያዝ ይገኙባቸዋል፡፡

 በተጨማሪም ለኪራይ የሚቀረቡ ቤቶችን በራሱ ተነሳሽነት ወይም በተከራዩ ወይም በአከራዩ ጠያቂነት ለመኖሪያነት የሚያስፈልገውን ደረጃና አገልግሎት ያሟሉ ስለመሆናቸው ማጣራት፣ የጎደለ ነገር ካለ እንዲሟላ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፣ እንዲሁም ከአከራይ ተከራይ ግንኙነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚፈታ ቅሬታ ሰሚ አደረጃጀት መፍጠር የከተማ አስተዳደሮች ይጠበቅባቸዋል፡፡

ረቂቅ ሕጉ የተዘጋጀው በኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ሲሆን፣ በቅርቡም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብና በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለፓርላማ እንደሚላክ ይጠበቃል።
ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment