Sunday, July 14, 2019

በልዩነት ውስጥ መኖር ይለመድ!

(14 July 2019, ሪፖርተር))--ለዓመታት ‹‹ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት›› በሚባለው አጥር ውስጥ ታስረው የኖሩት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእግር ብረታቸውን ፈትተው የተለያዩ ባህሪያትን እያሳዩ ነው፡፡ በሌኒናዊ ጥብቅ የሆነ ማዕከላዊነት ይገዙ የነበሩት ድርጅቶች የዓላማና የተግባር አንድነት እንዳላቸው ለዓመታት ቢዘምሩም፣ አሁን በመካከላቸው የሚስተዋለው የበዳይና የተበዳይ ትርክት የግንባሩን ገመና እየገላለጠው ነው፡፡ ሕወሓት በግንባሩ ውስጥ የነበረውን የበላይነት ከተነጠቀ በኋላ፣ በተለይ ከአዴፓ ጋር የነበረው መጎሻሸም ሰሞኑን ገጽታውን ቀይሮ አደገኛ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀድሞ መግለጫ ሲያወጣ፣ የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም በመቀጠል አውጥቷል፡፡ ሕወሓት ኢዴፓን የትምክህት ኃይሎች እንደፈለጉ እንዲፈነጩ አድርጓል በማለት ሲከስ፣ አዴፓ በበኩሉ አገሪቱ አሁን ለምትገኝበት የፖለቲካ ብልሽት ዋና ተጠያቂና በአማራ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ማኒፌስቶ ማውጣቱን በማስታወስ ሕወሓትን ወንጅሎታል፡፡ የሁለቱም የቃላት ጦርነት ከበድ ባሉ አገላለጾችና ታሪካዊ ዳራዎች የታጀበ ነው፡፡ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ልዩነት መኖሩ በአግባቡ ከተያዘ ጤናማ ነው፡፡ ችግሩ ግን በማዕከላዊነት አስተሳሰብ ተጠርንፈው የኖሩ ስለሆኑ፣ ልዩነትን በጨዋነትና በስክነት ለማስተናገድ ይችላሉ ወይ የሚለው ዋነኛ ጥያቄ መሆን አለበት፡፡ እነሱ ለዓመታት በልዩነት ውስጥ መኖር አለመዱምና፡፡

ይህ መሠረታዊ ጥያቄ የሚነሳው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የታየው ልዩነት፣ ከዚህ ቀደም ልዩነትን ለመቀበል ፈቃዱም ሆነ ፍላጎቱ የሌለው ኢሕአዴግ ውስጥ በመፈጠሩ ነው፡፡ ለልዩነት ቦታ የማይሰጥና ሁሉንም ጠቅልሎ የመያዝ ባህል ለዓመታት በሰፈነበት ድርጅት ውስጥ፣ ሁለት አባል ድርጅቶች የቃላት ጦርነታቸው ከተከታዮቻቸው አልፎ ወደ ሕዝብ ውስጥ እንዳይሰርፅ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ አብረው ባሳለፏቸው በርካታ ዓመታት የተጠራቀሙ ቅሬታዎችና ብሶቶች ሲገነፍሉ ቁስሎችም ስለሚያመረቅዙ፣ የቃላት ትግትጉ ወደ ደጋፊና ሕዝብ ዘንድ ሲወርድ ለግጭት መንስዔ እንደሚሆን መረዳት ይገባል፡፡

የአማራንና የትግራይን ሕዝብ ታሪካዊ ግንኙነት ከማበላሸት አልፎ፣ አድማሱን እያሰፋ ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ ሊሆንም ይችላል፡፡ ለጊዜው በየጎራው የተሠለፉ ወገኖችን ትከሻ ለመለካካትና ይዋጣልን ለማለት፣ ገለልተኛ ነን የሚሉትን እውነቱ ማን ዘንድ እንደሆነ ለማስተንተን፣ ባለጉዳዮቹን ደግሞ ነጥብ ለማስቆጠርና የበላይነትን ለማሳየት ቢያግደረድርም፣ ዞሮ ዞሮ የሚፈጠረው ችግር ሰለባ የሚያደርገው ንፁኃንን ነው፡፡ ሁለቱም ድርጅቶች መፎካከር የሚኖርባቸው በሠለጠነ መንገድ በልዩነት ውስጥ መኖር እንደሚቻል ለማሳየት ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ግን ከተለመደው አዙሪት ውስጥ መውጣት አይችሉም ማለት ነው፡፡

ደጋግመን እንደምንለው ከምንም ነገር ላይ መቅደም ያለበት የአገር ህልውና ነው፡፡ የአገር ህልውና አስተማማኝና ዘለቄታዊነት የሚኖረው በልዩነት ውስጥ መኖርን መልመድ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የአገርን ህልውና ከፓርቲ በላይ መመልከት የሚችል ሰብዕና የተላበሱ አመራሮች ሲኖሩ የሕዝብ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ ከሥልጣን በላይ አገርን የሚያስቀድሙ አመራሮች የሕዝብ አክብሮት ይቸራቸዋል፡፡ ሕዝብ ድጋፍ የሚሰጠው ፓርቲ ሁሌም የሚጨነቀው ለአገር ህልውና ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በሕዝብ ስም መነገድ፣ ሥልጣንን ለግላዊና ለቡድናዊ ጥቅም ብቻ መጠቀምና ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ መገኘት ክብር ያሳጣል፡፡ ሁለት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕዝብ ዘንድ የሚቀርቡት የተሻለ ድጋፍ ለማግኘት ነው፡፡

ይህ ድጋፍ የሚገኘው ደግሞ የተሻለ ብቃት፣ ሥነ ምግባርና ለሕዝብ የሚጠቅም አጀንዳ ይዞ መገኘት ሲቻል ነው፡፡ በዚህ ቁመና ላይ መገኘት የሚገባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዴሞክራት መሆን የግድ ይላቸዋል፡፡ ዴሞክራት ደግሞ በልዩነት ውስጥ መኖር የሚችልና ከሕገወጥነት የራቀ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ተቀባይነት ያለው ባህሪ በመላበስ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘት የሚቻለው፣ ልዩነትን በማክበርና የሕዝብን የልብ ትርታ በማዳመጥ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ በቃላት ጦርነት ሳይሆን በተግባር እንደሚመዝን መገንዘብ ይገባል፡፡ የኋላ ታሪክንም እየመረመረ የዛሬውንም ሁኔታ እንደሚገመግም ማጤን ያስፈልጋል፡፡

የሕወሓትና የአዴፓ መግለጫዎች የሚጠቀሙት ኢሕአዴግ ራሱን ወደ መጨረሻው ጠርዝ እየገፋ መሆኑን ነው፡፡ በድርጅቱ ታሪክ በሁለት አባል ድርጅቶች መካከል እንዲህ ዓይነት የለየት መሸካከር ደርሶ አያውቅም፡፡ በ1993 ዓ.ም. በሕወሓት ውስጥ በተፈጠረው ልዩነት፣ አንዱን ወገን በማባረር ሌላው ኃይል ሥልጣኑን መቆጣጠሩ ይታወሳል፡፡ ይኼኛውን ልዩ የሚያደርገው ግን ሁለት ክልሎችን በገዥ ፓርቲነት የሚያስተዳድሩ መሆናቸው ነው፡፡

ለኢሕአዴግም ቢሆን አዲስ ክስተት በመሆኑ፣ ምን ዓይነት አቋም እንደሚያዝ ውሎ አድሮ ይታወቃል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ለኦዴፓና ለደኢሕዴን ከባድ የቤት ሥራ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በድርጅቱ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይፋ እንደተደረገው፣ አጋር ድርጅቶችን በማካተት ለሚመሠረተው አዲሱ ፓርቲ ትንሳዔ ሊሆንም ይችላል፡፡ ሌላ ክስተት ሊፈጠርም ይችላል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በየወቅቱ እየተገናኘ አንድነቱን በተለያዩ መግለጫዎች ለማሳየት ቢሞክርም፣ ኢሕአዴግን ግን ጣራው እንደተሸነቆረ ቤት እያፈሰሰ ነው፡፡ ልዩነትን ማስተናገድ አቅቶትም አባል ድርጅቶቹ በነገር እየተወጋጉ ነው፡፡ በልዩነት ውስጥ መኖር ካልቻሉ በወጉ መለያየት እንደሚቻል ቢያውቁ ይመረጣል፡፡ ካልሆነ ግን ለአገር የማይበጅ ነገር ውስጥ ይገባል፡፡

ኢሕአዴግ ውስጡ እየተሸረሸረ የሄደው ልዩነትን ለማስተናገድ የሚያስችል ተፈጥሮ ስለሌለው ነበር፡፡ በአገሪቱ አምስት ጊዜ ምርጫዎች ሲካሄዱ አንድም ቀን በምርጫ ተሸንፎ ተቃዋሚ ፓርቲ እንደሚሆን አስቦ አያውቅም ነበር፡፡ በውስጡ የተለያዩ ሐሳቦችን ማንሸራሸር ስላለመደ ለልዩነት ቦታ አይሰጥም ነበር፡፡ ተቃዋሚን በተፎካካሪነት ከማየት ይልቅ በጠላትነት መፈረጅ ስለሚቀናው፣ ዴሞክራሲን መላበስ ሳይሆን ጉልበተኝነት ልማዱ ነበር፡፡ ግራ ዘመም የሆነው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተብትቦት ትዕዛዝ ከላይ ወደ ታች ማንቆርቆር ባህሉ ከመሆኑም በላይ፣ ለመግለጽ አስቸጋሪ የሆነ የድብቅነት ባህሪ ነበረበት፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሊቀመንበርነት በኋላ ውስጡ መገላለጥ ሲጀምር ግን ዴሞክራሲያዊነት፣ ግልጽነትና ኃላፊነት ባዕድ ሆነውበታል፡፡ በዚህ የሽግግር ወቅት ይህንን የሠለጠነ ባህል መለማመድ አለበት፡፡ ይህ የሠለጠነ ባህሪ አይዋጥልኝም የሚል አባል ድርጅት ደግሞ እውነቱን ተናግሮ መንገዱን ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ልዩነትን በአግባቡ መያዝ እያቃተ የፀጥታና የደኅንነት ኃይሎችን በየጎራው መጎተት ሊከተል ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱ አደገኛ ጎዳና ውጤቱ ጥፋት ነው፡፡

ለአገርና ለሕዝብ እናስባለን የሚሉ ወገኖች ይኼ አደገኛ ዝንባሌ በአጭሩ ተቀጭቶ፣ በልዩነት ውስጥ መኖር እንዲለመድ ዕገዛ ያድርጉ፡፡ የቃላት ጦርነቱን ዳር ሆኖ እንደ ቴአትር መመልከት ለፀፀት ይዳርጋል፡፡ ‹በለው፣ ግፋው፣ አባረው. . .›› እያሉ ማሟሟቅም ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ አይበጅም፡፡ ይልቁንም በልዩነት ውስጥ መኖር መለመድ እንዳለበት ይስተጋባ!
ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment