Sunday, July 14, 2019

የአዴፓና የሕወሓት የቃላት ጦርነት ሥጋት ደቅኗል

(14 July 2019, (ሪፖርተር))--‹‹ሕወሓት ከምሥረታው ጀምሮ በማኒፌስቶው የአማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጇል››

አዴፓ

‹‹አገርን እየበታተነ ያለው የትምክህት ኃይል እንደፈለገው እንዲሆን ያደረገው አዴፓ ነው››

ሕወሓት

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ባለፈው ሳምንት በአንድ ቀን ልዩነት ባወጡት መግለጫ፣ የቃላት ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ሥጋት ደቅኗል፡፡


የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ካካሄደው የአንድ ቀን አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ አዴፓ አገርን እየበታተነ ያለውን የትምክህት ኃይል ዕድል አግኝቶ እንደፈለገው እንዲሆን እያደረገ ነው ብሎ፣ በአጠቃላይ በተፈጸመው ጥፋት በተለይም የድርጅቱ አመራሮችን ግድያ በጥልቀት በመገምገም ተጠያቂነት እንዲኖር በማድረግና ግልጽ አቋም በመውሰድ፣ አዴፓ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ አለበት ብሏል፡፡

‹‹የውስጥ ችግሮችን ለመሸፈን ጥፋቱን የሦስተኛ ወገን አለበት በማለት ማሳበብና ሌሎች ረዣዥም እጆች አሉበት በማለት ሕዝቡን ማወናበድ መቆም አለበት፤›› የሚለው የሕወሓት መግለጫ፣ አዴፓ በሁሉም ጉዳዮች ላይ የውስጥ ችግሮቹን በዝርዝር በመገምገም ግልጽ አቋሙን እንዲያሳውቅ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡ አዴፓ ይህን ማድረግ ካልቻለ ግን ሕወሓት ከአዴፓ ጋር አብሮ ለመሥራትና ለመታገል እንደሚቸገር አስታውቋል፡፡

ሐምሌ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ ስብሰባ የገባው የአዴፓ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ለሕወሓት መግለጫ የመልስ ምት ሰጥቷል፡፡ አዴፓ በመግለጫው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) ከምሥረታው ጀምሮ በ1968 ዓ.ም. ማኒፌስቶው የአማራን ሕዝብ በጠላትነት መፈረጁን ገልጾ፣ አጠቃላይ ትግሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የትሕነግ/ሕወሓትንና የጥፋት ኃይሎችን እኩይ ድርጊት መፋለም ሆኖ ሳለ ትግሉ በትሕነግ/ሕወሓትና በአዴፓ መካከል የሚካሄድ በማስመሰል፣ ወቅታዊ ጉዳታችንን እንደ ዘላቂ ሽንፈትና ውድቀት በመቁጠር፣ ዛሬም የአማራን ሕዝብ አንገት ለማስደፋት የተቀበረውን የትምክህት ትርክቱን ዳግም ይዞ ብቅ ማለቱ፣ ድርጅቱ መቼም ቢሆን መፈወስ የማይችል በሽታ ያለበት መሆኑን ያጋለጠ ተግባር ነው በማለት አዴፓ ኮንኖታል፡፡

‹‹ትሕነግ/ሕወሓት በፅናት የሚታገሉትንና ከእኔ ጎን አይሠለፉም የሚላቸውን ኃይሎች ሲሻው ትምክተኛ፣ ሲሻው ጠባብና አሸባሪ በማለት ታርጋ እየለጠፈ የሚያሸማቅቅ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት መሆኑን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል፤›› ያለው አዴፓ፣ የትሕነግ/ሕወሓት መግለጫ አዲስ ነገር ይዞ የመጣ ሳይሆን የተለመደ የፖለቲካ ሴራ ማሳያ ነው ብሎታል፡፡

የአገሪቱን ህልውናና ክብር አሳልፈው የሰጡና ኢትዮጵያን ለመበታተን ሌት ተቀን የማይተኙ ኃይሎች በስመ ለውጥ ግንባር በመፍጠር አሠላለፍ ባልለየ መልኩ ተደበላልቆ አንድ ላይ እንዲሆኑ በመደረጉ፣ በጥፋት ላይ ጥፋት እየተደራረበ አሁን ላለንበት ደረጃ በቅተናል የሚለው የሕወሓት መግለጫ፣ በተቃራኒው ለዚህች አገር ክብርና ህልውና ሲሉ ዕድሜ ልካቸውን የታገሉት የሚታደኑበት፣ የሚታሰሩበትና ጥላሸት የሚቀቡበት ሁኔታ ስለመፈጠሩ ገልጿል፡፡

ሕወሓት የትምክህት ኃይሎች የሚላቸው የሕዝብን መብትና ጥቅም ረግጠው የግል ፍላጎታቸውንና ያሻቸውን ለመፈጸም የሚጓጉትን ጥቂት ኃይሎች እንጂ፣ ሕዝብን ፈርጆ እንደማያውቅ ገልጿል፡፡ በማንኛውም መመዘኛ ትምክህተኛ ተብሎ የሚጠራ ሕዝብ እንደሌለ የሚገልጸው የሕወሓት መግለጫ፣ የአማራ ሕዝብም ትምክህተኛ ተብሎ ሊጠራ እንደማይችል ጠቁሟል፡፡ ‹‹ሆኖም ፀረ ሕዝብ የትምክህት ኃይሎች የቆየውን ኋላቀር ህልማቸውን ለማስፈጸም እንደ ሕዝብ ትምክህተኛ ተብለሃል በማለት ሕዝብን እያደናገሩ ይገኛል፡፡ በአማራ ሕዝብ ስም እየነገዱ በአሉባልታ ወሬ ሕዝቡ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ደሙን ለመምጠጥ አኮብኩበው እየጠበቁ ይገኛሉ፤›› ይላል የሕወሓት መግለጫ፡፡

አዴፓ በበኩሉ ‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል›› እንደሚባለው አገራችን አሁን ለምትገኝበት የፖለቲካ ብልሽት ዋነኛ ተጠያቂ ትሕነግ/ሕወሓት ሆኖ፣ የአማራን ሕዝብ ህልውናና ክብር የማይመጥን መግለጫ አውጥቷል ብሏል፡፡ ምንም እንኳን የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለስብሰባ የተቀመጠው ካጋጠመው ወቅታዊ ችግር በፍጥነት እንዴት መውጣት እንዳለበትና የለውጡን ቀጣይነት ለመጠበቅ ቢሆንም፣ ትሕነግ/ሕወሓት በመግለጫው ‹‹ራሱ ነካሽ፣ ራሱ ከሳሽ›› ሆኖ በመቅረቡ መግለጫ ለማውጣት መፈለጉን ጠቁሟል፡፡ አዴፓ በቅርቡ ካጋጠመው ሐዘን ሳይወጣ ትሕነግ/ሕወሓት እንዲህ ዓይነት መግለጫ ማውጣቱ፣ ከአንድ እህት ፓርቲ የማይጠበቅ አሳፋሪ ድርጊት ነው ሲል ኮንኖታል፡፡

ምንም እንኳን ሕወሓት በመግለጫው በዋናነት አዴፓ ላይ ቢያነጣጥርም፣ የፌዴራል መንግሥቱን ሳይሸነቁጥ አላለፈም፡፡ በዚህም መሠረት ተጀምሮ የነበረው ተስፋ ሰጪ ልማትና ዕድገት በአሁኑ ወቅት መሪ አልባ ሆኖ ቁልቁለት መውረድ ጀምሯል የሚለው የሕወሓት መግለጫ፣ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት ከምንም ጊዜ በላይ የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ እንዳልቻሉ ገልጿል፡፡ ‹‹የጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ግድያ የሚያረጋግጠው እውነትም መንግሥት የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ማክበር ተስኖት በግፍና ጭካኔ የሥልጣን ፍላጎታቸውን ማርካት የሚፈልጉ የትምክህት ኃይሎች እንዳሻቸው የሚፈነጩበት፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ መሽገው የሕዝቦች አለኝታ የሆነውን ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓት ለማፍረስ በግላጭ የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መፈጠሩን ነው፤›› ብሏል ሕወሓት በመግለጫው፡፡

አዴፓ ባወጣው መግለጫ ትሕነግ/ሕወሓት ፈጽሞ አክብሮት የማያውቀውንና ራሱ ሲጥሰው የነበረውን ሕገ መንግሥታዊና የፌዴራል ሥርዓት ጠበቃ በመምሰል የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ጭቁን ሕዝቦችን በማደናገር ለዳግም ሰቆቃ እንዲዳረጉ አድርጓል ብሏል፡፡

በፀረ ለውጥ እንቅስቃሴው አገራዊና ክልላዊ ለውጡ በጥርጣሬ እንዲታይ ትሕነግ/ሕወሓት ከጥፋት ኃይሎች ጀርባ መሽጎ አመራር እየሰጠ ነው የሚለው አዴፓ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የለውጥ ፍላጎት መነሻ ተደርገው የተወሰዱ አሳሪና ደብዳቢ ፀረ ዴሞክራቶችን፣ ሕዝብና አገርን በድፍረት የዘረፉ ሌቦችን፣ በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ትሕነግ/ሕወሓት አቅፎና ደብቆ ይዟል በማለት ይወነጅለዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ ትሕነግ/ሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ የዘመናት አስመሳይነቱን አጋልጧል የሚለው አዴፓ፣ ራሱን ብቸኛ የኢትዮጵያ ጠበቃ አስመስሎ ማቅረቡ የሞራልና የተግባር ብቃት የሌለው ድርጅት መሆኑን አሳብቆበታል ብሏል፡፡ በዚህም የትሕነግ/ሕወሓት መሰሪና አሻጥር የተሞላበት የዘመናት ባህሪው ተጋልጧል ሲል ገልጿል፡፡

‹‹ትሕነግ/ሕወሓት ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሁለት አገረ መንግሥት ዕይታ ያለው፣ አንድም ቀን ለሕዝቦች አንድነት የማይጨነቅ፣ በሥልጣን ላይ እስከቆየና ዕላፊ ጥቅም እስካገኘ ድረስ ብቻ አስመሳይ የአንድነት ኃይል ሆኖ መቀጠል የሚፈልግ፣ ነገር ግን እንደ ዛሬው በሥልጣን ላይ ሆኖ በአድራጊ ፈጣሪነት ሁሉንም ማሳካት ሳይችል ሲቀር፣ በቁም ቅዠትና ከትግራይ ሕዝብ ሥነ ልቦና ባፈነገጠ መልኩ ‹‹የዥዋዥዌ ፖለቲካን›› የሙጥኝ ያለ እምነት የማይጣልበት ድርጅት ነው፤›› የሚለው የአዴፓ መግለጫ፣ የአማራ ሕዝብና አዴፓ ሆን ተብሎ የተበላሸውን አገራዊ ፖለቲካ እንዲታረም፣ ከሌሎች የለውጥ ኃይሎች ጋር ሆኖ ፊት ለፊት ተፋልሞ የለውጡን ውጤቶች ጠብቆ ለመዝለቅ ሌት ከቀን የሚታትር ድርጅት እንጂ፣ እንደ ትሕነግ/ሕወሓት በከፋፋይነት በሽታ የተጠመደ ድርጅት አይደለም ብሏል፡፡

በየቀኑ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አዳጋች ደረጃ ላይ መደረሱን የሚገልጸው ሕወሓት በበኩሉ፣ የአገሪቱ ሁኔታ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ እየታወቀም ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በማስወገድ በቀላሉ ሥርዓት የማፍረስ ተግባርን በይፋ የሚያወግዝና የጠራ አቋም በመያዝ የሚደረግ ትግል አልታየም ብሏል፡፡ በተቃራኒው ግን ሁሉንም የለውጥ መሪዎች ነበሩ በማለት ይህ እኩይ ተግባር ቀጣይነት እንዲኖረውና በዚህ ተግባር ላይ እጃቸው የነበረ አካላት ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ ሆን ተብሎ ያለ ኃፍረት ጥረት እየተደረገ ነው ብሎ፣ የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት እንዲጠበቅ ኃላፊነት የተሸከሙ የፀጥታና ደኅንነት አካላት በተፈጸመው ጥፋት ላይ ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መንገድ እየተሠራበት አለመሆኑን በመግለጽ ሕወሓት ትችቱን አቅርቧል፡፡

ትሕነግ/ሕወሓት ይህን ወቅታዊ ሁኔታ የራሱን የዘመናት ወንጀሎች ለመሸፋፈን እየተጠቀመበት እንደሆነ የሚገልጸው አዴፓ፣ እውነትና ፍትሕ ቢኖር ኖሮ ላለፉት ዘመናት በትሕነግ/ሕወሓት የሴራ ፖለቲካ ምክንያት ለተለያዩ ጥናፋትና እንግልት በተዳረገው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ቅርቃር ውስጥ በወደቀው አገራዊ አንድነታችን ምክንያት፣ ከወገቡ ዝቅ ብሎና ከልቡ ተፀፅቶ የተበደለውን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ የነበረበት ዋነኛው ተጠያቂ ትሕነግ/ሕወሓት ነበር ብሏል፡፡ በመሆኑም ትሕነግ/ሕወሓት አዴፓ ይቅርታ ካልጠየቀ አብሮ ለመሥራት እንደሚቸገር መግለጹ፣ ‹‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ›› የሆነው የድርጅቱ የሴራ ፖለቲካ መገለጫ ነው ብሎታል፡፡

በእንዲህ ዓይነት ጠንካራ ቃላት ታጅበው በሁለቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የወጡት መግለጫዎች፣ ድርጅቶቹ የለየለት የቃላት ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ሁለቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የገቡበት የቃላት ጦርነትም በኢሕአዴግ ህልውናም ላይ ሆነ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ሥጋት መደቀኑ እየተነገረ ነው፡፡ አገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ ሆና አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ባለችበት ወቅት፣ ሁለቱ ፓርቲዎች የገቡበት ጦርነት ከእነሱ የሚጠበቅ እንዳልሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ወቅት እንደ ኢሕአዴግ አንድ ሆነን የአገሪቷን ሰላምና ደኅንነት እናስጠብቅ ማለት ሲገባቸው፣ በአደባባይ አንድ አይደለንም ብለው መናገራቸው ተስፋ ያስቆርጣል የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፣ ‹‹የጉልበተኛ ቋንቋ በመጠቀም እንደ ተራ ሰዎች ነው የተጣሉት እንጂ፣ ልምድ እንዳላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች እየተንቀሳቀሱ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አገሪቱ ከሁለቱም ፓርቲዎች የምትጠብቀውን አመራር እንዳታገኝ አድርገዋታል የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት መፈታት የማይችል ነው? ወይስ አንዱ በአንዱ ላይ ነጥብ ለማስቆጠር የሚደረግ አካሄድ ነው? ተብሎ ሊፈተሽ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

ሕወሓት በጀመረው የቃላት ጦርነት አዴፓን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከቶታል የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፣ አዴፓ በበኩሉ ያወጣው መግለጫ ራሱን ለመከላከል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ሁለቱም ፓርቲዎች አንዱ በአንዱ ላይ ነጥብ ለማስቆጠር የገቡበት የቃላት ጦርነት እንጂ፣ ከዚያ የዘለለ ነገር ይኖረዋል ብለው እንደማያምኑ ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም የእውነት ከተጣሉና ተጣልተው የሚቀጥሉ ከሆነ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ራሱ ችግር ውስጥ ይወድቃል ብለዋል፡፡

ለውጡን ተከትሎ አገሪቱ የተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ መውደቋ የሚታወቅ ሲሆን፣ በተለይም በለውጡ ደጋፊና በለውጡ አደናቃፊ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው ፍጭት የአገሪቱ አንድነትና ሰላም ከደፈረሰ ሰነባብቷል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥም በአገሪቱ የፖለቲካ ከባቢ ውስጥ ግንባር ቀደም የሆነው የኢሕአዴግ ህልውናም ሥጋት ተደቅኖበታል፡፡ በተለይ በኢሕአዴግ ፓርቲ አባል ድርጅቶች መካከል ያለው መቃቃርና አለመተማመን ለፓርቲው የመፈራረስ ሥጋት እንደደቀነበት የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በተለይም የአሁኑ የአዴፓና የሕወሓት የቃላት ጦርነት የፓርቲውን ህልውና በእጅጉ ይፈታተነዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከሁለቱ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ባሻገርም ቀሪዎቹ ኦዴፓና ደኢሕዴን በተለይ በሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ምክንያት የገቡበት ተቃርኖ ነገሮችን ሊያባብስ ይችላል ተብሎም ይፈራል፡፡ ለዚህም መነሻው በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ስለሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ በጉዳዩ ዙሪያ ጠንከር ያለ አቋማቸውን ማንፀባረቃቸው በሚመሩት ኦዴፓና ደኢሕዴን መካከል ሻካራ ግንኙነት እንዲኖር ሊያደርግ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ በመሆኑም አራቱም ፓርቲዎች እንዲህ ዓይነት ውጥረት ውስጥ ባሉበት ወቅት፣ አዴፓና ሕወሓት በጀመሩት የቃላት ጦርነት የኢሕአዴግ ህልውና በፍጥነት እንዲያከትም ማድረጉ አይቀሬ ነው እየተባለ ነው፡፡

ሕወሓት ባወጣው መግለጫ ራሱን የኢሕአዴግ አባል እንዳልሆነ ቆጥሮ የፌዴራል መንግሥት በቀጣዩ ምርጫ ላይ ያለውን አቋም በግልጽ እንዲያስቀምጥ መጠየቁ በጣም እንዳስደነገጣቸው የሚናገሩት፣ የሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት ናቸው፡፡ ሕወሓት በመግለጫው ራሱን የኢሕአዴግ አባል አድርጎ ሳይሆን የቆጠረው፣ ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ ነው የሚመስለው የሚሉት አቶ ውብሸት፣ አገሪቱም ሆነ ኢሕአዴግ አሁን የገቡበት ቀውስ መነሻው የሕግ አለመከበር ውጤት መሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹አገሪቱ በሕግ እየተመራች አይደለም፡፡ የፖለቲካው ሥርዓቱም እየበሰበሰ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህም ማሳያው መንግሥት ሕግ የጣሱ ሰዎችን አንዳንዶቹን በማሰር ሌሎቹን ደግሞ መተው ነው ብሎ፣ እንዲህ ዓይነት ቅጥ አምባሩ የጠፋበት አካሄድ ውስጥ መግባቱ አገሪቱን ዋጋ ያስከፍላታል ብለዋል፡፡ በዚህ አካሄድ አገሪቱ ያሉባትን እንደ ወሰንና የማንነት ጥያቄዎች መመለስ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡

ሕወሓት ለውጡን ተከትሎ ከማዕከላዊ መንግሥት የተገለለ ሲሆን፣ አሁን ከአዴፓ ጋር በጀመረው የቃላት ጦርነት ወደ ማዕከላዊ መንግሥት የመመለስ ፍላጎት እንዳለው ጠቁሟል፡፡ ሕወሓት በመግለጫው የአገሪቱ ህልውናና ደኅንነት ዋስትና እንዲኖረው ኢሕአዴግ ወደ ነባሩና የሚታወቅበት መለያው እንዲመለስ ጥሪ አቅርቧል፡፡ አዴፓም በበኩሉ የሕወሓትን መዳከም ተጠቅሞ የራሱን የፖለቲካ ቦታ መያዝ እንደሚፈልግ የሕግ ባለሙያው አቶ ሙሉጌታ ይገልጻሉ፡፡  ሆኖም ሁለቱም ፓርቲዎች እየሄዱበት ያለው መንገድ ጥሩ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል በተፈጠረው የቃላት ጦርነት መካከል አስታራቂ መግባቱ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን አራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች እርስ በርሳቸው ባለመተማመንና በመከፋፈላቸው ምክንያት ግንባሩ የመፍረስ ሥጋት ውስጥ ቢሆንም፣ ማዕከላዊ መንግሥቱን የሚመራው ኦዴፓና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱ ፓርቲዎች የገቡበትን የቃላት ጦርነት በመሸምገል ትልቅ ሸክም ወድቆባቸዋል ተብሏል፡፡ ሆኖም ነገሮች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ አገሪቱም ሆነ ኢሕአዴግ ፈታኝ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል እየተባለ ነው፡፡

በአራቱ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች መካከል ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ ግን እየቀጠለ ከሄደ አገር ሊያፈርስ እንደሚችል የሚጠቁሙት አቶ ውብሸት፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ አገሪቱን ሊታደጓት የሚችሉት የመከላከያ ሠራዊቱና የፀጥታ አካላት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የመከላከያ ሠራዊቱና የፀጥታ አካላቱ ከፓርቲዎቹ የፖለቲካ ወላፈን ራሳቸውን ጠብቀው፣ አገሪቱን ከቀውስ ለመታደግ ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው ሲሉ አቶ ውብሸት አሳስበዋል፡፡
ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment