Sunday, June 23, 2019

ጄነራል ሰዓረ መኮንን መገደላቸውን ሕወሓት አረጋገጠ

(23 Jun, (Jun))--ጄኔራል ሰዓረ መኮንን እና የቅርብ ወዳጃቸው ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ከምሽቱ 3 ሰዓት አካባቢ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አረጋገጠ። የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ሊቀ-መንበር ዶክተር ደብረ ጺዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው ተጨማሪ ግድያ ሊኖር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።


የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የመረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ሐሰን ኢብራሒም በባሕር ዳር የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት እና በአዲስ አበባ የተፈጸመው ጥቃት «መንግሥትን ለማዳከም» ያቀደ እንደነበር ተናግረዋል።

ጄኔራል ሐሰን በብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን ተናግረዋል። «ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ትናንት በባሕር ዳር የተከሰተውን አደጋ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሕልፈተ-ሕይወታቸው ጊዜ ድረስ ሥራውን እየመሩ እያለ፤ በሥራው ላይ እያሉ ነው ጉዳቱ የደረሰባቸው» ሲሉ አብራርተዋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር እና የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ሊቀ-መ
ንበር ዶክተር ደብረ ጺዮን ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው ተጨማሪ ግድያ ሊፈጸም ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ጄኔራል ሰዓረ እና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ «ከጸረ- ሕዝብ፤ ከሌላ ጥቃት ይከላከልልኛል፤ ይጠብቀኛል» ባሉት ጠባቂ መገደላቸውን የገለጹት ዶክተር ደብረ ጺዮን ጥቃቱን «የተናጠል፤ የአንድ ጥበቃ ወንጀል ብለን አንወስደውም። ከባሕር ዳሩ ድርጊት ጋር የተያያዘ ነው» ብለዋል።

ጄኔራል ሰዓረ በአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ባላቸው ኃላፊነት ምክንያት በዕቅድ የተያዘ ጥቃት ዒላማ መሆናቸውንም ተናግረዋል። «ይኸን ግድያ የሁለቱ ጄኔራሎች ብለን አንወስደውም። ሌሎች ግድያዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት እንችላለን» ሲሉ ሥጋታቸውን በመቐለ ከተማ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርገዋል። «በባሕር ዳር ላይ ያነጣጠር አይደለም፤ በአገር ላይ ያነጣጠረ ነው። መንግሥትን የማፍረስ፤ መንግሥትን የማንበርከክ» ጥረት እንደሆነም ዶክተር ደብረ ጺዮን ገልጸዋል።

ጄኔራል ሐሰን በበኩላቸው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የኢትዮጵያ ሕዝብ "እርስ በርስ በብሔር እንዲናቆር ወይም ትርምስ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ይፈጠራል ብለው ያሰቡትን ዕድል ለመጠቀም እና ለማሳካት የተደረገ" ነው ሲሉ ተናግረዋል።

«ጥቃቱ በግለሰቦች ላይ የተሰነዘረ» አይደለም ያሉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የመረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ሐሰን ኢብራሒም «የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስ በርሱ ለማናከስ፤ የቆየ አንድነቱን ለማፍረስ በሰራዊቱም ውስጥ ጸንቶ የቆየውን አንድነት ለማፍረስ እና በዚህ አጋጣሚ በሀገር ላይ የመፍረስ አደጋን በማስከተል ያሰቡትን ዕኩይ አላማ የማሳካት ዕቅድ ይዘው ያደረጉት ተግባር ነው» ሲሉ ተናግረዋል።
DW Amharic

No comments:

Post a Comment