Thursday, December 27, 2018

ከስህተቱ የማይማር የትውልድ መሳቂያ ይሆናል!

(Dec 27, (ሪፖርተር))--‹‹ብልህ ከሌሎች ስህተት ሲማር ሞኝ ግን ከራሱም አይማርም›› የሚለው ዕድሜ ጠገብ አባባል ትልቅ መልዕክት አለው፡፡ የሰው ልጅ በሥራ ላይ ሲሆን ስህተት ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ‹‹ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም›› የሚል የዛገ ተረት እየተረተ መኖር ግን አይችልም፡፡ ስህተት ሲደጋገም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ስህተትን በጣም መቀነስ ብቻ ሳይሆን፣ በተቻለ መጠን ላለመሳሳት ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡ ዘመኑ የውድድር ስለሆነ፡፡ ይኼንን ጉዳይ ወደ ወቅታዊው የአገሪቱ ፖለቲካ ስንመልሰው፣ የዘመናት ስህተት ያለቀቃቸውና ዛሬም እንደ በፊቱ የተለመደውን ስህተት የሚደጋግሙ በስፋት ይታያሉ፡፡

ዓመታት ሲለዋወጡ ትውልድም በዚያው መጠን መለዋወጡ የግድ ነው፡፡ ይህ ያለንበት ጊዜ ደግሞ ለስህተት ወይም ለክፍተት ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ፣ በአጋጣሚ የተገኘ መልካም ዕድል ካመለጠ መመለሻ የለውም፡፡ ትናንት በነበረ ዝና የተገኘ ድጋፍ በሰዓታት ውስጥ እንዳልነበረ ሊሆን ይችላል፡፡ በአፍ ወለምታ በተፈጠረ ተገቢ ያልሆነ ንግግር ወይም አለኝ ተብሎ በሚታመን ድጋፍ ሳቢያ በመታበይ ነገሮች ግልብጥብጣቸው ሲወጣ፣ አጋጣሚዎች ካመለጡ በኋላ መንደፋደፍ ትርፉ መላላጥ ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ ከሚባሉ ችግሮች መካከል አንዱ፣ ተቀራርቦ መነጋገር አለመቻል እንደነበር ይታወቃል፡፡ ካለፉት ዘጠኝ ወራት ወዲህ ግን እንኳን አገር ቤት ያሉት ቀርቶ ነፍጥ አንግበው በረሃ የወረዱት ሳይቀሩ ተመልሰው በመምጣት፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን በተመቻቸ ምኅዳር ላይ ለማከናወን ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ተስፋ ሰጪ ጅምሮችም በስፋት ታይተዋል፡፡ ካሁን በኋላ ለኢትዮጵያ የሚበጀው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንደሆነ ብዙዎችን አስማምቷል፡፡

ይሁን እንጂ ‹‹በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል›› እንዲሉ፣ ይኼንን መልካም ጅማሬ የሚፈታተኑ ችግሮች ታይተዋል፡፡ ችግሮቹ በግጭት እየታጀቡ ንፁኃን በከንቱ ሕይወታቸውን ገብረዋል፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ የማይገባባቸው ሥፍራዎች እየተበራከቱ ናቸው፡፡ ካለፈው ስህተት መማር የማይፈልጉ ኃይሎች ያንኑ ስህተት እየደጋገሙ ችግር መፍጠራቸውን ቀጥለዋል፡፡

ይህ ግን የት ድረስ እንደሚወስዳቸው ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ ከስህተት አለመማር ግን አለ የሚባል ድጋፍ እንደሚያሳጣ ቢታወቅ ይመረጣል፡፡ ካልሆነ ደግሞ የትውልድ መሳቂያና መሳለቂያ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ከታሪክ የማይማር ታሪክን መድገሙ አይቀርምና፡፡  ከዚህ ቀደም አማፂ ከነበሩ ኃይሎች ጋር መንግሥት ያደረገው ድርድርና ስምምነት ምን እንደነበር በተደጋጋሚ መጠየቁ አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ የድርድሩና የስምምነቱ ዝርዝር ባይገለጽም፣ በአንድ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ግን መግባባት ያስፈልጋል፡፡

አማፂ የነበረ ኃይል ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ሲቀላቀል ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ትጥቁን መፍታት አለበት፡፡ ሠራዊቱን ወደ ተዘጋጀለት ካምፕ አስገብቶ ተገቢው ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ሥምሪት የሚደረግ ሲሆን፣ የፖለቲካ ድርጅቱም ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚፈልገውን ጨዋነትና ዲሲፕሊን ይዞ ወደ ተፎካካሪነት ይሸጋገራል፡፡ ከዚህ ውጪ ትጥቅ አልፈታም ማለት፣ ያሉትን አስተዳደራዊ መዋቅሮች በማፈራረስ በራሴ አምሳያ እተካለሁ ማለትና የመሳሰሉትን ሕገወጥ ድርጊቶች መፈጸም አይቻልም፡፡ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅና በምዕራብ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋ፣ እንዲሁም በሆሮ ጉድሩ ዞኖች ውስጥ በመንግሥት ተሿሚዎች፣ በፀጥታ አስከባሪዎችና በንፁኃን ላይ ተፈጸመ የተባለው ግድያና የመንግሥት መዋቅሮችን ሥራ ማስቆም ሕገወጥነት ነው፡፡ በሕግ የሚያስጠይቅም ነው፡፡


ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን ከተቀላቀሉ አማፂያን መካከል አንዱ በሆነው ኦነግ ታጣቂዎች ተፈጽሟል የተባለው ድርጊት እጅግ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ክልል ገዥ ፓርቲ ኦዴፓ ከኦነግ ጋር በመሆን ሌሎች ፓርቲዎችን በማሳተፍ የጋራ መድረክ መፍጠራቸው ይታወሳል፡፡

የመድረኩ ዋነኛ ዓላማም ችግሮች ሲያጋጥሙ በመነጋገርና በመደራደር ለመፍታት እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ ይኼንን የመሰለ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ወደ ጎን በማለት ሕዝብን ማተራመስና አገርን ቀውስ ውስጥ መክተት ከስህተት በላይ የገዘፈ ድርጊት ነው፡፡ የኦነግ አመራሮች ከክልሉ መንግሥት ጋር በሚያደርጓቸው ውይይቶች ቃል የገቧቸውን ጉዳዮች ታች ወርደው ተግባራዊ እያደረጉ አይደሉም ተብለው በክልሉ መንግሥት እየተወቀሱ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ንፁኃን ይሞታሉ፣ ይፈናቀላሉ፣ ንብረታቸው ይወድማል፣ መንገዶች እየተዘጋጉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ይቋረጣሉ፡፡

ሕዝብን እወክላለሁ የሚል ኃይል በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመሳተፍ አገር ውስጥ ገብቶ ሰላም የሚያደፈርስ ከሆነ፣ የሕዝብ ተወካይነቱ የሚለካው በምንድነው? በአንድ በኩል መጪው ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ገደብ ነው መደረግ ያለበት እያለ የሚወተውት ኃይል፣ ሰላም እየደፈረሰ ምን ዓይነት ምርጫ ነው የሚጠብቀው? በስህተት ላይ ስህተት እየደራረቡ መጓዝ አይቻልም፡፡ ሰላማዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በአመፃ ውስጥ ሊካሄድ አይችልም፡፡ 

የክልሉ መንግሥት፣ ገዥው ፓርቲም ሆነ ፖሊስ ከዚህ በኋላ የአመፃ ድርጊቶችን እንደማይታገሱ አስታውቀዋል፡፡ አሁንም ሰላማዊ ጥረቱ ቀጥሎ ችግሮች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ቢፈቱ ይመረጣል፡፡ ችግሮች እንዲፈቱ ግን የሁሉም ወገኖች ትብብር አስፈላጊ ነው፡፡ ሕጋዊ መንገዶችን ተከትሎ ችግሮችን መፍታት ሲቻል አላስፈላጊ ደም መፋሰስ ውስጥ መግባት ለበለጠ ስህተት ይዳርጋል፡፡

በተለይ የውዝግቡ መነሻ መሆኑ እየተነገረለት ያለው ኦነግ አመራሮች ፍላጎታቸውን በግልጽ ተናግረው የመፍትሔው አካል ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ ምን እንደሚፈልጉ ለሕዝብ ማሳወቅ አለባቸው፡፡ በተድበሰበሱ አነጋገሮች ሰላም አይመጣም፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ የሚፈልገው ግልጽነት ነው፡፡ ግልጽነት ካለ ደግሞ ተጠያቂነት ይኖራል፡፡ ተጠያቂነት እየጠፋ የንፁኃን ሕይወት ለአደጋ መጋለጥ የለበትም፡፡ ከዚህ በፊት በተፈጸሙ ስህተቶች ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚሸከመው በላይ መከራ አሳልፏል፡፡

ካሁን በኋላ ወደ ኋላ እየተመለሱ ስህተትን መደጋገም ፈጽሞ አይቻልም፣ የሚታገስ ትውልድም የለም፡፡ ሕዝብን ረስቶ ትኩረትን ሥልጣን ላይ ብቻ በማድረግ አገርን ማተራመስ የማይወጡት አዘቅት ውስጥ ይከታል፡፡ እንኳን አሁን ያለው ትውልድ መጪውም ይኼንን ዓይነቱን አሳዛኝ ድርጊት ከታሪክ መጻሕፍት ማንበብ አይፈልግም፡፡

አሁን የሚፈለገው በዴሞክራሲያዊ መንገድ መነጋገር ብቻ ነው፡፡ ጨዋነትን የተላበሰ፣ የሰከነና በመርህ ላይ የተመሠረተ ውይይትና ድርድር እንዲኖር የዓመታት ስህተቶችን ማረም የግድ ይላል፡፡ በዛቻና በፉከራ የታጀበ ድንፋታ ለአገር ፋይዳ የለውም፡፡ የተለመዱ ስህተቶችን በዚህ ዘመን እየደጋገሙ ወጤት መጠበቅ ዘበት ነው፡፡ ለዚህም ነው ከስህተቱ የማይማር የትውልድ መሳቂያ ይሆናል የሚባለው!
ሪፖርተር (ርዕሰ አንቀጽ)

No comments:

Post a Comment