Thursday, December 27, 2018

የሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል ተግባርና ኃላፊነቶች ምንድን ናቸው?

(Dec 27, (ሪፖርተር))--እሑድ ታኅሳስ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ቤተሰቦቻቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ መቋቋሙ የተገለጸውና ‹‹የሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ወታደራዊ ኃይል፣ የተሰጠውን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ያደረገውን ዝግጅትና ብቃት የሚያሳይ ወታደራዊ ትርዒት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ለሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት አሳይቷል።

የአባላቱን የብቃት ደረጃ ለማሳየት ወታደራዊ ትርዒት ያቀረበው የሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል የመከላከያ ሠራዊቱን የደንብ ልብስና መለዮ የሚጠቀም ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም በመከላከያ ሠራዊቱ አደረጃጀት ውስጥ በሕግ የሚታወቅ ባለመሆኑ፣ ሕጋዊ አደረጃጀቱንና ተግባርና ኃላፊነቱን የተመለከቱ ጥያቄዎችን በርካቶች አንስተዋል። ጥያቄዎቹን መነሻ በማድረግ ሪፖርተር የሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል የተመሠረተበትን ሕግና የሕጉን ይዘት ተመልክቷል።  የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል የተቋቋመው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም. ባወጣው ደንብ ቁጥር 426/2010 ነው። በዚህም መሠረት የጥበቃ ኃይሉ በሕግ ዕውቅና አግኝቶ ከተመሠረተ ስድስተኛ ወሩ ላይ ይገኛል።

የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል የተቋቋመበት ዓላማ አስፈላጊ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ፣የመንግሥትና የአገር መሪዎችን ደኅንነትና ቤተ መንግሥትን መጠበቅ እንደሆነ የተቋቋመበት ደንብ አንቀጽ አምስት ይደነግጋል።የመንግሥትና የአገር መሪዎች ማለት ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ርዕሰ ብሔር መሆናቸውን ደንቡ ይደነግጋል። የጥበቃ ኃይሉ ለኦፕሬሽን ሥራዎች ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ የኦፕሬሽን ሥራዎች ማለት የዕዝ ሰንሰለትና በደንቡ የተደነገጉትን ዋና ተግባራት እንደሚያጠቃልል ደንቡ ያመለክታል።

የጥበቃ ኃይሉ ለአስተዳደራዊ ሥራዎች ሲባል ተጠሪነቱ ለአገር መከላከያ ሚኒስቴር ቢሆንም፣ ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት መሆኑ በደንቡ ተደንግጓል። አስተዳደራዊ ሥራዎች ማለት ከሰው ኃይል አስተዳደር፣ ከበጀት አስተዳደርና ከሌሎች ተዛማጅ ሥራዎች ጋር የተያያዘ መሆኑም ተመልክቷል።

በመሆኑም የሰው ኃይል ምልመላ፣ ሥልጠና፣ ወቅታዊ ግምገማና ዝውውር ወይም ስንብትን በተመለከተ መመርያዎችን ራሱ አዘጋጅቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በማስፈቀድ ተግባራዊ እንደሚያደርግ፣ ለሰው ኃይል ምልመላ፣ ሥልጠናና ቅጥር ከመከላከያ ሚኒስቴርና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚፈጽም ተደንግጓል።

የጥበቃ ኃይሉ በዋናነት ጥበቃ የሚያደርገው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለርዕሰ ብሔሩና ለትዳር አጋሮቻቸው እንዲሁም በሥራቸው የሚተዳደሩ እስከ 21 ዓመት የሆናቸው ልጆቻቸውን ያጠቃልላል። በተጨማሪም ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ለርዕሰ ብሔር ከእነ ቤተሰቦቻቸው የደኅንነት ጥበቃ እንደሚያደርግ ተደንግጓል።  ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የሌሎች አገሮች መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎችም ጥበቃ ያደርጋል።

የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስፈልጉ ማናቸውም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቁ ቁሳቁስ፣ ተሽከርካሪዎች፣ ትጥቆችና አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎችን እንደሚታጠቅም ደንቡ ይደነግጋል።  አስፈላጊ ቴክኖሎጂ ለሚለው ሐረግ ደንቡ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ ይኸውም፣ ‹‹በደንቡ የጥበቃ ሽፋን ያገኙትን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያግዝ ተሽከርካሪ፣ ሰው አልባ አውሮፕላን፣ ሔሊኮፕተር፣ ደረጃውን የጠበቀ ትጥቅ፣ እንስሳትና ሌሎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን›› እንደሚያጠቃልል ደንቡ ይገልጻል።

ጥበቃ ከሚደረግባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ቤተ መንግሥት ሲሆን፣ ለዚህም ራሱን የቻለ ትርጓሜ ይሰጣል። ‹‹ቤተ መንግሥት ማለት የመንግሥትና የአገር መሪዎች የሚሠሩበትና የሚኖሩበት ማንኛውም ሥፍራ ሲሆን፣ ሁለቱም ቤተ መንግሥቶች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግቢና የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የቪአይፒ (VIP) ተርሚናል፣ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የርዕሰ ብሔሩንና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጊዜያዊ የሥራና የማረፊያ ቦታዎችን ያጠቃልላል፤›› የሚል ሕጋዊ ትርጓሜ አስቀምጧል።

የጥበቃ ኃይሉ በሕጉ የጥበቃ ሽፋን የተሰጣቸውን የመንግሥት መሪዎችን ደኅንነትና ቤተ መንግሥትን ለመጠበቅ አስፈላጊ ዕርምጃ እንደሚወስድ የተደነገገ ሲሆን፣ ማንኛውም የፌደራል ወይም የክልል የፀጥታ አካልም ሆነ ሌላ ተቋም በዚህ ደንብ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲባል ከጥበቃ ኃይሉ ለሚቀርብ ማንኛውም የትብብር ጥያቄ የመተባበር ግዴታን ይጥላል። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ይኼንን ኃላፊነት ይወጣ የነበረው የንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘበኛ ሠራዊት እንደነበር ሲታወስ፣ በደርግ ጊዜ ደግሞ ልዩ ጥበቃ ብርጌድ የሚባል ኃይል እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment