(Feb 01, 2013, በኡመልኸይር ቡሎ)--ቀድሞ የነበሩት ባህላዊ አልባሳት በጣም ነጭና ሰፊ በመሆናቸው ሁልጊዜና በየትኛውም ሥፍራ ለመልበስ አስቸጋሪ በመሆናቸው ለበዓላት፣ ለሠርግ እና ለተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች ካልሆነ በስተቀር አይለበሱም ነበር።
በአሁኑ ጊዜ እየተዘጋጁ የሚቀርቡ የሀገር ልብሶች ግን በተለያየ ዲዛይን ዘመኑን ተከትለው ስለሚዘጋጁ በዘወትር ቀናት ለመልበስ ይፈጠር የነበረውን ውሱንነት አስቀርተውታል። ይህ በፎቶው ላይ የምትመለከቱት ዘመናዊ የሀገር ልብስ ቀላልና ማራኪ ተደርጐ በመሠራቱ ጊዜና ቦታ ሳንወሰን በሀገር ምርታችን እንድንዋብ አግዟል።
ይህ ዘመናዊ የሀገር ልብስ የተዘጋጀው በጣም
ነጭ ካልሆነ የጥጥ ጨርቅ በሱሪና በእጀ ጉርድ አላባሽ ነው። የበለጠ ለማስዋብና ዘመናዊነትን እንዲላበስ ደግሞ
የአላባሹን አንገት በጣም ሰፊና አንገቱ ዙሪያ ማራኪ የሆነ ጥለት ተደርጐበታል። ሱሪውም ከላይ ሰፋ ብሎ ከጉልበት
በታች ረዘም ያለና ባት ላይ የሚጣበቅ ጥልፍ አለው። በእዚህ ዓይነት መዘጋጀቱ ልብሱ ቀላልና በማንኛውም ቦታ
ለመልበስ ምቹ እንዲሆን እንደሚያደርገው ዲዛይነሯ ወይዘሮ ፍቅርተ አዲስ ትገልጻለች።
ይህን የተዋበ ዘመናዊ የሀገር ልብስ ተረከዙ ከፍ ካለ ጫማ ጋር በሠርግ፣ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች፣ በእረፍት ቀን፣ በቢሮ፣ በመሳሰሉት ቦታዎች ሁሉ በመልበስ መድመቅ እንደሚቻልም ዲዛይነሯ ትናገራለች።
አዲስ ዘመን
No comments:
Post a Comment