(Feb 11, 2013, አዲስ አበባ)--ከፍተኛ የሕክምና ወጪ በሚጠይቅ ሕመም በተያዘ የአንድ ሰው ታሪክ ልነሳ። በሽታው «ሄፕታይተስ ቢ» ይባላል።
ግለሰቡ በጤና ተቋም ተመርምሮ በሽታው እንዳለበት ካረጋገጠ በኋላ የታዘዘለትን መድኃኒት ለመግዛት ወደ መድኃኒት
ቤት ያመራል። የአንዱ መድኃኒት ዋጋ ሰባት ሺ ብር ነው። ስድስቱን በአርባ ሁለት ሺ ብር ገዝቶ ከሕመሙ ለመፈወስ
በመጓጓት እቤቱ ይገባል።
ባለሙያዎች መድኃኒቱ ትክክለኛውን ተመሳስሎ የተሠራ መሆኑን ያረጋግጣሉ። ስለፈዋሽነቱም ለማረጋገጥ ወደ ጤናና ሥነምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት (ፓስተር) ይላካል። ውጤቱም የመድኃኒቱን ፈዋሽነት ውድቅ ያደረገ ነበር።
ይህ መድኃኒት ከየት መጣ? ሕጋዊ ፈቃድ አውጥቶ በሚንቀሳቀስ መድኃኒት ቤት እንዴት ሊገኝ ቻለ? በአዲስ
አበባ ያለውን ሕገወጥ የመድኃኒት ሽያጭ ለመቆጣጠር የተቋቋመው የአዲስ አበባ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ
ባለሥልጣን ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ሙከራ ተቋሙ የመድኃኒቱን ግዢ የፈጸመበትን ሕጋዊ ሰነድ ማቅረብ አልቻለም።
ይህም መድኃኒቱ በኮንትሮባንድ ወደ ሀገር ውስጥ የገባ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ነበር። መድኃኒት ቤቱ ታሸገ። በሽያጭ
ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ባለሙያዎችም በሥራቸው ተጠያቂ ሆኑ።
በሀገራችን የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጠር
ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ቢሆንም ሕገወጥ ነጋዴዎች የረቀቀ ስልት በመጠቀም ከአልባሳትና ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ጀምሮ
የተለያዩ መድኃኒቶችን ያስገባሉ። ያሠራጫሉ። ሌሎች ቁሳቁስ በሀገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያስከትሉት ሳንካ
እንዳለ ሆኖ መድኃኒቶች በዚህ መልኩ ገብተው ጥቅም ላይ መዋላቸው ተደራራቢ ችግሮችን ያመጣሉ።
በኮንትሮባንድ የሚገቡ መድኃኒቶች ችግር
በሦስት መንገድ ይገለጻል የሚሉት የፌዴራል ምግብ መድኃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን
የኢንስፔክሽንና ቅኝት ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አበራ ማኅበራዊ ሳንካውን ያስቀድማሉ። በኮንትሮባንድ ገብተው ጥቅም
ላይ የሚውሉ መድኃኒቶች ጥራታቸውን፣ ፈዋሽነታቸውንና ደህንነታቸውን በሚያረጋግጠው አካል ተፈቅደው የማይገቡ
በመሆናቸው ከማዳን ይልቅ ለሌላ በሽታ ሊዳርጉ ይችላሉ። መድኃኒቶቹ በሕገወጥ መንገድ የሚጓጓዙ ስለሆነ ተገቢውን
የቅዝቃዜ ወይም የሙቀት መጠን የጠበቁ አይደሉም። በዚህም የተነሳ ለሕመምተኛው የሚጠበቀውን ፈውስ ላያስገኙ ይችላሉ።
በኮንትሮባንድ የሚገቡ መድኃኒቶች ኢኮኖሚያዊ
ተጽዕኖ ሁለተኛው ሀገራዊ ጉዳት ነው። ለመንግስት መከፈል ያለበት ቀረጥ ለሕገወጥ ነጋዴዎች ሀብት ማከማቻ ይሆናል።
ትክክለኛውን አቅጣጫ ተከትለው የሚሠሩ ነጋዴዎችም ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል። የድርጊቱ ፖለቲካዊ ተጽዕኖም ሌላው
የሚነሳ ጉዳይ ነው። ሕገወጦች መድኃኒቶችን ለማዘዋወር በሚያደርጉት ሙከራ ሁካታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። በተደራጀ ሁኔታ
የሚንቀሳቀሱት ሕገወጥ የመድኃኒት አስመጪዎች ድርጊቱን ሲፈጽሙ ከመንግሥት አካላት የሚደርስባቸውን ቁጥጥር ጥሰው
ለማለፍ በመሣሪያ የታገዘ ጥቃት ስለሚፈጽሙ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ይፈጥራል።
በኮንትሮባንድ የሚመጡ መድኃኒቶች ይህን ሁሉ
ሀገራዊ ችግር እየፈጠሩም በተለያየ መንገድ ሠርገው በመግባት በየመድኃኒት መሸጫዎች ይሠራጫሉ። ችግሩን ለማስወገድ
በፌዴራልና በክልል ደረጃ የተዘረጋው መዋቅር ሊገታቸው አልቻለም። የኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ
አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር በመቀናጀት በመግቢያ ኬላዎች ላይ ቁጥጥር
ያደርጋል። ተቋሙ ከዚህ ባለፈ በሀገር አቀፍ ደረጃ መድኃኒት የሚያስመጡና የሚያከፋፍሉ ተቋማትም ላይ ፍተሻ
ያደርጋል።
መድኃኒት ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡና
የሚያከፋፍሉ ድርጅቶች በዓመት አራት ጊዜ ቅኝት ይደረግባቸዋል። መድኃኒቶቹ ሲገቡ የተሰጣቸውን መለያ ቁጥር
በማስተያየት ትክክለኛ መሆናቸው ቁጥጥር ይደረጋል። አቀማመጣቸውና የሳኒቴሽን ሁኔታ ፍተሻ በማድረግ መድኃኒቶቹ
ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ጥረት ይደረጋል።
በመድኃኒት አስመጪዎች ላይ በሚደረገው
ቁጥጥር በኮንትሮባንድ የገቡ ሕገወጥ መድኃኒቶችን ይዘው የሚያከፋፍሉ አስመጪዎች እንደማይገኙ የፌዴራል የምግብ
መድኃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን አዳነ
ይናገራሉ። ይሁንና እስከ አሁን በተደረገው ቁጥጥር ሁለት ተቋማት ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው መድኃኒት በማስገባት ሥራ
ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ጉዳያቸው በሕግ አግባብ ተይዞ ተገቢውን ቅጣት አግኝተዋል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በሚያደርገው ቁጥጥር በ2004 የበጀት ዓመት ብቻ ከ8 ሚሊዮን
ብር በላይ የሚገመት ሕገወጥ የኮንትሮባንድ መድኃኒት በመግቢያ ኬላዎች ላይ ይዟል። እነዚህ መድኃኒቶች
ደህንነታቸው፣ ጥራታቸውና ፈዋሽነታቸው በሚመለከተው አካል ፍተሻ ያልተደረገባቸው ናቸው። የሚጓጓዙት መድኃኒት
የሚያስፈልገውን ጥንቃቄ ባልጠበቀ መልኩ በግመልና በሌሎች እንስሳት ተጭነው ነው። መድኃኒቶቹ በአካባቢው ላይ ጉዳት
የሚያስከትሉ ከሆነ እንዲቃጠሉ ሲደረግ ጎጂ ሆነው የተገኙት ወደመጡበት አገር እንዲመለሱ ይደረጋል።
በኮንትሮባንድ የሚገቡ መድኃኒቶችን
የመቆጣጠሩ ሥራ የተጠናከረ ቢሆንም ሾልከው የሚገቡት በመሸጫ መደብሮች የሚገኙበት ሁኔታ ይኖራል። ይህን የሚቆጣጠሩት
የክልል አስተዳደሮች ሲሆኑ በአዲስ አበባ ደረጃ የከተማው የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ ባለሥልጣን ነው።
በአዲስ አበባ ከአምስት መቶ በላይ የሚሆኑ
በመድኃኒት ችርቻሮ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች አሉ። በእነዚህ ተቋማት ላይ በሚደረገው ድንገተኛ ቁጥጥር የሚገኘው አቢይ
እንከን ከተፈቀደላቸው ደረጃ በላይ መድኃኒት ይዞ መገኘት ነው፡፡ መድኃኒት ቸርቻሪዎች ባላቸው አቅምና በባለሙያው
ደረጃ የሚይዙትም መድኃኒት የተለያየ ነው፡፡ መድኃኒት ቤት የሚል ስያሜ ያላቸው በፋርማሲ ሙያ በዲግሪ ደረጃ
በተመረቀ ባለሙያ ሥራው ሲመራ ለመድኃኒት መደብሮች በዲፕሎማ የሠለጠነ ባለሙያ በቂ ነው። እነዚህ ሁለቱ መድኃኒት
ቸርቻሪዎች የሚይዙት መድኃኒት ደረጃ የተለያየ ነው። በአዲስ አበባ በሚደረገው ቅኝት አንዳንድ መደብሮች ከደረጃቸው
በላይ የሆኑ መድኃኒቶችን ይዘው ይገኛሉ። ያኔ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድባቸዋል።
የአዲስ አበባ የምግብ የመድኃኒት ጤና
ክብካቤ ቁጥጥር ባለሙያ የሆኑት አቶ ኤፍሬም ግርማ በከተማዋ በሚገኙ መደብሮች በኮንትሮባንድ መልክ የገቡ
መድኃኒቶችን ድንገት በሚደረገው አሰሳ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራሉ። ቢሮው በሚያደርገው ክትትል መደብሮቹ
የሚይዙት መድኃኒት ከአከፋፋዮቹ ከተረከቡት ጋር ተመሳሳይ መለያ ቁጥር እንዳለውና ሌሎችንም ሰነዶች ያመሳክራሉ።
በዚህ መንገድ በሚደረገው ክትትል ብዙ ጊዜ እንከን አይገኝም። መደብሮቹ በመደርደሪያቸውም ሆነ በመጋዘን
የሚያስቀምጡት መድኃኒቶች ከሕጋዊ አካል የተገዙ ናቸው።
በመድኃኒት ቤቶች ቁጥጥር የሚያደርገው አካል
የቅኝት ወሰን በመድኃኒት መቸርቸሪያውና በመጋዘኑ የተገደበ ነው። ፍቃድ የተሰጠው በእነዚህ ቦታዎች ለሚከናወነው
እንቅስቃሴ ብቻ በመሆኑ ሌሎች የተጠረጠሩ ቦታዎችን ለመፈተሽ የፍርድ ቤት ማዘዣ ያስፈልጋል። በሕገወጥ የመድኃኒት
ንግድ ላይ የተሰማሩ መድኃኒት ቤቶች ደግሞ በኮንትሮባንድ ያስገቧቸውን መድኃኒቶች የሚያከማቹት ሌላ ቦታ ነው።
በረቀቀ መንገድ የሚከናወነው ሕገወጥ
የመድኃኒት ሽያጭ ይፋ የሚወጣው በሁለት መንገድ ነው። በአንድ በኩል በመድኃኒት መሸጫዎቹ የሚሠሩ ባለሙያዎች
በተለያየ ምክንያት ከሥራ ሲለቁ በሚሰጡት ጥቆማ ሕገወጦቹ ሥራቸው ይጋለጣል። አንዳንድ ተጠቃሚዎች የገዙት መድኃኒት
ትክክለኛነት ሲያጠራጥራቸው ወይም የጎንዮሽ ጉዳት ሲያስከትልባቸው ለሚመለከተው አካል የሚሰጡት ጥቆማ ለሌላው መንገድ
ነው። ቸርቻሪዎቹ ከአከፋፋይ የገዙበትን ማመሳከሪያ ደረሰኝ ማቅረብ ካልቻሉ መድኃኒቱ በሕገወጥ መንገድ የገባ
ለመሆኑ እርግጠኛ ይኮናል።
በመግቢያው ላይ ታሪኩ የተጠቀሰው ግለሰብ
ገጠመኝ ይህን ያረጋግጣል። በከፍተኛ ወጪ የተገዛው ሕይወት አድን የተባለ መድኃኒት አጠራጣሪ ነገሮች ስለታዩበት
አገልግሎት ላይ አልዋለም። ግለሰቡ መድኃኒቱን ባለማወቅ የተጠቀመ ቢሆን የሚጠበቀውን ፈውስ አያገኝም። ምናልባትም
ሕይወትን የሚያሳጣ አጋጣሚም ሊፈጠር ይችላል።
በኮንትሮባንድ መድኃኒት የሚያስገቡ ሰዎች
ዓላማ አንድ ነው፡፡ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ትርፍ ማግኘት። ሕጋዊ ቢሆኑ ለመንግሥት የሚከፍሉትን ታክስና ሌሎች
ወጪዎች ወደ ግል ካዝናቸው ለማስገባት በሚያደርጉት ሩጫ በሰው ላይ ሞት ይፈርዳሉ። በሀገር ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ
እንቅስቃሴ ላይ ጥቁር ነጥብ ያስቀምጣሉ።
መድኃኒትን እንደ ሌሎች ሸቀጦች
በኮንትሮባንድ ባልተገባ አያያዝና ማጓጓዣ ማስገባት የከፋ ወንጀል ነው። ይህ ሕገወጥ ንግድ ጥቂቶቹን በሚሊዮን
የሚቆጠር ብር ሲያሳፍስ የበርካቶችን ሕይወት አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል። ኅብረተሰቡ ድርጊቱን ለመቆጣጠር ከሚተጉት
ባለድርሻ አካላት ጎን በመሆን ሕገወጦችን በማጋለጥ በራሱና በሀገር ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ሊከላከል ይገባል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment