(Jan 17, 2013,by ዳንኤል በቀለ,አዲስ አበባ)--በሀገራችን በዓላትንና የተለያዩ ድግሶችን
ለማድመቅ ጠላ ማዘጋጀት በብዙዎች ዘንድ የተለመደና የኖረ ባህል ነው፡፡ በተለይ ከሃይማኖት ጋር የተያያዙት ዋና ዋና
በዓላት፣ ሠርግ ፣ክርስትና እንዲሁም የሟቾችን መታሰቢያ ለመዘከር የሚታሰቡ ቀናት ላይ ጠላ አይጠፋም። በገጠሩ
የሀገራችን ክፍሎችም አርሶ አደሩ ምርቱን ለመሰብሰብ በሚጠራው ደቦ ላይ ሥራው የሚካሄደው « የዶሮ ዓይን» የመሰለ ጠላን ጐንጨት እየተባለ ነው።
ይህ ባህላዊ የጠላ አጠማመቅ ዘዴ ለዘመናት ሲሠራበት ኖሯል። ከጥንስሱ ጀምሮ ጠላው ለመጠጣት ዝግጁ እስኪሆን ከ15 እስከ 20 ቀን
ይፈጃል። ጥሬ ዕቃዎቹን ከገበያ ገዝቶ ማዘጋጀትና ጠላ ለመጥመቅ የሚደረገው ሂደት ጊዜ ከመፈለጉም ባሻገር ሥራው
አድካሚ ነው።
ከዘመናዊ የአኗኗር ሥርዓት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ይህን ባህላዊ መጠጥ ለማዘጋጀት ያለው ፍላጎት
እየቀነሰ ሊመጣ ይችላል። በተለይ በከተሞች የጋራ መኖሪያ ቤቶች መስፋፋት ለጠላ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ አመቺ
ባለመሆናቸው ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ግድ ይላል።
ወይዘሮ ሙሉነሽ አለነህ ለእዚህ መፍትሔ አማራጭ ይዛ ብቅ ብላለች። በ1998 ዓ.ም ከባህርዳር ኪያሜድ የጤና ኮሌጅ በነርስነት የተመረቀችው ወጣት በሙያዋ ሥራ ፈልጋ መቀጠርን እንደ አንደኛ አማራጭ አልወሰ ደችውም። ይልቁንስ ዘወትር በውስጧ የሚመላለሰውን ጠላን ዘመናዊ በመሆነ መልኩ ለማዘጋጀት የሚያስችለውን ዘዴ ለመሞከር ጥረት ማድረግ ጀመረች።
ለሃሳቡ መነሻ የሆኗት የተለያዩ ጉዳዮች
አሉ። የመጀመሪያው አብዛኛው ሰው በበዓላትና በድግስ ቀናት ጠላ ለማዘጋጀት ፍላጎት ቢኖረውም በጊዜ እጥረት የተነሳ
ያሰበውን ማድረግ አለመቻሉ ነው። ባህላዊውን መጠጥ ከቤት የማግኘት ፍላጎቱ ከፍተኛ ቢሆንም ካለው የአዘገጃጀት
ውጣውረድ የተነሳ ጠላ ከየቤቱ እየጠፋ መሄዱን ታስታ ውሳለች።
ሌላኛው ምክንያት የጋራ መኖሪያ ቤት
መስፋፋት ነው። ባለችበት አካባቢ ይህ ሁኔታ ጎልቶ ይታያል። የጋራ መኖሪያ ቤቶችና ዘመናዊ ግንባታዎች እየተስፋፉ
መጥተዋል። በእነዚህ ቤቶች ጠላ ለማዘጋጀት የሚደረገውን ባህላዊ ቅደም ተከተል መተግበር ያስቸግራል። ጌሾ ይወቀጣል፣
አሻሮ ይቆላል፣ የጠላ ቂጣ ይጋገራል። እነዚህን ለማከናወን ዘመናዊ ቤቶቹ አመቺ አይደሉም።
በዓላትን ባህላዊውን ሥርዓት አከናውኖ
ማሳለፍ የለመዱ ሰዎች የጠላ ከቤት መጥፋት ቅር ያሰኛቸዋል። ባህል የማንነት መገለጫ ነውና ተጠብቆ ሊዘልቅ ይገባል
እንጂ ሊጠፋ አይገባም የምትለው ወይዘሮ ሙሉ በአንድ ወቅት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አስመ ልክቶ በተደረገ ስብሰባ
አንድ እናት የሰነዘሩት አስተያየት ሃሳቧን እንድ ትገፋበት እንዳደረጋት ትናገራለች።
በዕለቱ ከተለያየ አካባቢ የመጡ ሰዎች ተሰብስበው ስለጋራ መኖሪያ ቤቶች ጠቀሜታ ውይይት ይደረግ ነበር። በቤቶቹ ላይ የተለያየ ጥያቄና አስተያየት ይሰነዘ ራል። አንድ እናት በሰ ጡት አስተያየት «ቤቶቹ ጠላ ለማዘጋጀት አይመ ቹም፡፡ ቡና መውቀጥም አይቻልም። ታዲያ እን ዴት ነው ጠላና ቡና ሳናዘጋጅ የምንኖረው?» የሚል ነበር።
ወይዘሮ ሙሉነሽ ይህን ሃሳብ እያውጠነጠ ነች
ጠላ በቀላሉ የሚዘ ጋጅበት ዘዴ ትፈልግ ጀመር፡፡ ከረጅም ጥረት በኋላ ለጠላ የሚያስፈ ልጉትን ግብዓቶች በሙሉ
በመቀላቀል በዱቄት መልክ የተዘጋጀ ጠላ ለማዘጋጀት ችላለች። ውህዱ ጌሾ፣ ብቅል፣ የጠላ ቂጣ እና አሻሮ የያዘ ነው።
ሁሉም ግብዓቶች ተመጣጥነው ይገኛሉ። ይህን ዱቄት በመመሪያው መሠረት የሚያስፈልገውን ውሃ ጨምሮ ከተቀመጠው ቀነ
ገደብ በኋላ የሚፈ ለገውን ጠላ ማግኘት ይቻላል።
የወይዘሮ ሙሉነሽ የፈጠራ ሥራ አዲስ አቅጣጫ የሚያመለክት ነው። ጠላን ለማዘጋጀት የሚታለፉትን ሂደቶች ያሳጥራል። ለዚህም ሥራዋ የኢትዮጵያ አዕምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በ2002 ዓ.ም የፈጠራ ባለቤትነት መብት ሰጥቷታል።
ወይዘሮ ሙሉነሽ ጠላን በእዚህ መልኩ አዘምኖ ለማዘጋጀት መነሻ የነበራት ካፒታል 500 ብር
ብቻ ነበር። የምትረዳት አንድ ሠራተኛም ነበረች። የጠላውን ዱቄት እያዘጋጀች ለሰዎች በመስጠት አስተያየታቸውን
ሰበሰበች። የምታገኘው ምላሽ አበረታች ነበር። ያገኘችው በጎ ምላሽ ስንቅ ሆኗት አነስተኛ ሱቅ በመክፈት ሽያጭ
ጀመረች።
መጀመሪያ ላይ ተጠቃሚው አነስተኛ ነበር።
አዲስ ነገር እንደመሆኑ አልተላመደም። ቀስ በቀስ አንዱ ለአንዱ እየነገረ ተጠቃሚው እየጨመረ መጣ። ብዙዎች ጥረቷን
ያደንቁና ያበረታቷት ጀመር። ከጊዜ ወደ ጊዜ ከደንበኞቿ የሚሰጣትን አስተያየት እየተቀበለችም ሥራዋን አሻሻለች።
ጠላን በእዚህ መልኩ ማዘጋጀቱ በርካታ ጠቀሜታ እንዳለው ወይዘሮ ሙሉነሽ ታምናለች። በበዓላት ወቅት ጠላ ለመጥመቅ የሚባክነውን ጊዜ ይቀንሳል። ባህል እንዳይረሳ ያደርጋል። የአልኮል መጠኑን መመጠን ይቻላል። አንድ ጊዜ ጥሩ ሌላ ጊዜ ደግሞ ያልተዋጣለት ጠላ ከመጥመቅ ያድናል።
ወይዘሮ ሙሉነሽ ጠላን በዘመናዊ መልክ
ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው። የአልኮል መጠኑን ለማስለካት ሞክራለች። በአንድ ወቅት ባህርዳር ፖሊ
ቴክኒክ በተዘጋጀ ዓውደርዕይ በባለሙያ ታይቶ አምስት በመቶ የአልኮል ይዘት እንዳለው ተረጋግጧል። አውስትራሊያ፣
አሜሪካ እና ግሪክ የመሳሰሉ አገራት የተላከው የጠላ ዱቄት ከተጠቃሚዎች ጥሩ ምላሽ አስገኝቶላታል።
የጠላ ዱቄቱ ከአንድ ኪሎ ጀምሮ በላስቲክ
ታሽጎ የተዘጋጀ ሲሆን፤ አብሮትም የአጠቃቀም መመሪያ ሰፍሯል፡፡ በቀጣይ ወደ ውጭ ለመላክ ሊሟሉ የሚገባቸውን
መስፈርቶች በማጥናትና ዝግጅት በማድረግ የውጭውን ገበያ ለመያዝ ታስባለች። ወይዘሮ ሙሉነሽ ያደረገችውን ጥረት እያዩ
የሚያበረታቷት አካላት አሉ። የክልሉ ጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ እና የሴቶች የሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ተጠቃሽ
ናቸው። የተለያዩ አውደ ርዕዮች ሲኖሩ ይጋብዟታል። በእዚህ መልኩ ባገኘችው አጋጣሚ የጀርመን ተራድኦ ድርጅት
ባዘጋጀው ውድድር ተካፍላ ሦስት ሺ ብር፤ ደሴ በተዘጋጀው ውድድርም ሁለት ሺ ብር በሽልማት አግኝታለች።
በየጊዜው የምታገኛቸው ማበረታቻዎችና የሰዎች
በጎ ምላሽ ያነሳሳት ወይዘሮ ሙሉነሽ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የሥራ ፈጠራ ተሰጥኦ ውድድር ተካፋይ ሆናለች።
ለውድድሩ የቀረቡት ተወዳዳሪዎች እንዴት አድርገው የሥራ ዕቅድ እንደሚያቀርቡ ሠልጥነዋል፡፡ በወቅቱ ነፍሰጡር
የነበረችው ወይዘሮ ሙሉነሽ በሠለጠነችው መሠረት ዕቅዷን ያዘጋጀችው የሚያብጠውን እግሯን እያስታመመች ነበር። ውስጧ
ከፍተኛ ተነሳሽነት ስለነበር በአግባቡ ያዘጋጀችው የሥራ ዕቅድ ከዳኞችም ሆነ ከተመልካቾች ጥሩ ምላሽ አስገኝቶላታል።
1 comment:
betam Tiru fetera nwu. tebareki
Post a Comment