Friday, January 18, 2013

‹‹በጀርመን ያለን ክብር በኢትዮጵያ ለሊስትሮዎች የምንሰጠውን ያህል ነው›› (ተጻፈ በ Super User)

(Jan 17, 2013, Reporter )--በየዓመቱ ገና ሲከበር አንድ ነጭ አሮጊት ወይም ሽማግሌ የተራቆተ ጥቁር ሕፃን አቅፈው እርዱን እየረዳን ነው የሚሉ ፖስተሮችን በጀርመን ማየት የተለመደ ነው፡፡

ገንዘብ ለማግኘትና ዕርዳታ ለማሰባሰብ የሚጠቀሙበት ዘዴ ኢትዮጵያውያንን በአጠቃላይም አፍሪካውያን ዳያስፖራዎችን አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ በተለይ ለኩሩው ኢትዮጵያዊ ከባድ ነው፡፡ የዕርዳታ ድርጅቶች የሚያደርጉት እገዛ ጥሩ ቢሆንም፣ ዕርዳታ ለማግኘት የሚጠቀሙበት መንገድ የዕርዳታን መጥፎ ገጽታ ያሳያል፡፡ ከቅኝ ግዛት ጀምሮ ጥቁርን የበታች አድርጎ ማየቱ ዛሬ ላይም ዕርዳታ ነክ መግባቢያዎች ላይ ይንፀባረቃል፡፡››

ይህን የሚሉት አቶ ዳዊት ሻንቆ በበርሊን ከ10 ዓመት በፊት የተቋቋመውና በየዓመቱ ኢትዮጵያ በመመላለስ የሚሠራው የሊስትሮ ፕሮጀክት መሥራችና ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ዳያስፖራው በየአገሩ ስላሉ መልካም ጐኖች የማስረዳት፣ የማግባባትና የማስማማት ሥራ ውስጥ መግባት፣ ለዚህም በመካከሉ ያሉ ልዩነቶችን ጠብቆ በሚግባባበት ትንሿ ጉዳይ ላይ አብሮ መሥራትና የተበላሸውን ገጽታ መለወጥ ይገባዋል ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ በድህነት ሸማ የተሸፈኑ እምቅ ዕውቀቶች፣ መልካም ጐኖችና ራዕዮችን በማጉላትና ግንዛቤ በመፍጠርም ላይ በሚሠራው የሊስትሮ ፕሮጀክት በጀርመንም ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግንዛቤ በማስጨበጥ ላይ እንደሚሠራ ይገልጻሉ፡፡ ለሊስትሮ ፕሮጀክት ዋና መነሻው ደግሞ በጀርመን የሚኖሩ የኢትዮጵያውያን ወይም የአፍሪካውያን ዳያስፖራዎች ሕይወት መሆኑን በጀርመን ያለን ክብር በኢትዮጵያ ለሊሰትሮዎች የምንሰጠውን ያህል ነው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ በፖሊስና በሊስትሮ መካከል ግጭት እናያለን፡፡ በጀርመንም እንዲሁም ነው፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግንዛቤ መፍጠር ሲሆን፣ የሊስትሮዎችን ሐሳብ መስማትና ማገዝም ሌላው ነው፡፡ ሊስትሮዎች ሲጠየቁ መማር፣ መሥራትና መለወጥ እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ፡፡ ይህ የኢትዮጵያም ራዕይ ነው የሚሉት አቶ ዳዊት፣ ያቋቋሙት ፕሮጀክት ብቻውን የሚወጣው ባይሆንም፣ ዳያስፖራውም ሆነ በአገር ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ ከሚሠራው ጋር ተዳምሮ መልካም አመለካከትን ማምጣት ይቻላል ይላሉ፡፡

በተለይ ዳያስፖራው ድልድይ ሆኖ መሥራትና በውጭ ያለውን የኢትዮጵያ መጥፎ ገጽታ መለወጥ ይችላል፤ አንድ የኢትዮጵያ ተወካይ ከጀርመን አቻው ጋር በሚያደርገው ውይይት ያለውን አለመግባባት በቀላሉ ይረዳል፣ በጀርመን ያለውን ባህል ያውቃል፣ አካሄዱን ለምዶታል፤ በአገሮቹ መካከል ውይይቶች ሲደረጉ ዳያስፖራው  እንዲግባቡ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላል፡፡ አቅሙም አለውም ብለዋል፡፡

የ17 ዓመት ወጣት እየሉ በካርታ ሥራዎች ድርጅት አማካይነት ለጐበዝ ተማሪዎች በተሰጠ የትምህርት ዕድል ለሄዱትና ከዛ በፊት ከአዲስ አበባ በቀር ሌላውን የኢትዮጵያ ክፍል ለማያውቁት አቶ ዳዊት በኢትዮጵያ ስላለው ድህነትና ችግር ይህንንም ያህል የጠበቀ ዕውቀት አልነበራቸውም፡፡ ይልቁንም የሚያስታውሱት ‹‹ኢትዮጵያ አገሬ ልምላሜሽ ማማሩ ፏፏቴሽ ይወርዳል በየሸንተረሩ . . . ›› የሚለውን ዘፈን ነበር፡፡ ጀርመኖች በየጊዜው ስለኢትዮጵያ የሚነግሯቸውን መጥፎ ገጽታ አላምን ያሉት አቶ ዳዊት፣ ጀርመኖቹ የሚያቀርቡላቸውን መጻሕፍት በማንበብ ‹‹ችግር አለ፣ ጦርነት ነበር፣ ራሴም ድህነት አለ ብዬ ብቀበልም በድህነት ውስጥ ጠንካራ ጐን አለ፡፡ ጥሩ ገጽታችንን ማሳየት አለብኝ፤›› ብለው መነሣታቸውን ገልጸዋል፡፡

በውጭው ዓለም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ደሃ መሆኗ እንጂ ማኅበረሰቡ ያለው ጠንካራ የመረዳዳት፣ አብሮ የመኖር ባህል እምብዛም ሲገለጽ አይስተዋልም፡፡ ኢትዮጵያዊው ከሰል እየሞቀ የሚግጠው በቆሎ ምናልባት ደሃ ሊያስመስለው ይችላል፡፡ ሆኖም ይህ ባህሉ ነው፡፡ በዛ ሰዓት ላይ የሚያወጋው ትልቅ ቁምነገር አለው፡፡ አቶ ዳዊት ይህን ማን ያውቅልናል? ለምንድን ነው ላይ ላዩ የሚታየው? ከሚል ሐሳብ በመነሳት ጀርመኖች የዕረፍት ጊዜያቸውን በኢትዮጵያ እንዲያሳልፉ ስለኢትዮጵያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ቅስቀሳ ጀምረው ነበር፡፡ ‹‹ምናልባት የዕርዳታ ማስተባበሪያ ሠራተኛ ሆኜ ካልተፈለኩ የረፍት ጊዜዬን ኢትዮጵያ አላሳልፍም፤ ልጆቼን ጥዬ ብሞትስ፣ ብገደልስ፤›› ያሏቸው እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡

የመረጃ ክፍተት እሳቸው በሚያደርጉት የገጽታ ግንባታ ላይ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ስለኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ በማሄዱ ልዑኮች ላይም ያጠላ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማስተዋወቅ ጀርመን በየዓመቱ የልዑካን ቡድን ይመጣ ነበር፡፡ እነሱ የሚያስተዋውቁትን ስዕል እንኳን አያምኑም ብለዋል፡፡

ዳያስፖራዎች አስተርጓሚ መሆን አለብን፣ ድልድይ መሆን አለብን መረጃ መስጠት አለብን፡፡ የዳያስፖራው ተሳትፎ ከትውልድ አገርም ባለፈ በዓለም ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ዳያስፖራው ተዓማኒነትም አለው፡፡ ሆኖም አልተጠቀመበትም ይላሉ፡፡

በዓለም ባንክ የተሰጠው ግምት የሚያሳየው የአፍሪካ ዳያስፖራዎች ለየትውልድ አገራቸው የሚልኩት ገንዘብ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ረጂዎችና መንግሥታት ለአፍሪካ ከሚሰጡት ዕርዳታ ስምንት እጥፍ ይበልጣል፡፡ በኢኮኖሚውም ቢሆን ትልቅ ሥፍራ ይዟል፡፡ ሆኖም ከዳያስፖራው ይልቅ ሰጪና ረጂ አገሮች በአፍሪካ ላይ የሚያደርጉት ተፅዕኖና ጫና ከባድ ነው፡፡ ዳያስፖራው ግን ከፍተኛ ገንዘብ እያፈሰሰ አብሮ መሥራት ባለመቻሉና በተለያዩ ምክንያቶች በመራቁ ልዩነት ማምጣት አልቻለም፡፡

የተለያዩ የዳያስፖራ ቡድኖች የተለያየ ፍላጐት ቢኖራቸውም አንድ የሆነውን ይዘው ልዩነታቸውን አጉልተው መሔድም አልቻሉም፡፡ በጀርመን የኢትዮጵያ ማኅበረሰብም በጣሙን የፖለቲካ አጀንዳ ውስጥ የገባ ነው፡፡ አገር ውስጥ ስላለው ፖለቲካ በሰፊው የሚያወራ ነው ይላሉ፡፡

በርሊን መኖሬ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶኛል፡፡ ትልቅ የፖለቲካ ልዩነት የነበራቸው አገሮች ሲቀላቀሉ ደም ጠብ ሳይል፣ ሰው ሳይደበደብ፣ ሁለት መኪናዎች ሳይጋጩ ልዩነታቸው በሒደት ተፈትቷል፡፡ በማለት ከወገኖቻቸው ጋር ስለኢትዮጵያ ሳይሆን ጀርመኖች እንዴት የፖለቲካ ልዩነታቸውን እንደፈቱ ሐሳብ ቢያቀርቡም ለመወያየት አልተሳካላቸውም፡፡ በሌላ በኩል ቤተሰብ ለማገዝ በአገር ኢንቨስት ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ በዚህ በኩል ምን ዓይነት ተፅዕኖ መፍጠር እንችላለን? በፖለቲካና በማኅበራዊ ውይይት ውስጥ የዳያስፖራው ሚና ምንድን ነው? የሚለው ላይ እየሠሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment