Sunday, January 01, 2012

የሆስተሷን ዓይኖች ባጠፋው ፍርደኛ ላይ የተሰጠው ቅጣት ተቃውሞ አስነሳ

(Sunday, 01 January 2012, Reporter)--‹‹ውሳኔው ጥሩ ነው ወይም አይደለም ለማለት ከደንበኛችን ጋር አልተወያየንም›› የተከሳሽ ጠበቆች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና የበረራ አስተናጋጅ (ሆስተስ) የነበረችውን አበራሽ ኃይላይን ዓይኖች ማጥፋቱ በተረጋገጠበት የቀድሞ ባለቤቷ አቶ ፍስሐ ታደሰ ላይ ታኅሣሥ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. የተወሰነው የ14 ዓመታት ፅኑ የእስራት ቅጣት ተቃውሞ አስነሳ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በጥፋተኛው ላይ ባስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ ቅሬታቸውን ያሰሙት የተጐጂዋ ቤተሰቦች፣ በኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት አሁን በዓይኔ መጣህ ፀረ ሴቶች ጥቃት ዘመቻ ቡድን፣ ክሱን የመሠረተው ዓቃቤ ሕግና ችሎቱን ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ የተከታተሉ የችሎቱ ታዳሚዎች ናቸው፡፡

ፍርድ ቤቱ ታኅሣሥ 20 ቀን 2004 ዓ.ም. የሰጠውን የ14 ዓመታት ፅኑ የእስራት ቅጣት በችሎት ተገኝተው ሲከታተሉ የነበሩ የችሎቱ ታዳሚዎች፣ ‹‹ከዚህ በኋላ የሴቶች ጥቃት አይቆምም፡፡ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ባለመሰጠቱ ከዚህ በፊት አሲድ የተደፋባት በካሚላት የተጀመረው የወንጀል ድርጊት ፈርጁን እየቀያየረ በየጊዜው እያደገ መጥቷል፡፡ አሁንስ ፈራን፡፡ መንግሥት ካልደረሰልን ማን ሊደርስልን ነው? እህት፣ እናትና ሴት ልጅ ያለው ሁሉ አጽንኦት ሰጥቶ ሊከታተለው ይገባል፤›› በማለት ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል፡፡

የሆስተስ አበራሽ አጐት አቶ አስመላሽ ሞላ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹የቅጣት ውሳኔው ሲነገር ያለሁት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው?›› በማለት ራሳቸውን መጠየቃቸው ተናግረዋል፡፡ የአበራሽ ሁለት ዓይኖች ብቻ ሳይሆን የጠፉት፣ በሥሯ ይተዳደሩ የነበሩ እህቶቿና ቤተሰብቿ ጭምር መጥፋታቸውን ገልጸው፣ የተሰጠው ውሳኔ በእሷ ላይ የደረሰውን ጉዳትና ወደፊት የሚያስተከትልባት ችግር ከግምት ያላስገባ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ዛሬ የጠፋው የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሴቶች ዓይን ነው፤›› ያሉት አጐቷ  ፍርዱን በፀጋ ቢቀበሉትም፣ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገ በልጁ፣ በሚስቱና በእህቶቹ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከወዲሁ ሊያስብበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

‹‹በስለትና በእጅ ተጐልጉሎ አሰቃቂ በሆነ መንገድ የዘለዓለም ብርሃንዋን ባሳጣ ወንጀለኛ ላይ የ14 ዓመታት እስር ብቻ እንደሚወስን አውቄ ቢሆን ኖሮ አርፌ መቀመጥ ይሻለኝ ነበር፤›› ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡

በሆስተስ አበራሽ ላይ የደረሰው ጉዳት ከዓመታት በፊት በካሚላት ላይ ከደረሰው ጉዳት እንደሚበልጥ የተናገሩት አቶ አስመላሽ፣ ቅጣቱም አንሶ መወሰኑን በማነፃፀር ገልጸዋል፡፡ በካሚላት ላይ የአሲድ ጥቃት በማድረስ የተፈረደበት ዕድሜ ልክ እስራት መሆኑን በማስታወስ፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ደረጃ የኦሪት ሕግን ተግባራዊ እንድታደርግ እንደማይጠብቁ የሚገልጹት የአበራሽ አጐት አቶ አስመላሽ፣ ወንጀለኛው ካደረሰው ጉዳት አንፃር ግን ሞትም ባይሆን በዕድሜ ልክ እስራት ይቀጣል የሚል እምነት ቢኖራቸውም ውሳኔው የተገላቢጦሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክሱን ሒደት በቅርብ ሆነው የተከታተሉና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኅን የሰሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ማንባታቸውንና አስተማሪ የሆነ ቅጣት ይጠብቁ እንደነበር የጠቆሙት አቶ አስመላሽ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚመክሩት ተመሳሳይ ድርጊት ቢፈጸምበት መክሰስ ዋጋ የሌለው መሆኑን ነው፡፡

ሆስተስ አበራሽ በሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ወጪ እስካሁን ድረስ በመታከም ላይ መሆኗን የገለጹት አጐቷ፣ ‹‹ዛሬ (ታኅሣሥ 20 ቀን 2004 ዓ.ም.) የተወሰነውን ቅጣት ብትሰማ ምን እንደሚሰማት ከወዲሁ መገመት ያዳግተኛል፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ውሳኔው በተሰጠበት ዕለት ባወጣው የተቃውሞ መግለጫ ውሳኔው በጣም እንዳሳሰበው፣ መንግሥትና ኅብረተሰቡ እኩልነትን ለማረጋገጥ ደፋ ቀና የሚሉለትን ሁሉ የሚያመክንና አስተማሪነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ውሳኔ ሆኖ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለድርጊቱ ፈጻሚ እንደ ቅጣት ማቅለያ በዋነኛነት የወሰደው ፍርደኛው የኤችአይቪ/ኤድስ ታማሚ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ያስታወሰው ቅንጅቱ፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሰዎች ለሚፈጽሙት ማንኛውም ድርጊት እንደዋና ቅጣት ማቅለያ መወሰዱ የሕጉን ፍሬ ነገር የማይጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ገልጿል፡፡ አሰቃቂና ኢ ሰብዓዊ ለሆነ የወንጀል ድርጊት የተላለፈው ውሳኔ አስተማሪና ተመጣጣኝ ባለመሆኑ፣ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉትን የሴቶች ጥቃቶችን የሚያባብስና የሕግ አካላትን ታማኝነት የሚያሳጣ መሆኑን በማብራራት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

የፍርደኛው ጠበቆች የሆኑት ጠበቃ አምሀ መኮንንና ጠበቃ ስሜነህ ተክሉ የቅጣት ውሳኔውንና አጠቃላይ የክስ ሒደቱን በሚመለከት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ጠበቆቹ እንዳሉት፣ ከውሳኔው በፊትም ይሁን ከውሳኔው በኋላ በወ/ሮ አበራሽ ላይ በደረሰው አደጋ የሚያስደነግጥ፣ የሚያሳዝንና በማንም ላይ ሊደርስ የማይገባ መሆኑ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ነገር ግን የተፈጠረው ችግር መፈታት የነበረበት በፍርድ ቤትና በፍርድ ቤት ብቻ›› ነበር ያሉት ጠበቆቹ፣ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት በመምጣቱ በሕግ የተጣለባቸውን ግዴታ በጨዋነትና በሥነ ሥርዓት ለመወጣት መሞከራቸውን ተናግረዋል፡፡ ሒደቱም ፈታኝ እንደነበርም አልደበቁም፡፡ በክስ ሒደቱ ውስጥ ብዙ ከባድ ነገሮች እንደነበሩ የገለጹት ጠበቆቹ፣ የችሎት ታዳሚዎችና በሴቶች መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ ባለሙያዎች ጭምር ፍርድ ቤት ድረስ መፈክር ይዘው ሠልፍ መውጣታቸው ጥሩ እንዳልነበር አስረድተዋል፡፡

ክርክሩ የተጀመረበትና ያለቀበት ጊዜ እጅግ ፈጣን እንደነበርና መፍጠኑም ጥሩ እንደሆነ የገለጹት ጠበቆቹ፣ የዚህ ዓይነት የፍትሕ ፍጥነት በሁሉም ጉዳዮች ላይ ቢሆን እንደሚመረጥ ተናግረዋል፡፡ በነበረው የክርክር ሒደት አንዳንድ ጊዜ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ጊዜ ያጥራቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የመከላከያ ምስክሮችን ሲያሰሙ አንዱ የመከላከያ ምስክር መስክሮ ሲወጣ ከፍርድ ቤት በራፍ ላይ ተወስዶ መታሰሩ (እስካሁንም መታሰሩንና ክስም እንደተመሠረተበት መስጠታቸውን ይናገራሉ) በጣም እንዳስገረማቸው ጠበቆቹ አስታውቀዋል፡፡

መስክሮ ሲወጣ በታሰረው የመከላከያ ምስክር ምክንያት ፍርኃት ያደረባቸው የሙያ መከላከያ ምስክሮቻቸው አንቀርብም ማለታቸውን የገለጹት ጠበቆቹ፣ ያልተሟሉላቸው የሰነድ ማስረጃዎች ስላሉ ለሚመለከተው አካል ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ቢጠይቁም፣ ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረጉ የክርክር ሒደቱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ማለፉን አልደበቁም፡፡

ደንበኛቸው በተጠቀሰበት የወንጀል አንቀጽ ጥፋተኛ መባሉን ያስታወሱት ጠበቆቹ፣ ዓቃቤ ሕግ የቀረበውን የቅጣት ማክበጃና እነሱ ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ ፍርድ ቤቱ በሕጉና በቅጣት መወሰኛ መመርያው መሠረት በሚገባ መርምሮ ውሳኔ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ ውሳኔው ጥሩ ነው ወይም ጥሩ አይደለም ለማለት ግን ከደንበኛቸው ጋር ተገናኝተው ያልተነጋገሩ በመሆናቸው፣ ጠበቆቹ የራሳቸውን አስተያየት መስጠት እንደሚያስቸግራቸው በመናገር ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ደንበኛቸው ካደረሰው ጉዳት አንፃር ለእሱ ጠበቃ በመሆናቸው የደረሰባቸው ተፅዕኖ ካለ ተጠይቀው፣ አንድ ጠበቃ አንድን ጉዳይ አሳፋሪ ነው ወይም አስነዋሪ ነው ማለት እንደማይችል፣ በጠበቆች የሥነ ምግባር ደንብ ላይ በግልጽ የተቀመጠ መሆኑን የተናገሩት ጠበቆቹ፣ በተለይ እንደዚህ ያለ ከባድ አደጋ ሲደርስ ትክክለኛ ፍትሕ ላይ የሚደረሰው፣ ተከሳሹ በሕግ ባለሙያዎች ሲደገፍ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ የቅርብ ወዳጆቻቸው ‹‹ይኼንን ጉዳይ ባትይዙት›› ከማለታቸው ውጭ ምንም የደረሰባቸው ችግር ወይም ተፅዕኖ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ እነሱ ጥብቅና ባይቆሙለትም መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ የማቆም ግዴታ እንዳለበትም ሊታወቅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በሆስተስ አበራሽ ኃይላይ ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ሁለት ክሶችን ማለትም በከባድ የሰው መግደል ሙከራና በሕግ የተከለከለን የጦር መሣርያን ይዞ መገኘት ወንጀል ክስ የመሠረተው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ላይ ቅር መሰኘቱን ገልጿል፡፡

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በጥፋተኛው ላይ የ14 ዓመታት ፅኑ እስራትና ለሦስት ዓመታት ከማንኛውም ማኅበራዊ መብቶቹ መነሳት ላይ ያለውን ቅሬታ ተከትሎ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚያስገባ አስታውቋል፡፡

በሆስተስ አበራሽ ላይ መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም. በተፈጸመው የወንጀል ድርጊት ላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተው ከ52 ቀናት በኋላ ጥቅምት 24 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ ክሱን የመሠረተው በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 27(1)፣ 539(ሀ) እና 809 ሥር የተደነገገውን መተላለፉን በመግለጽ ነበር፡፡ ዓቃቤ ሕግ አምስት የሰው፣ ሰባት የጽሑፍና አንድ የኤግዚቢት ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡ ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ሲሰጥ፣ ተከሳሽ ፍስሐ ታደሰ 11 የሰውና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ መከላከያ ምስክሮቹን አሰማ፡፡ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎችን፣ ከተከላካይ ምስክሮች ቃልና የሰነድ ማስረጃዎች ጋር፣ እንዲሁም ከሕጉ ጋር በመመርመር በተከሳሹ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ መስጠቱን በተከታታይ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከሁለቱም ወገን የቀረበውን የክርክር ሒደት መርምሮና አገናዝቦ ሲጨርስ፣ ከትናንት በስቲያ ጥፋተኛው ፍስሐ ታደሰ በ14 ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣና ቅጣቱን ሲጨርስ ለሦስት ዓመታት ማንኛቸውም ማኅበራዊ መብቶቹ እንዲሻሩ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
Source: Reporter 

1 comment:

Anonymous said...

በጣም ያሳዝናል ባገሩ የተሰደደ ህዝብ ::

Post a Comment