Friday, August 02, 2019

አገር ለገጠማት ችግር መፍትሔው መተባበር እንደሆነ ተረጋግጧል!

(31 July, (አዲስ አበባ ))--ኢትዮጵያዊያን የሚያምርባቸው ሲተባበሩ ብቻ ነው፡፡ ተባብረው በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገራቸውን ስም በክብር ሲያስጠሩ ይከበራሉ፡፡ ሰኞ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ከዳር እስከ ዳር በመነቃነቅ የችግኝ ተከላ ሲያከናውኑና በራሳቸው ያቀዱትን ክብረ ወሰን መስበራቸው ሲሰማ፣ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በዓለም ዙሪያ አስተጋብተውታል፡፡ ኢትዮጵያውያን መልካም ተግባር ለማከናወን ሲተባበሩ ምንም ነገር እንደማይበግራቸው ደግሞ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ በዚህ ትውልድም አዲስ ታሪክ ተሠርቷል፡፡

ነገር ግን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካና በመሳሰሉት ልዩነቶች ምክንያት ሲጋጩ ስማቸው ጥላሸት ተቀብቶ አገራቸውንም ቀውስ ውስጥ ይከታሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በኅብረ ብሔራዊነት አጊጠው በመተባበር ታላላቅ ተግባራትን ማከናወን እየቻሉ፣ እርስ በርስ በከንቱ ሲጋጩና ሲጋደሉ ከፍተኛ ሰቆቃ ይፈጠራል፡፡ በጠባብ ብሔርተኝነት ሕዝብን በመከፋፈል እርስ በርሱ ማፋጀት፣ የገዛ ወገንን ማፈናቀልና አገር ለማፍረስ ፖለቲካውን ማጦዝ ለኢትዮጵያ አይበጅም፡፡ ልዩነትን አክብሮ ለአገር ዕድገት አንድ ላይ መሠለፍ ግን ለመጪው ትውልድ ቅርስ ለማቆየት ይጠቅማል፡፡ ኢትዮጵያ ለገጠማት ወቅታዊ ችግር መፍትሔው መተባበር ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ተባብሮ አንድ ላይ መቆም ካልተቻለ ግን ውጤቱ ተያይዞ መጥፋት ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድ ቀን ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኞች የመትከላችን ዜና በመላው ዓለም ሲስተጋባ፣ ከራሳችን አልፈን ለዓለም የአየር ንብረት ጥበቃ ጭምር አስተዋጽኦ ማድረጋችን ግንዛቤ ይፈጠራል፡፡ በሙቀትና በአየር ብክለት እየተሰቃየች ላለችው ዓለም ያበረከትነው ፀጋ ጭምር ሆኖ ይቆጠራል፡፡

በአንድነት ሆነን ለጋራ ዕድገት የሚበጅ ተግባር ላይ ስንታይ ጎረቤቶቻችን ከሥጋት ነፃ ሆነው ለትብብር እጃቸውን ይዘረጋሉ፡፡ ይህ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አገርን አረንጓዴ ከማልበስ በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል የተዘራውን የክፋትና የተንኮል ሴራ የሚበጣጥስና ለአገር በአንድነት መቆምን ማመላከቻ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የልጆቿ ትብብር እንጂ እርስ በርስ መተናነቅ እንዳልሆነም ማሳያ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ሐሜት፣ አሉባልታ፣ መጠራጠርና መጠላላት ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ጥፋት እንጂ ልማት አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሲተማመኑ ይተባበራሉ፡፡ ሲተባበሩ ደግሞ ተስፋ ይኖራል፡፡ ተስፋ ያለው ሕዝብ ደግሞ ያሰበውን ዓላማ ያሳካል፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ይኼ ነው፡፡

ለዘመናት አገራቸውን ከወራሪዎችና ከተስፋፊዎች በከፍተኛ ወኔና ጀግንነት ሲከላከሉ የኖሩት ኢትዮጵያውያን፣ ከልዩነቶቻቸው በላይ የጋራ የሆነችው ኢትዮጵያ ትበልጥባቸው እንደነበረ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ አብረውም ዘመናትን ሲሸጋገሩ የኖሩት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር የገነቡዋቸው የጋራ እሴቶች ስለነበሯቸው ነው፡፡ በልዩነቶች ውስጥ ሆነው ተጋብተውና ተዋልደው አገራቸውን ለትውልዶች እያስረከቡ የቀጠሉት፣ ከምንም ነገር በላይ አገራቸውን ስለሚወዱ ነበር፡፡ ከበርካታ አኩሪ ተግባሮቻቸው መካከል ታላቁ የዓድዋ ጦርነት ድል የመላ ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲል ነው፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝም መሠረት የሆነው ታላቁ የዓድዋ ድል የተገኘው፣ በወቅቱ ገናና በነበረ የአውሮፓ ኮሎኒያሊስት ኃይል ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

አውሮፓውያን በኃፍረት አንገታቸውን ሲደፉ ኢትዮጵያ ደግሞ የራሷን ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ዙሪያ በጭቆና ሥር የነበሩ መከረኞችን አንገት ቀና አድርጋለች፡፡ ይህ ኢትዮጵያዊያን ከዳር እስከ ዳር በጀግንነት የተሠለፉበት ታላቅ ድል የተገኘው ግን በመተባበር ብቻ ነው፡፡ ዛሬም ተባብሮ በመነሳት በዓለም ፊት ሞገስ የሚያስገኝ ታላቅ ድል በዚህ ትውልድ ሲታይ፣ ከመተባበር በላይ ምንም ጠቃሚ ነገር እንደሌለ ያረጋግጣል፡፡

ኢትዮጵያውያን ካሁን በኋላ ለግጭትና ለእርስ በርስ ጥላቻ የሚዳርጉ አጉል ድርጊቶችን መታገስ የለባቸውም፡፡ በዓለም ፊት ኃፍረት ውስጥ የሚከቱ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ ዘረፋዎችና የንብረት ውድመቶች አያስፈልጉንም ማለት አለባቸው፡፡ የገዛ ወገንን በአገር ውስጥ በማፈናቀል በጦርነት ከወደሙት ሶሪያና የመን በላይ በመሆን በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ መፈረጇ፣ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያዊያንን እንደ እግር እሳት ማንገብገብ አለበት፡፡

ስንትና ስንት ገድሎችን መፈጸም የሚችሉ ኩሩና አስተዋይ ኢትዮጵያውያን እያሉ፣ ለአገር ምንም ደንታ የሌላቸው ትርምስ እንዲፈጥሩ ዕድል መሰጠት የለበትም፡፡ ይልቁንም ለኢትዮጵያ የሚበጅ ሐሳብ ከየትም ይምጣ በነፃነት እንዲደመጥ መታገል ተገቢ ነው፡፡ ከጉልበተኝነት ይልቅ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መነጋገር፣ መከራከርና መደራደር መለመድ አለበት፡፡ በማኅበረሰቦች ውስጥ መተማመን እንዲኖር የውይይት ባህል ሊዳብር ይገባል፡፡ ጠባብ ብሔርተኞች አገር የሚያጠፉት የውይይት ባህልና መተማመን እንዳይኖር በማድረግ ነው፡፡ ለአገር ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ማምጣት የሚቻለው በመተባበር ስለሆነ ለሥልጡን ውይይት መዳበር መታገል ይገባል፡፡

በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ስም ያስጠራው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከፍተኛ ክትትል ይፈልጋል፡፡ የተተከሉ ችግኞች ፀድቀው መብቀል አለባቸው፡፡ ለተከላ የወጡት ኢትዮጵያዊያን እየተንከባከቡ አርዓያነት ያለው ተግባር መፈጸም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን በስኬት ማከናወን ሲቻል የዓለምን አድናቆት የበለጠ ያስገኛል፡፡ ችግኞቹን ተክሎ ተንከባክቦ ለማሳደግ ደግሞ ከአላስፈላጊ ድርጊቶች መቆጠብ የግድ ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ አገርን አረንጓዴ ማልበስ፣ ሕዝብን ከድህነትና ከኋላቀርነት ማላቀቅ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገባትን ሥፍራ ማስያዝና ለመጪው ትውልድ የምትመች አገር መፍጠር ይገባል፡፡ አገርን በብሔር በመከፋፈል ሕዝብን የምትገድሉ፣ የምታፈናቅሉ፣ የምትዘርፉና የምታወድሙ ከድርጊታችሁ ታቀቡ፡፡

ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና አድርጋ በኩራት መራመድ የምትችለው ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ብልፅግና፣ ፍትሕና እኩልነት ሲሰፍኑ ብቻ ነው፡፡ በሕግ የበላይነት የምትተዳደር አገር በአስተማማኝ ሁኔታ እንድትፈጠር ከግጭትና ከውድመት አስተሳሰብ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ቆርጠው ከተነሱና ከተባበሩ ምንም ነገር ማከናወን እንደማይሳናቸው በተግባር አሳይተዋል፡፡ ከውድመት ውስጥ ወጥቶ ወደ ዕድገት ጎዳና መሸጋገር አያቅትም፡፡ ኢትዮጵያ ለገጠማት ችግር ብቸኛው መፍትሔ መተባበር መሆኑ መረጋገጡን መተማመን ያስፈልጋል!
ሪፖርተር, አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment