(27 Jun, (አዲስ አበባ))-- ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳርና በአዲስ አበባ በአማራ ክልል ባለሥልጣናትና በአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ላይ በተፈጸመው ግድያ የተሰማንን ሐዘን እየገለጽን፣ ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን እንመኛለን፡፡ ይህ ዓይነቱ መራርና አሳዛኝ ድርጊት ዳግም እንዳይፈጸም መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡ በቀጥታም ሆነ በሥውር የሚፈጸሙ ደባዎችን ማስቆም የሚቻለው መነጋገር ሲቻል ብቻ ነው፡፡
የደረሰው አደጋ አስደንጋጭና አሰቃቂ በመሆኑም፣ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን እናነሳለን፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው ለውጥ የዴሞክራሲ ምልክትና ጅማሮ ይዞ ቢመጣም የጠላትነት ፖለቲካን፣ ቁርሾንና ኩርፊያን እያፈራረሰ ዕርቅንና የፖለቲካ መግባባትን ለማበራከት አለመቻሉና ከአደጋ አለመገላገላችን እያደረ እያሠጋንና እያስደነገጠን ነው፡፡ አሁንም በለውጥ ተቀናቃኞችም ሆነ ደጋፊዎች ዘንድ ያልተገላገልነው አሻጥርና የሴራ አደጋ አለ፡፡
በለውጥ ፈላጊው ውስጥም ከተቀናቃኙ ኃይል የባሰ የኢዴሞክራሲያዊነትና የፀረ ዴሞክራሲያዊነት ፍላጎቶችና ፀባዮች፣ ለውጡ እሳት ላይ መቆሙን እያሳዩ ነው፡፡ አደገኛ ገደል ውስጥ ለመውደቅ እንደምንንደረደር ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ነው፡፡ የሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. አደጋ የእነዚህ ማስጠንቀቂያ ድምፅ ነው፡፡ ይህ ድምፅ ካላስደነገጠን ደግሞ ከፊታችን አሳር ይጠብቀናል፡፡
በዚህ መነሻ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን ማንሳት ይጠቅማል፡፡ የመጀመርያው ሰላማዊና ሕጋዊ ትግልን ብቸኛው የጨዋታ ሕግ አለማድረጋችን፣ ሁለተኛው በዴሞክራሲ ላይ የጋራ መግባባት አለመያዛችን፣ ሦስተኛው የታጠቀ ኃይልን ከፖለቲከኝነት ማፅዳት አለመቻላችንና በዚህም ላይ ንቁ ዓይን ማጣታችን ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአገር ተጨባጭ ሁኔታ በግለሰብ ደረጃም ሆነ በድርጅት ከሰላማዊ ትግል ውጪ የሚያዋጣ የለም፡፡ በተለይ በድርጅት አማካይነት የሕዝብ ተቀባይነትንና ታግሎ ውጤት የማግኘት አቅምን በማጎልበት፣ በሕግ የተደነገጉና መተማመኛ የተሰጠባቸው መብቶችና ነፃነቶች አይገሰሱ፣ አይረገጡ፣ ሕገወጥነትና አጥፊነት ያስጠይቁ ከማለት የሚቀድምና የሚያዋጣ ትግል የለም፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መንግሥትን በኃይል የመጣልና የመተካት ታሪክን የሚያስቆም በመሆኑ፣ ሕገ መንግሥታዊነትንና የምርጫ ሥርዓትን ሁሉም የእኔ ብሎ እንዲቀበለው ማድረግ የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጥቅም ብቻ መሆን የለበትም፡፡ እየተገነባ ነው በሚባለው ሥርዓት ውስጥ በምርጫ እንጂ በጉልበት አትጣሉን ማለትም ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መጠቀሚያ ቢመስልም፣ ሁሉም ወገን የሚቀበለው መነሻ መሆን አለበት፡፡
ጥያቄው ሕገ መንግሥቱን የመቀበልና ያለ መቀበል ሳይሆን፣ የተቀበለውም ሆነ ያልተቀበለው ፍላጎቱን ይዞ ለመታገልና ለመወዳደር ያስችላል ብሎ የሚያምንበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ የመኖርና ያለ መኖር ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጮችን አመዛዝኖ መወሰን መቻሉን መቀበልና ለፍላጎቱ ዝግጁ ለመሆን ከውይይት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ አለ ከተባለም አያዋጣም፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ውስጥ በአንፃራዊነት አቋምን በሰላም ለማራመድ አስቻይ ሁኔታ አለ፣ የአሸባሪነት ፍረጃ ተነስቶ የተሰደዱ ተመልሰዋል፣ በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ ተፈተዋል፣ በተቃውሞው ጎራ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያገኙ አሉ፣ ነባርና አዲስ ገብ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚርመሰመሱበት ሜዳ አለ፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለሕገወጥና ለአውዳሚ ሥልጣን የሚደረግ ፍጅትን ለመከላከል ዘብ መቆም፣ የሁሉም ወገኖች ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአምባገነንነትና ከትርምስ መላቀቅ ይፈልጋል፡፡ ይህ የሕዝብ ፍላጎት ከዚህም በላይ ሄዶ ዴሞክራሲን ይሻል፡፡ ዴሞክራሲያዊነትን ለመለማመድም ሆነ ለማረጋገጥ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከማጣጣም በላይ መሠረት ለማስያዝ መረባረብ የግድ ይሆናል፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙም በሰላማዊና በሕጋዊ መንገዶች ለመፍታትና ውጤታቸውን በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ መሆን ይገባል፡፡
ዴሞክራሲ መብቶች በመሉ ተከብረው ሥራ ላይ የሚውሉበት የሕዝብ አስተዳደር መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ዴሞክራሲን የመገንባት አጋጣሚ ሲገኝ በዕርጋታ፣ በትዕግሥትና በአርቆ አሳቢነት መነጋገር ሲገባ የመተባበር ዕይታና ጥረት ለምን ይጠፋብናል? በሰከነ መንገድ ተነጋግሮ ለችግሮች ሰላማዊ መፍትሔ ማመንጨት መለማመድ ሲቻል ግድያ ውስጥ ለምን እንገባለን? በግልጽ ተነጋግረን በሕዝብ መዳኘት ሲገባን አንዳችን ሌላውን ለምን እናጠፋለን? በዚህ ሁኔታስ የዘመናት የተከማቸ ችግራችን ማቆሚያው የት ነው? ወጣቱን ትውልድስ ምን እያስተማርነው ነው? አገሪቱንስ ወዴት እየወሰድናት ነው? አገርን ከድጡ ወደ ማጡ ከመክተት በስክነትና በጨዋነት መነጋገር ይበጃል፡፡ ጤናማ ያልሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡
የታጠቀ ኃይል ፖለቲከኛ መሆኑ የአገር ፈተና ነው፡፡ በሕግ ረገድ በፌዴራልና በክልሎች መካከል ያለው ግንኙነትና ልዩነት ዝም ብሎ የተተወ ይመስላል፡፡ የአቅም ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ክልሎች እርስ በርሳቸውና ከፌዴራል መንግሥት ጋር ‹‹የመሣሪያ እሽቅድምድምና የሠራዊት ክምችት›› ውስጥ ቢገቡ የሚከለክላቸው ያለ አይመስልም፡፡
ነገሩ የአሜሪካንና የሩሲያን የልዕለ ኃያልነት ፉክክር ያስታውሳል፡፡ ‹ፌዴራል መንግሥት ለክልሎች ድጋፍ የሚመድበው በጀት ሚሊሻ እንዲቀልቡበት አይደለም› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በደሴ ከተማ ያደረጉትንም ንግግር እንዲሁ ያስታውሷል፡፡ ‹ሚሊሻ› የሚባለው የታጠቀ ኃይል በሕግ ካለመታወቁም በላይ፣ የ‹‹ልዩ ኃይል ወይም ልዩ ፖሊስ›› ምንነትና ዳር ድንበር በሕግ የተወሰነ አይደለም፡፡
መንግሥታዊ አውታራትን ከገዥው ፓርቲ መለየት እስኪሳን ድረስ ተንሰራፍቶ የኖረውን የአንድ ፓርቲ አገዛዝ፣ ዛሬም ከለውጡ በኋላ በአፍ ከሚነገረው በላይ የፓርቲና የመንግሥት ተግባራትን መቀላቀል ነውር ማድረግ አልተቻለም፡፡ የታጠቀ ኃይል ፖለቲከኛና ብሔርተኛ ከተደረገ የሕዝብ ደኅንነት ጥበቃን በብሔርና በክልል መሸንሸን ድረስ እንደሚወረድ፣ በማንነት ሰላማዊ ሠልፎችና በሶማሌ ክልል በገፍ መፈናቀል ወቅት ታይቷል፡፡ ዝርዝሩ ለጊዜው ግልጽ ባይሆንም የሰሞኑ ግድያ ይህንን ጥርጣሬ ያጠናክራል፡፡
ገለልተኛ ተቋማትን የማነፅ ተግባር የለውጡ ዓላማ መሆኑ ቢነገርምና ማሻሻያዎች እየተደረጉ ቢሆንም፣ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የፀጥታ ኃይሎችንና የዓቃቤ ሕግ ተቋማትን ለፓርቲም ሆነ ለብሔርተኝነት የማይበገሩና የሁሉም የጋራ አለኝታ ተደርገው ለመታየት የሚበቁበትን መሠረት መጀመር አልተቻለም፡፡ መንግሥት ራሱ ሰብዓዊ ክብርንና መብቶችን የሚጠብቅ ለመሆን፣ ከፖለቲካና ከብሔርተኛ ወገንተኝነት ገለልተኛ ሆኖ ለመታነፅ ገና ብዙ መንገድ ይቀረዋል፡፡ ለዚህም ተግባር ከባድ ሥራ ከፊታችን ተደቅኗል፡፡ ያውም በርካታ ውስብስብ ችግሮች ተደንቅረው ማለት ነው፡፡
በአሁኗ ኢትዮጵያ የጠላትነት ፖለቲካን ማፍረስና ለየትኛውም ቡድን ሳይወግን የሚያገለግል የመንግሥት አውታር የመገንባት ሥራ ውስጥ ቢገባ እንኳን፣ ኃላፊነትን የማክበር ጨዋነት ፖለቲካዊ ዝንባሌንበልጦ እስኪጠናከር ድረስ የመከላከያ፣ የደኅንነት፣ የፖሊስ፣ የዓቃቤ ሕግና የዳኝነት ሰዎችን ከፓርቲ አባልነት ከመከልከል ባለፈ ከየትኛውም የፖለቲካ ተሳትፎ የተገለሉ እንዲሆኑና ከፖለቲካዊ አመለካከት ነፃ ለመሆን እንዲጣጣሩ ማሳመን፣ መንግሥትን የሚመሩ ወገኖች ኃላፊነትም ግዴታም መሆን አለበት፡፡
እነዚህ ተቋማት ለፍላጎቶቻቸውና ለዓላማዎቻቸው ዓርማ አበጅተውና የፖለቲካ ቀለም ተቀብተው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀፅላ ሲሆኑና በእነሱ ሲሽከረከሩ፣ የባህር ዳርና የአዲስ አበባ አደጋዎች አዲስ ማስጠንቀቂያ ይሆናሉ፡፡
እነዚህ ተቋማት ገለልተኛ ይሁኑ ማለት ቁልፍ ጥያቄ የሚሆነው ነፃነትና ፍትሕ፣ መብትና እኩልነት ለዘፈቀደ ጉልበተኛ ሳይንበረከኩ፣ እንዲሁም መንግሥታዊ ግልበጣም ይባል ጥቃት ሳያቃዣቸው ሊኖሩ የሚችሉት በገለልተኝነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲገነባ ነው፡፡ የመንግሥት አውታራት ከሕዝብ በቀር ለማንም ቡድን ብቸኛ መጠቀሚያ የማይሆኑበት ባህሪ እስኪጎናፀፉ ድረስ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ገለልተኝነትን መላበስም እንዲሁ፡፡
ጥያቄው ግን ብዙ ጊዜ መውሰዱ ሳይሆን ይህንን ረዥም ጉዞ ዛሬ ጀምረነዋል ወይ? የተከሰተው አደጋና የሚያስከትለው ጦስ አስደንግጦናል ወይ? የሚለው ነው፡፡ የማስጠንቀቂያ ድምፁም ጭምር ማለት ነው!
ሪፖርተር ርዕሰ አንቀጽ

No comments:
Post a Comment