Sunday, June 30, 2019

አብን አመራሩን ጨምሮ ከ350 በላይ አባላቱና ደጋፊዎቹ መታሰራቸውን አስታወቀ

(30 Jun, (ክሪፖርተር))--የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉን ጨምሮ፣ ከ350 በላይ አባሎቹና ደጋፊዎቹ መታሰራቸውንና እየታሰሩም መሆኑን አስታወቀ፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ክርስቲያን ታደለ ዓርብ ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ሰከላ ወረዳ ውስጥ ታስረዋል፡፡ የታሰሩበትንም ምክንያት ለጊዜው ባያውቁም፣ በወረዳው ፖሊስ ታስረው የሚገኙ ሁለት የአብን አባላትን ለመጠየቅ በሄዱበት ወቅት ሌሎች ሁለት የምክር ቤት አባላትም አብረዋቸው መታሰራቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ክርስቲያንን በሚመለከት ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንና ይፈቷቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸው፣ (ኅትመት እስከገባንበት ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት ድረስ አልተፈቱም) ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ የአብን አባላትና አመራሮች በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝና በአማራ ክልሎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ እየታሰሩ እንደሚገኙ ደሳለኝ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ከአብን ምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ክርስቲያን፣ አቶ በላይነህ ጌታቸው፣ አቶ አንማውና አቶ ገዛኸኝ የሚባሉ አባላት እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡ አባላቱ ለምን እንደሚታሰሩና ፍርድ ቤት ስለመቅረባቸው ተጠይቀው፣ ከተወሰኑት በስተቀር ፍርድ ቤት የቀረበ እንደሌለ (እስከ ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ) ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚገምቱት ምክንያቱ ሰሞኑን በአማራ ክልል ባለሥልጣናት ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ በአማራ ብሔርተኝነት ላይ የተቃጣ መሆኑንና በአብን ላይም እየተደረገ ያለው አፈና ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የታሰሩትን 26 አባላት ጨምሮ፣ በአጠቃላይ 350 አባላትና ደጋፊዎች መታሰራቸውንና እየታሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የታሰሩትን የአብን አባላትና ደጋፊዎች ለምን እንደታሰሩ ሲጠይቋቸው የአብን ደጋፊ በመሆናቸው፣ አብን ደግሞ አሸባሪ ድርጅት በመሆኑና በሽብር ተግባር ወንጀል በመጠርጠራቸው መሆኑን እንደገለጹላቸው ደሳለኝ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከአብን ምክር ቤት አባላትና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት አባላት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን፣ ወደፊት ስለሚወስዷቸው ሕጋዊ ዕርምጃዎችና የትግል አቅጣጫዎች በቅርቡ እንደሚያሳውቁም አስረድተዋል፡፡

በተጠቀሱት ክልሎች ታስረዋል ስለተባሉት የአብን ደጋፊዎችና አባላትን በሚመለከት ማብራሪያ ለማግኘት ሪፖርተር በስልክ ያገኛቸው የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽነር አበራ አዳሙ፣ በክልሉ ሰሞኑን በተፈጠረው ችግር ምክንያት ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ምላሹ ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጸው፣ ሰሞኑን ማብራሪያ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉምዝና የኦሮሚያ ክልል ኃላፊዎችን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ 
ክሪፖርተር

No comments:

Post a Comment