Saturday, December 15, 2018

ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

(Dec 15, (Addis Ababa))--የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ከዚህ ዓለም ዛሬ ታኅሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ሌሊት 11 ሰዓት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ ለሁለት ዙር ኢትዮጵያን በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ ሲሆን፣ የፕሬዚዳንትነት የሥራ ዘመናቸውን እንዳጠናቀቁ በቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ መተካታቸው ይታወሳል፡፡



ፕሬዚዳንት ሙላቱ ከወራት በፊት በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን በመልቀቃቸው በፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ተተክተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ግርማ ከፕሬዚዳንትነታቸው በኋላ በተለያዩ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ በግንባር ቀደምትነት ሲሳተፉ የነበሩ ሲሆን፣ አረንጓዴ ልማት ዋነኛ ትኩረታቸውም ነበር፡፡

ታኅሳስ 19 ቀን 1917 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተወለዱት ፕሬዚዳንት ግርማ ዘመናዊ ትምህርታቸውን እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ የተከታተሉ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት በሲቪል ማኅበራትና የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪነት ሥልጠናዎችን ወስደዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ግርማ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በኢትዮጵያውያን እንዲመራ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው ሲሆን፣ በሚዲያና በተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶች ላይ በበርካታ ሥፍራዎች አገልግለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ግርማ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment