Sunday, December 30, 2018

አገር በፕሮፓጋንዳ አትፈርስም!

(Dec 30, (ሪፓርተር))-- የአገር ጉዳይ ሲባል የተወሰኑ ቡድኖች ወይም ስብስቦች ሳይሆን፣ የመላው ሕዝብ ጉዳይ ማለት ነው፡፡ ማንም በተደሰተና በከፋው ጊዜ እየተነሳ አገርን መገንባት ወይም ማፍረስ አይችልም፡፡ አገር የመላው ሕዝብ አንጡራ ሀብት ናት የሚባለው፣ የሁሉም ነገር ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ በመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ በታሪኩ የሚታወቀው፣ አገሩን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች ሲጠብቅና ደሙን አፍስሶ የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍልላት ነው፡፡ ለዚህ ምስክር መቁጠር ሳያስፈልግ ታሪክ የከተባቸውን ድርሳናት ማገላበጥ በቂ ነው፡፡

አቶ እከሌ ወይም ወይዘሮ እከሊት በተደሰቱና ባኮረፉ ቁጥር፣ የኢትዮጵያን ዕጣ ፋንታ መወሰን አይቻላቸውም፡፡ አገር ረቂቅ በሆኑ ማኅበራዊ መስተጋብሮችና የጋራ እሴቶች ላይ የተገነባች መሆኗን እየዘነጉ፣ ነጋ ጠባ ስለመፍረስና ስለመበተን ማላዘን ደካማነት ነው፡፡ ይልቁንም ከጎጥና ከጎራ አስተሳሰብ በመላቀቅ፣ ኢትዮጵያ እንዴት ትልቅ አገር መሆን እንደምትችል መላ ማለት ያስከብራል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን በማስተባበር የአካባቢውን ሰላም በማስከበር ብሔራዊ ደኅንነቷንና ጥቅሟን ለማረጋገጥ መትጋት እየተቻለ፣ በረባ ባልረባው ሰላሟን እያናጉ ቀውስ መፍጠር ለዘመኑ አይመጥንም፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚያምርባቸው ተባብረው አገር ሲገነቡ እንጂ፣ አገር ለማፍረስ ሲያሟርቱ አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ግብዝነት ፋይዳ ቢስ ነው፡፡

እርግጥ ነው የአሁኗን ኢትዮጵያ በጥንቃቄ ለሚያስተውል ሰው የተደበላለቁ ስሜቶች ይፈጠሩበታል፡፡ በአንድ በኩል ከፍተኛ ተስፋ የሚያሰንቁ በርካታ ጅምሮችን ሲያዩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሥጋቶች አሉ፡፡ እነዚህ የተደበላለቁ ስሜቶች ገፊ ምክንያቶች አሉዋቸው፡፡ ተስፋን በሚመለከት ሕዝቡ ወደ አምባገነናዊ ሥርዓት ላለመመለስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዱ ዕርምጃዎችን ከልቡ መደገፉ አንደኛው ነው፡፡ በሕዝብ ላይ ለዘመናት ሲያናጥር የኖረው ድህነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ የሚረዱ አዋጭ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲነደፉለት የጋለ ፍላጎት ማሳየቱ ሌላው ጠቋሚ ነው፡፡ በተጨማሪም ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የምታስተናግድ አገር እንድትኖረውና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በተደጋጋሚ መሻቱ ተጠቃሽ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ኃላፊነትን መወጣት ከተቻለ የዘመናት ቁስሎች ሽረው የምታስጎመጅ አገር መፍጠር አይከብድም፡፡ በሌላ በኩል እንደ ሥጋት የሚጠቀሱት ሥርዓተ አልበኝነትን ማበረታታት፣ ልዩነትን በማጦዝ የጋራ ጉዳዮችን ማደፋፋት፣ ከመጠን ባለፈ ራስ ወዳድነትና የሥልጣን ጥም በመስከር ሕዝብና አገርን መናቅ፣ የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች ለተወሰነ ጊዜ ቀውስ ቢፈጥሩም፣ በአገር ወዳድና በቅን ዜጎች ከፍተኛ ጥረት አይሳካላቸውም፡፡ አገር ሁሌም የሚጠብቋት ጀግኖች ልጆች ይኖሯታልና፡፡ ስለዚህ ስለመፍረስና መበተን ማውራት ተገቢ አይሆንም፡፡

እዚህ ላይ መሳሳት አያስፈልግም፡፡ በለውጥ ጊዜ የተለያዩ መሰናክሎች ማጋጠማቸው የማይቀር ክሰተት ነው፡፡ ለውጡ ጥቅማቸውን የሚያሳጣቸው ወገኖች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አገርን የሚፈታተኑ ሲሆን፣ ለዚህም እንደ መሣሪያ የሚጠቀሙባቸውን ይመለምላሉ፡፡ እነዚህ ተልዕኮ ተቀባዮች ደግሞ የሚያገኙትን ትርፍ ብቻ በማሥላት ይሰማራሉ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚታየው ሰላምና መረጋጋት እያደፈረሱ ንፁኃን ይገድላሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ያፈናቅላሉ፡፡ ሰላምና መረጋጋት ከቀን ወደ ቀን እየጠፋ ሲሄድ በሕዝብ ዘንድ ሥጋት ይፈጠራል፡፡ ይህንን አጋጣሚ የሚጠቀሙበት ደግሞ ዘወትር የመፍረስና የመበተን ፕሮፓጋንዳ እየነዙ፣ በየቦታው ሁከት እንዲበራከት በእሳት ላይ ቤንዚን ያርከፈክፋሉ፡፡

ከዚህም አልፈው ተርፈው የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ አገሪቱን ቀውስ ውስጥ በመክተት፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን እምነት ይሸረሽራሉ፡፡ በገበያ ውስጥ የምርት እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ፣ ስትራቴጂካዊ ምርት የሆነውን ነዳጅ ሳይቀር በኮንትሮባንድ በማሸሽ፣ የመገበያያ ገንዘብ በመደበቅና ወደ ውጭ ምንዛሪ በመቀየር ከንግድ እንቅስቃሴ በመሰወርና በመሳሰሉት ሕዝባዊ ቁጣ እንዲነሳ የቻሉትን ሁሉ ይሞክራሉ፡፡ ሕዝብና መንግሥት መናበብ ከቻሉና አገር ወዳድ ዜጎች በድፍረት ማጋለጥ ከቻሉ ግን ሴራዎችን ማምከን አያቅትም፡፡

የአገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኢትዮጵያውያን ከስሜታዊነት ይልቅ፣ ለምክንያታዊነት ትኩረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደ ዋዛ ያመለጠ መልካም አጋጣሚ ተመልሶ የመገኘቱ ዕድል እጅግ በጣም የመነመነ በመሆኑ፣ የአገር የጋራ ጉዳይን በምክንያታዊነት ላይ በተመሠረተ ኃላፊነት መወጣት ይገባል፡፡ ፖለቲከኞች ከሥልጣን በላይ ሕዝብና አገርን ካላስቀደሙ፣ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች አገርን ከቡድን ፍላጎት በታች ካሳነሱ ራሳቸውን መመርመር አለባቸው፡፡ ሥልጣን የሚገኘው ከጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን ከዴሞክራሲያዊ ምርጫ መሆኑን የሚገነዘብ ማንኛውም ጤነኛ ሰው፣ በሕዝብና በአገር ላይ የሚቆምሩ ቁማርተኞችን በይሉኝታ ማለፍ የለበትም፡፡

የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ መሆኑ በሚገባ መታወቅ አለበት፡፡ ሕዝብን ወደ ጎን ገፍትረው የሚወዳት አገሩን እንደ ብድር ማስያዣ ዕቃ የሚደራደሩባት ፖለቲከኞችም ሆነ አክቲቪስት ተብዬዎች፣ ከዚህ በኋላ አርፋችሁ ተቀመጡ መባል አለባቸው፡፡ አገር በማንም ፈቃድ ተሠርታ የምትፈርስ የእጅ ሥራ አይደለችም፡፡ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ዘመናትን የተሻገረች መሆኗን መዘንጋት ደግሞ ተላላነት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ታሪካዊት አገር ናት፡፡ ሕዝቡም ይህችን ታሪካዊት አገር በደሙ በመጠበቅ ታሪክ የሠራ ነው፡፡ ወደ ፊትም ይቀጥላል፡፡ አንድ መረሳት የሌለበት ነገር ይህ ታታሪ፣ አስተዋይና ጨዋ ሕዝብ በአገሩ ህልውና እንደማይደራደር ነው፡፡ በብሔረሰባዊም ሆነ በኅብረ ብሔራዊ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ተወዳዳሪም ሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አባሎቻቸው፣ ይህንን ታላቅ ሕዝብ ሊያከብሩ የግድ ይላል፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን ሕዝብ ዘንድ ቀርበው መወዳደር የሚችሉት፣ ሕዝብ አክብረው በጨዋታ ሕጉ መሠረት ብቻ ሲንቀሳቀሱ ነው፡፡

ከዚህ ውጪ አገሩን እያመሱ ሕገወጥነትን ለማንገሥ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ግን፣ ይህ ጀግና ሕዝብ ፈጽሞ አይታገሳቸውም፡፡ በሌላ በኩል አገር ትፈርሳለች ብለው የሚያስቡም ሆኑ ለማፍረስ የሚሯሯጡ ህልማቸው እንደማይሳካ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት በትውልዶች ቅብብል እዚህ የደረሰችው፣ ከአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶች ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቃ መሆኗን መዘንጋት አይቻልም፡፡ የታሪክ ድርሳናት ከዶጋሊ እስከ ዓድዋ የነበሩ ትንቅንቆችን በስፋት ተርከዋቸዋል፡፡

ከፋሽስት ኢጣሊያ ጋር የተደረገው የአርበኝነት ትግል በማንም መፋቅ የማይችል ታሪክ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ታሪካዊት አገር በመሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ በጀግኖች ለልጆቿ መስዋዕትነት የምትጠበቅ በመሆኗ በማንም ፕሮፓጋንዳ አትፈርስም!
በጋዜጣዉ ሪፓርተር

No comments:

Post a Comment