Saturday, December 15, 2018

ከነትጥቃቸው ቤተ መንግሥት ከገቡ ኮማንዶዎች 66ቱ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ተፈረደባቸው

(Dec 14, (Addus Ababa))--ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ለማግኘትና ጥያቄዎችን ለመጠየቅ በሚል ምክንያት ከነትጥቃቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ገብተው ከነበሩ 216 የመከላከያ ሠራዊት መካከል 66ቱ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ፍርድ እንደተሰጣቸው ተገለጸ፡፡



ሐሙስ ታኅሳስ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊት ሪፎርምና አገራዊ ሰላምና ፀጥታን በማስመልከት መግለጫ የሰጡ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች እንደገለጹት፣ የሠራዊቱ አባላት ሆነው ቤተ መንግሥት ከነትጥቃቸው መግባታቸው በሠራዊቱ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ በመሆኑም፣ አባላቱ እዚሁ ፊታችን ዕርምጃ ይወሰደባቸው በማለት ቁጣቸውን መግለጻቸውን ከፍተኛ መኮንኖቹ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት 66 የሠራዊቱ አባላት በቀዳማዊ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ፍድር እንደተሰጣቸውና የተቀሩት አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ተነግሯል፡፡ ‹‹ቤተ መንግሥት የሚገባው በምርጫ ነው እንጂ በጠመንጃ አይደለም ሲሉ የሠራዊቱ አባላት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፤›› ሲሉም መኮንኖቹ አስረድተዋል፡፡

በተያያዘም በሠራዊቱ እየተሠራ ያለው የሪፎርም ሥራ ዓመቱን ሙሉ እንደሚቀጥልና በቀጣይም አሁን የተጀመረውን ሪፎርም ጥልቀት የማስያዝ ሥራ እንደሚቀጥል ተነግሯል፡፡
ሪፖርተር (ብሩክ አብዱ )

No comments:

Post a Comment