Tuesday, January 20, 2015

ሃይማኖታዊ በዓላት የአብሮነታችን ማሳያና የገፅታ ግንባታው ፈርጦች ሆነዋል!

(ጥር 12/2007, (አዲስ አበባ))--የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባለፉት ዘመናት ገዢዎችና በተለያዩ ጊዜያት የፖለቲካ ሥልጣን የጨበጡ ኃይሎች የጫኑባቸውን ጭቆናና በደል በጋራ ትግላቸው አስወግደዋል። በመደብ ልዩነትና በዘር እየከፈሉ የማንነት፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የታሪክና የባህል መገለጫዎቻቸውን ለመጨፍለቅ ያካሄዱባቸው ለዘመናት የዘለቀ የጭቆና ጫና ዳግም ላይመለስ ፈራርሷል። ለዚህ ደግሞ ከሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ ሥር እየሰደደ የመጣው ህገመንግሥትና ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ዋስትና መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም።

የሀገራችን ህዝቦች ጥንትም ሆነ ዛሬ ተከባብረው በእኩልነት የሚያመልኳቸው ሃይማኖቶች አሏቸው። ኢትዮጵያውያን በመቻቻልና በወንድማማችነት የሚኖሩ፣ ሰው አክባሪና የሞራልና ሥነምግባር ባለቤቶችም ናቸው የሚባለው ገዢዎች እንኳን ለማለያየት የሞከሩት ግን ህዝቡ ለዘመናት ይዞት የዘለቀው ብዝሃነትን የተላበሰ መንፈሳዊ ሀብት ስላላቸው ነው። አሁን ደግሞ ህገመንግሥቱ ለመላው የሀገሪቷ ዜጐች የእምነት ነጻነት ዋስትና ሰጥቷል። መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ በመሆናቸው መንግሥታዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ መንግሥት እንደማይኖር በግልፅ ተደንግጓል። በተግባርም እየሆነ ያለው ይሄው ነው።

በዚህ መልካም እድል እየተጠቀሙ የእምነት አስተምህሮትን በማስፋት ሃይማኖታዊ ሥርዓትን፣ በዓላትን በነፃነትና በእኩልነት መንፈስ የሚያከናውኑ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። በተለይ በተለያዩ የእምነት ተከታዮች እየተከበሩ ያሉ ሃይማኖታዊ በዓላት ከመንፈሳዊ እሴታቸው ባሻገር ኢትዮጵያዊ ባህልና የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት የሚንጸባረቅባቸው ሆነዋል። በህዝቡ አብሮነት፣ አለባበስ፣ ዝማሬና ዜማ እንዲሁም በሀገራዊው የዴሞክራሲያዊ አንድነታችን መገለጫ ሰንደቅ ደምቆና ተውቦ የሚታየው ሥነ-ሥርዓት የሌላውን ዓለም ህዝብ ትኩረትም እየሳበ ነው።

ከቀደምቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ተከታዮች ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በልዩ ስሜት እየተከበረ ያለው የጥምቀት በዓልም አንዱ ማሳያ ነው። በተለይ እንደ አዲስ አበባ፣ ጐንደርና መቀሌን በመሳሰሉት ከተሞች በዓሉን ተከትሎ የሚካሄዱ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ሥነ-ሥርዓቶች፣ የንግድ፣ ኢንቨስትመንት ባዛር፣ የመዝናኛና መሰባሰቢያ ደማቅ ሁነቶች ሆነዋል። በተለያዩ ሀገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና በርካታ የውጭ ሀገር ዜጐች ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት፣ ለዘመድ ጥየቃም ሆነ ለኢንቨስትመንት እንዲሁም ደማቁን ሃይማኖታዊ በዓል ለማክበር እየተንቀሳቀሱ ያሉበት አንዱ ምክንያትም እየሆነ ነው።

ሌሎች የኦርቶዶክስ ቤተርክስቲያን ተከታዮችና ምዕምናን የሚያከብሯቸው በዓላትም ከመቼውም ጊዜ በላቀ አኳኋን እየተከበሩ ናቸው። እንደ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት፣ ፋሲካና መስቀል ያሉት መንፈሳዊ በዓላት የሀገራችን ህዝቦችን አኗኗር፣ ልዩ ሃይማኖታዊ ቀለማትን ከማንፀባረቅ ባሻገር የሌላው ሀገር ጐብኝን መሳብ እየቻሉ ነው። በተለይ የመስቀል ደመራ ልዩ ሥነ-ሥርዓት እየጐለበተ በመምጣቱ የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የባህልና ትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) በመንፈሳዊ ቅርስነት እንዲመዘገብ አድርጐታል። በዚህም የሀገሪቷ መንፈሳዊ የዓለም አቀፍ ቅርሶች ቁጥር ከፍ እንዲል አስተዋፅኦ አድርጓል።

በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበሩ፣ እንደ ኢድአልፈጥር፣ አረፋና መውሊድ ያሉት በዓላትም በሰፊው አማኙ ህዝብ በድምቀትና በሰላም የሚከበሩ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእምነቱ ተከታዮች በብዛት ወደ ክብረበዓሉ መከበሪያ ስፍራ ወጥተው ማክበራቸው ብቻ ሳይሆን ቀደምት በሆኑ መስኪዶች የሚስተዋሉ መንፈሳዊ የአከባበር ሂደቶች ትልቅ ዋጋ የሚሰጣቸው ሆነዋል። በሌሎች የእምነት ዘውጐች ማለትም ፕሮቴስታንትና ካቶሊክም ውስጥ የሚገኙ አማኞች ህገመንግሥቱ የፈጠረላቸውን የእምነት ነፃነት መሠረት በማድረግ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ክዋኔዎችን በድምቀት ከመከወን አልተቆጠቡም።

ጥቅሉ የብዝሃነታችን መገለጫ የሆኑት ሃይማኖታዊ በዓላትና መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች የአበሮነታችን ዋነኛ ማሳያዎች ሆነዋል የሚባለው በተለያዩ ምክንያቶች ነው። አንደኛ መላው ህዝብ ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ያረጋገጠለትን እኩልነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት መሠረት በማድረግ በመቻቻልና በአብሮነት የሚያከብራቸው በመሆኑ ነው። ሁለተኛው በየእምነቱ ሥነ-ሥርዓት ሁሉ ምእመኑ ኢትዮጵያዊ ማንነቱና ጨዋነቱን መሠረት አድርጐ ሲያከብር የሌላውን ዓለም ትኩረት ለመሳብ መቻሉ ነው። ከዚህም በላይ በሀገራችን የሚከበሩ የተለያዩ ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ በዓላት ለሀገር ገፅታ ግንባታም ሆነ የቱሪስት መስህብነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ መሆናቸው ነው።

ከረጅሙ ታሪካችን ጋር እየተሳሰሩ ሲመዘኑም በዩኔስኮ መመዝገብ የቻሉ ትልልቅ መንፈሳዊ ፈርጦች እየተገኙበት ያለ መስክ መሆኑም ሊጤን ይገባል። በዚህ ረገድ ለወደፊቱም መንግሥትና የየእምነቱ ተከታዮች ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በሁሉም ሃይማኖቶችና መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች የሚከበሩ በዓላት ያላቸውን ድርብርብ ፋይዳ ተገንዝቦ እንዳይበረዙና እንዳይፈዝዙ መትጋትም ይገባል።
 
በሃይማኖት አክራሪነት ፅንፈኝነት አጉል ብሂል የህዝቦችና መቻቻልን የሚጐዱና የሀገርን የሠላም አውድነት የሚያጠለሹ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ሁሉም ዘብ ሊቆም ይገባል። በየበዓላት ወቅት የተቸገሩ ድሆችን የመጠየቅ፣ የታሰሩና የታመሙትን ወገኖችን የመጐብኘት ሞራላዊ ግዴታችንንም ለአፍታ ያህል ልንዘነጋ አይገባም። ኢትዮጵያውያን ካሉን መልካም ፀጋዎች መካከል ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ በዓላት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ መባሉም ለዚሁ ነው።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ 
 
Related topics:
Home
 

No comments:

Post a Comment