Thursday, February 13, 2020

የቫላንታይን ቀን በአንዳንዶች ዕይታ

(Feb 13, 2020, (አዲስ አበባ))--በአዳዲስና ዘመናዊ ሁነቶች እየተራቀቀች የመጣችው አዲስ አበባ በተለያዩ አገሮች ያሉ ልምዶችን ለነዋሪዎቿ እያለማመደች ነው፡፡

በተለይ በአብዛኛው የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ በየወሩ ለማየት በሚቻል መልኩ የሚከበሩት ፋዘርስ ዴይ፣ ክሬዚ ዴይ፣ ካልቸር ዴይ፣ ማዘርስ ዴይ፣ እና ሌሎች በርካታ ክብረ በዓላት በተማሪዎች መካከል ተንሰራፍተዋል፡፡


ነገ የካቲት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚከበረውን የቫላንታይን ቀንን አስመልክቶ ገና ከወዲሁ በከተማዋ የሚታየው ሽርጉድም የየአገሮች ልምድና ባህል መወራረስን የሚያሳይ ነው፡፡ የቫላንታይን ቀን አከባበር በኢትዮጵያ በዚህን ወቅት እየገነነ መጣ ተብሎ ለማስቀመጥ ቢቸግርም ከዘጠናዎቹ አጋማሽ ወዲህ መጉላቱን አንዳንዶች ይስማሙበታል፡፡

በአዲስ አበባ በሚገኙ ወጣቶችና ወጣት ጥንዶች እየተዛመተ የመጣው የፍቅረኞች ቀን አከባበር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ አገር በቀል ባህል እየመሰለ መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያውያን በበርካታ ባህሎቻችንና የእኛ በምንላቸው መገለጫዎች በዓለም ላይ ብንታወቅም ከነኚህ ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ባህሎቻችን መካከል የተወሰኑትን ከሌሎች የተቀላቀሉ እንደሆኑ የሠርግ ሥነ ሥርዓታችንን በማንሳት የሚናገሩ አሉ፡፡

በቬሎ፣ በሱፍ፣ በብልጭልጭና በሻምፓኝ እየታጀበ የሚሠረገው የኛው የከተማ ሠርግ አገር በቀል አለመሆኑንና ወደ ፈረንጅ አገር ዘወር ብለው የተመለሱ የአገር ልጆች ያመጡት የውጭ አገር የሠርግ ሥነ ሥርዓት ነው፡፡

የፍቅረኞች ቀንም ከዚሁ ከሠርግ ሥነ ሥርዓት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ክስተት ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት ዓለም አቀፋዊነቱ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ይህንኑም ባህል በነዛ የሠለጠኑ አገራት ለትምህርትና ለሥራ ተጉዘው የተመለሱት የወንዝ ልጆችና የቴክኖሎጂና የኔትዎርክ መስፋፋት ወዲህ አሻግረውታል፡፡ ለዛሬው የተጋነነ ሁኔታ ምክንያቱ ሉላዊነትን (ግሎባላይዜሽንን) ተከትሎ የመጣው የመገናኛ ብዙሃን፣ የማኅበራዊ ድረ ገጾች ተፅዕኖ በወጣቶቹ ላይ የገዘፈ ጥላ ማጥላቱ ነው፡፡

በቫላንታይን ቀን መሠረታዊ ቁም ነገር ላይ ብዙም የማያግባባ አንድምታ እንደማይኖረው ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ፍቅረኞች (ጥንዶች) የቫለንታይን ቀንን አስመልክተው ፍቅራቸውን ቢዘክሩና ስለነገ ሕይወታቸውም ቃልኪዳን ቢገባቡበትም ምንም ክፋት የለውም፡፡ ብዙዎቻችን የማያስማማውና ለሞቀ ክርክር ሊጋብዝ የሚችለው ግን ከቁም ነገሩ ባሻገር እየተስፋፋ የመጣው ባዕድ ልማድ ነው፡፡

ወጣት ፀጋነህ ችሮታው በአንድ የውጭ ድርጅት ውስጥ የሚሠራ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ነው፡፡ ይህ ቀን በመጣ ቁጥር የሚያበሳጨው ምክንያት እንዳለው በመገረም ይናገራል፡፡ “ይህንን ቀን በጣም ነው የምጠላው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የገዛ ጓደኛዬን የተጣላሁበት ቀን ነው፡፡ አብሮ አደግ የሆነው ጓደኛዬ ከፍቅረኛው የቀረበለትን ልዩ የመዝናኛ ፕሮግራም ለማቃናት ሲል በርከት ያለ ገንዘብ በብድር ጠይቆኝ ልሰጠው ባለመቻሌ ልንቀያየም በቅተናል፤” ይላል፡፡

 “ምንም እንኳን ጊዜው ካለፈ በኋላ በግልፅ ተነጋግረን መተማመን ብንችልም ለዓመታት ፀንቶ የቆየው ልባዊ ጓደኛነታችንን ግን ወደነበረበት ቦታ መመለስ አልቻልንም፡፡ ለዚህ ደግሞ የጓደኛዬ ለፍቅረኛው ያለው ስሜትና በእሷ መልካም ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሠረተ አኗኗር እንዲኖረው ከመፍቀዱ የተነሳ ነው፤” ሲል ያብራራል፡፡

ኢየሩሳሌም ሳህሉም የዚህን “ቅጥ ያጣ” የምትለውን የፍቅረኞች ቀን አከባበር ከሚኮንኑት አንዷ ናት፡፡ እንደ ኢየሩሳሌም አስተያየት ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ ወይም ሊሆን በማይገባው ሁኔታ በርካታ ገንዘብ አውጥቶ ስጦታ መለዋወጡ፣ ከከተማ ወጣ ብሎ ውድ በሆኑ ሥፍራዎች መዝናናቱና ከልክ በላይ በሆነ መዝናናት ሕይወትን ለአደጋ ማጋለጡና ሥራን መበደሉን በጽኑ ትቃወመዋለች፡፡ “ወጉ እንዳይቀር ብቻ በምሽት ተገናኝቶ መጨዋወቱና የወደፊት ሕይወትን መተለሙ ከጥሩ የእራት ግብዣ ሥነ ሥርዓት ጋር በቂ ይመስለኛል፡፡ መቼም ስጦታ መለዋወጡ ደንብ ነው ከተባለም ቀለል ባሉ ስጦታዎች መግለፅ ይቻላል፤” ትላለች፡፡

በተቃራኒው ደግሞ “የማንም ይሁን የማን ዓለም አቀፍ ባህል ነውና ደስ ይላል፤” የሚለው ወጣት አሽረፍ ሙሳ ፍቅረኛ ባይኖረውም እንኳን በበዓሉ ቀን የሚለበሰውን ለብሶ ከሱ ቢጤ ሴት ጓደኞቹ ጋር በአንዱ የመዝናኛ ሥፍራ እንደሚታደም ሐሳቡን ይገልጻል፡፡ በእርግጥ አሽረፍ አንድ የማይደብቀው ነገር ቢኖር በእነሱና ከልብ በሚፋቀሩት ጥንዶች መካከል ሰፊ ልዩነት መኖሩንና ይህም አንዳንድ ጊዜ የሥነ ልቦና ጫና እየፈጠረበት “በሚቀጥለው ዓመት እንኳን ከእውነተኛ የፍቅር ጓደኛዬ ጋር አደርገዋለሁ” የሚል ምኞት እንዲያድርበት ምክንያት እንደሆነ ነው፡፡

ከቀናት በፊት ደጃፋቸውንና በሮቻቸውን በእንኳን አደረሳችሁ የምኞት መግለጫ ማስታወቂያዎች ማሸብረቅ የጀመሩት ካፌዎች፣ ሆቴሎችና መጠጥ ቤቶችም እንደ ገና ሁሉ ቤቶቻቸውን በቀያይ መብራቶችና ጨርቆች አደማምቀዋል፡፡ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ያካተቱ ዝግጅቶችንም እንዳሰናዱ በየሬዲዮ ጣቢያው ማስነገሩን ቀጥለዋል፡፡

ሃያ ሁለት አካባቢ በሚገኝ አንድ ዘመናዊ ካፌ ውስጥ በአስተዳዳሪነት የሚሠራው ከፍያለው ስሜ ወቅቱን ከሌሎች የበዓል ወቅቶች ጋር የሚያገናኝበትን ምክንያት እንዲህ ሲል ይገልጻል፡፡ “አንደኛ የፍቅር ነገር በመሆኑ በራሱ ደስ ይላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከገቢ አንፃር ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ ቤቱን ከማሳመርና ከማጽዳት ጋር የተያያዘ ነው፡፡”

ይሁንና ከፍያለውን ቅር የሚያሰኘው አንድ ነገር እንዳለ ገልጿል፡፡ እሱም ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊ ሕፃናት በርከት ባለ ቁጥር በእንዲህ ዓይነቱ ፕሮግራም ዋና ተሳታፊ መሆንና በመጨረሻም ተገቢ ባልሆነ መልኩ ምሽቱን ለማሳለፍ መሞከር ብዙ ጉዳት ያለውና ጉዳዩን በውል ለማይረዳው ቤተሰብም ከፍተኛ ችግር ያለው መሆኑን ነው፡፡
ሔኖክ ረታ
Source: Reporter

3 comments:

Anonymous said...

አይይ! "ድንቄም የቆቱን አወርድ ብላ የብብቱዋን ጣለች አሉ..." Better to save our own culture ..

Anonymous said...

erasen mhone melkam

Anonymous said...

qenu tasebo mewalu berasu keadeguche ageroche gare menestasterachenene yegelestale mekeberu ayasekefame huletu yefeker guwadegnamoche yerasachew yehone bota qen yenorewale ahune gen bezihe generation feker maga endehone melawe tefetoal meneayenet abelale yehune ayeru yehune ayetawekem telanet teweledo gena 14wey 15 amete sayemolawe end shemebeko yrezemuna satwa sel wend wendu selesate becha new asetesasebachew edemawe alederesem tebeleo mayegebawen ayeshetem endayebale ayemelekethem yelale selezi benezihe agerachen endatetefa tegeto mesteleye yegebale elalew.

Post a Comment