Friday, February 01, 2013

የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች የአፍሪካ ዋንጫው ድምቀት ነበሩ

(Feb 01, 2013,አሰግድ ተስፋዬ )--ደምቀው ሻምፒዮናውን ያደመቁ የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች፤ኑሮዋቸውን በደቡብ አፍሪካ ያደረጉ ኢትዮጵያውያን በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለዋሊያዎቹ ከፍተኛ ድጋፍ ከመስጠታቸውም በላይ የሻምፒዮናው ድምቀት መሆናቸውን በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። 
 

ዋሊያዎቹ ማራኪና አዝናኝ ጨዋታ ማሳየት ሳይሳናቸው ነገር ግን በልምድ ማነስና በጥቃቅን ስህተቶች ወደ ቀጣዩ ዙር አለማለፋቸውን ተከትሎ ሻምፒዮናው የዋሊያዎቹን ደጋፊዎች እንደሚያጣና በእዚህም የውድድሩ ድምቀት ሊደበዘዝ እንደሚችል ጎል ዶት ኮም ድረ ገጽ ጽፏል።

« የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች በአንድነትና በኅብረት ለቡድናቸው ካለማቋረጥ የሰጡት ድጋፍና ለድጋፉ ማድመቂያ የተጠቀሙባቸው ቁሳቁስ የአፍሪካ ዋንጫው ከ31 ዓመት በኋላ የተመለከተው ተጨማሪ ድምቀት ሆኖ አልፏል » ብሏል ድረ ገጹ። 

ኢትዮጵያውያኑ ደጋፊዎች ወጣት አዛውንት፣ ወንድ ሴት ሳይሉ በተደራጀ መልኩ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት የደመቀ ልብስ በመልበስ፣ ቀለማቱን ፊታቸውንና ጸጉራቸውን በመቀባት የውድድሩ ልዩ ድምቀት መሆን ችለው ነበር ብሏል ዘገባው።

« በቋንቋቸው በመዝፈን ለቡድናቸው ተጨማሪ ኃይል ሆነዋል። ቡድናቸው ከውድድሩ እስኪሰናበት ድረስ በታማኝነትና በፍቅር አበረታትተዋል » ሲል ጽፏል። ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን በተመለከተም አነስተኛና ጥቃቅን ስህተቶችን እያነሱ ዘወትር ብሔራዊ ቡድኖቻቸውን ከሚወቅሱና ቅሬታ ከሚያቀርቡት ከሌሎች አገሮች በተለየ የምሥራቅ አፍሪካዋ አገር ጋዜጠኞች በተረጋጋና በሰከነ ስሜት ነገሮችን በአንክሮ የሚከታተሉ መሆናቸውንም ዘገባው አስነበቧል። ብዙ ነገር ሳይጠብቁ ወደ ውድድሩ ማምራታቸውን መታዘቡንም ነው ድረ ገጹ ያስነበበው።
 
በተለይ የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች ለቡድናቸው ተሰባስበው ይሰጡት የነበረው ማራኪ ድጋፍ ሻምፒዮናውን ለተከታተሉ ሰዎች ዘወትር የማይረሳ ትዝታ ሊሆንባቸው እንደሚችልም ነው የጻፈው።

የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች ከልባቸው ያመኑበትን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉም ዘገባው አስነብቧል። ይህንንም ከደጋፊዎቹ መካከል የተወሰኑት ዋሊያዎቹ ከዛምቢያ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ለፈጸሙት ጥፋት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መቀጣቱን ተከትሎ በቀጣዩ ጨዋታ ለተፈጠረው ነገር ይቅርታ መጠየቃቸውንና እግር ኳስን እንደሚወዱ በትልቅ ጽሑፍ ማስነበባቸውን በአብነት በማንሳት ጽፏል።

ድረ ገጹ « ዋሊያዎቹ ከምድባቸው ማለፍ አለመቻላቸው ለደጋፊዎቻቸው የሚያስቆጭ ቢሆንም ለሻምፒዮናው ግን ልዩ ድምቀት ሆነዋል» በማለት ደጋፊዎቹን አድንቋል። የእግር ኳስ ዓለም የዋሊያዎቹን ደጋፊዎች ማጣት ስለማይፈልግ ኢትዮጵያ በታላላቅ የውድድር መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ መሳተፍ ይኖርባታል ሲል አስተያየቱን ጽፏል።
 
ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ የሚገቡትና ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ደማቅ አቀባበል የሚደረግላቸውን ዋሊያዎቹን በተመለከተ የናይጄሪያው አሰልጣኝ ስቴፈን ኬሺ በሰጡት አስተያየት « ቡድኑ ለቀጣይ አምስት ዓመታት አብሮ መቆየት ከቻለ የአህጉሪቱ የበላይ መሆን ይችላል » ብለዋል።

ዋሊያዎቹ በአብዛኛው በልምምድ ሜዳ ላይ የሚተገበርን ተጠጋግቶ ኳስ በአጭር እየተቀባበሉ የመጫወትን ስልት አዝናኝ በሆነ መልኩ ያሳዩበትን ሁኔታ አሰልጣኙ አድንቀዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ, በአሰግድ ተስፋዬ 

No comments:

Post a Comment