Saturday, January 19, 2013

የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በድምቀት ተከብሮ ዋለ

(Jan 19, 2013, Addis Ababa)--የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከብሮ ዋለ፡፡


ዛሬ ማለዳው ላይ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በሺህዎች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች፣የውጭ ቱሪስቶች፣አምባሳደሮችና በርካታ እንግዶች ታቦታቱን ወደየመጡበት ሸኝተዋል፡፡


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቢ መንበረ ፓትሪያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ናትናኤል በአዲስ አበባ በጃንሜዳ ለታደመው ሕዝበ ክርስቶያን እግዚአብሔር ሐብቱን ለሰው ልጆች ከሚያድልባቸው ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ጥምቀት_አንዱና የመጀመሪያው እንደሆነ አስተምረዋል፡፡

በዓሉን ለመታደም በስፍራው የተገኙት በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር ዶክተር መሐመድ ኢድሪስ በበኩላቸው በዓሉ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን፤ ብሄራዊ ትርጉም ያለው የአንድነት፣ የሰላምና የእድገት ማሳያና አስደሳች መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

''ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለአገሪቱ፣ ለአፍሪካና ብሎም ለመላው ዓለም ሕዝብ በአንድነት እግዚአብሄርን ማክበር እንደሚችሉ ያሳየችበት በመሆኑ ሌሎች አገሮችም  ሊማሩበት ይችላሉ'' ብለዋል፡፡

በዓሉ ከመንፈሳዊነት ባሻገር ለአንድነት፣ ለሰላምና ለልማት ያለውን ትርጉም ለመላው ዓለም እንደሚያሳይና በበዓሉ ላይ በመካፈላቸው ደስታ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።'' ኢትዮጵያና ግብፅ አንድ ቤተሰቦች ነን መልካም በዓል ይሁንላችሁ'' ሲሉ መልካም ምኞታቸውን አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ታደሰ በንቲ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉ የአገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ለዘመናት ሲያከብሩት የኖሩት ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክና የቱሪዝም ሃብት የሚተዋወቅበት የሕዝቦች የማንነት መገለጫ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት ጃንሜዳን ጨምሮ በአዲስ አበባ 16 የተለያዩ ቦታዎች ያደሩት ታቦታት ከጥቂቶቹ በስተቀር በመጡበት አኳኋን ወደ የአጥቢያቸው በሰላም ተመልሰዋል፡፡
 ምንጭ፡ ኢዜአ
 Home

No comments:

Post a Comment