Saturday, January 19, 2013

የከተራ በዓል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከበረ

(አዲስ አበባ ጥር 10/2005)--የእየሱስ ክርስቶስ የበዓለ ጥምቀት ዋዜማ የከተራ በዓል ዛሬ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ተከብሮ ዋለ፡፡ 


በዓሉ በተለይ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ የተከበረው በሺህዎች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች፣የውጭ ቱሪስቶች፣አምባሳደሮችና ሌሎችም እንግዶች በተገኙበት ነበር። ታቦታቱ ከየአድባራቱ ሲነሱ ብዑዓን ጳጳሳት፣የዐብያተ ክርስቲያን የሰንበት ተማሪዎች፣ ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን፣ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ዲያቆናት ቀሳውስት፣በሺህዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን፣የውጭ ዜጎች በአሉ ወደሚከበርበት ሥፍራ በታላቅ ድምቀት አምርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዐቃቢ መንበረ ፓትሪያሪክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ናትናኤል ከብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን ባህረ ጥምቀቱ ሥፍራ ሲደርሱ በበዓሉ አከባበር ላይ በነበሩ ምእመናን ዘንድ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ ብዑእነታቸው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የአየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት የሰላም ተምሳሌት በመሆኑ በዓሉ ሰላምንና መቻቻልን በማስተማሩ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በመደጋገፍና በመረዳዳት ሊያከብረው ይገባል። 

ቅዱስነታቸው በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የስምምነትና የአንድነት በዓል እንዲሆንም ተመኝተዋል፡፡ ብጹእነታቸው ቃለ ምእዳንና ቡራኬ ከሰጡ በኋላ ታቦታቱ ለማደሪያ ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳኖቻቸው ገብተዋል፡፡ ኢዜአ በበዓሉ ሥፍራ ላይ ያነጋገራቸው የውጭ ቱሪስቶች በኢትዮጵያ ጥንታዊና መንፈሳዊ በዓላት ተጠብቀው በመቆየታቸው ለአገሪቱ የውጭ መስህብ በመፍጠር የሃብት ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያውያን በባህላቸውንና ትውፊታቸውን ጠብቀው እዚህ በማድረሳቸው ሊኮሩ እንደሚገባውም አመልክተዋል።በነገው እለት ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የጥምቀት በዓል ይከበራል፡፡ ጃንሜዳን ጨምሮ ታቦታቱ በአዲስ አበባ 16 የተለያዩ ቦታዎች የሚያድሩ ሲሆን፣ ከጥቂቱ በስተቀር ታቦታቱ በመጡበት አኳኋን ወደየአጥቢያቸው እንደሚመለሱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።  
Source: ENA

No comments:

Post a Comment