Wednesday, January 16, 2013

ቅዱስ ሲኖዶስ በሰሜን አሜሪካ ሲካሄድ የነበረው የሰላምና የአንድነት ጉባዔ አለመሳካቱን ገለጸ

(አዲስ አበባ ጥር 8/2005)-- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ በሰሜን አሜሪካ ሲካሄድ የነበረው የሰላምና የአንድነት ጉባኤ አለመሳካቱን አስታወቀ። 

(ena)
ቅዱስ ሲኖዶሱ የስድስተኛው ፓትሪያሪክ ምርጫ የቤተክርስቲያኗን ቀኖናውን ጠብቆ እንዲካሄድም ውሳኔ አሳለፈ። ቅዱስ ሲኖዶሱ በወቅታዊ የቤተክርስቲያኗ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ያወጣው የአቋም መግለጫ ከኅዳር 25-30 ቀን 2005 በአሜሪካ ዳላስ ከተማ ውስጥ የተካሄደውን የሰላምና የአንድነት ጉባኤ እንዲሁም የስድስተኛውን ፓትሪያሪክ ምርጫ ያካተተ ነበር።

 የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫው እንዳመለከተው ከ20 ዓመታት በፊት የቤተ ክርስቲያኗ አራተኛ ፓትሪያሪክ የነበሩት ጳጳስ ነሐሴ 28 ቀን 1983 በወቅቱ ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት ሥልጣናችውን በራሳቸው ፈቃድ ማስረከባቸውን አስታውሷል። በወቅቱ የነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ ጳጳሱ ተሽሏቸው ወደ መንበራቸው ይመለሳሉ በሚል ለ10 ወራት ያህል ሲጠባበቅ እንደቆየ ያስታወሰው መግለጫው፣ ነሐሴ 28 ቀን 1983 ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ፍንጭ መስጠት ባለመቻላቸው ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቅሷል። 

ቅዱስ ሲኖዱሱ የቤተክርስቲያኗ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ግንቦት 5 ቀን 1984 አምስተኛውን ፓትሪያሪክ መምረጡንም መግለጫው አስታውሷል። ሆኖም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ እኒሁ ፓትሪያሪክ በሞያሌ በኩል ኬንያ ገብተው ሰባት ዓመታትን ከቆዩ በኋላ ወደ ሰሜን አሜሪካ በማቅናት በስደት አገር ሲኖዶስ ማቋቋማቸውን አብራርቷል። 

ድርጊቱ በቤተ ክርስቲኗ ታሪክ ውስጥ ተሰምቶ የማይታወቅ ከመሆኑም ባሻገር ከቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ውጭ መሆኑንም ገልጿል። እንደመግለጫው ከሆነ ይህን ድርጊት ለማረም ሲኖዶሱ ከ1999 ጀምሮ በስደት የተቋቋመው ሲኖዶስ አባላትን ሰሜን አሜሪካ ድረስ በመሄድ ለማነጋገርና ወደ ቤተክርስቲያኗ እንዲገቡ በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። 

ቅዱስ ሲኖዶሱ አራተኛው ፓትሪያሪክ ወደ አገራቸው ተመልሰው ደረጃቸውና ክብራቸው ተጠብቆ የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶ በመረጡት ቦታ በጸሎት ተወስነው እንዲኖሩ የሚቻለውን ያህል ጥረት ቢያደርግም፤ የተጠበቀው ሰላምና አንድነት ተቀባይነት አለመገኘቱን ገልጿል። 

ስድስተኛው ፓትሪያሪክ በአንድነት ለመምረጥ እንዲቻል በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አባቶች ወደ አገራቸው እንዲገቡ ለማመቻቸት ቅዱስ ሲኖዶሱስ ከህዳር 26- 30 ቀን 2005 ወደ አሜሪካ የልዑካን ቡድን በመላክ ድርድር አካሂዷል። 

ነገር ግን በሰሜን አሜሪካ አባቶች የአራተኛው ፓትሪያሪክ መንበራቸው ክፍት በመሆኑ ወደ መንበራቸው መመለስ እንዳለባቸውና ሙሉ የፓትሪያሪክነት ሥልጣን ተሰጥቷቸው ቤተ-ክርስቲያኗንም መምራት እንዳለባቸው በመግለጽ ይህ የማይደረግ ከሆነ እንደማይስማሙ በመግለጻቸው የተጠበቀው ስምምነት ሳይገኝ መቅረቱን መግለጫው ዘርዝሯል። 

የቅዱስ ሲኖዶሱ በመሪ አለመኖር ምክንያት የቤተክርስቲያኗ ሥራ እየተጎዳ በመምጣቱ ቀደም ሲል የሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ አማካኝነት የስድስተኛው ፓትሪያሪክ ምርጫ ሂደት የቤተክርስቲያኗን ህግ ጠብቆ እንዲከናወን ውሳኔ አሳልፏል።

በአስመራጭ ኮሚቴው አማካኝነትም የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ይደረጋል። አራተኛው ፓትሪያሪክ በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁትን የመንበረ ፓትሪያሪክ ሥልጣን ዳግም ለመመለስ ያቀረቡት ጥያቄ የቤተክርስቲያኗን ሕግ የሚጥስና ሥርዓት አልበኝነት የሚያሰፍን በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዱሰ እንደማይቀበለውኝ አረጋግጧል። 

በውጭ ካሉ አባቶች ጋር የሚደረገው የሰላምና የአንድነት ድርድር ወደፊትም እንደሚቀጥልና የተሰጠውን የሰላም እድል በመቀጠም ወደ አንድነት ለመምጣት ፈቃደኛ ከሆኑ ቤተክርስቲያኗ ለመቀበል ዝግጁ መሆኗን መግለጫውን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። 
Source: Ethiopian News Agency

No comments:

Post a Comment