Thursday, March 08, 2012

ነባር ይዞታ ወደፊት በሊዝ መካተቱ እንደማይቀር ተጠቆመ

‹‹አርቆ አስተዋይ ባለይዞታ ዛሬ ወደሊዝ እንዲገባ ይመከራል››
(Wednesday, 07 March 2012)--የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር  ነባር ይዞታዎች በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ውዥንብር ፈጥሮ ባለው የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዲሱ አዋጅ 721/2004 መሠረት በሊዝ እንደማይካተት (ለሦስተኛ ወገን ካልተላለፈ በስተቀር) ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጭምር የተናገሩ ቢሆንም፣ በአዲሱ አዋጅ አይካተት እንጂ በቀጣይ ከኅብረተሰቡ ጋር በመወያየትና መግባባት ላይ በመድረስ ወደ ሊዝ መግባቱ እንደማይቀር ተጠቆመ፡፡

ነባር ይዞታዎች ወደ ሊዝ መግባታቸው እንደማይቀር የተጠቆመው፣ የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከመንግሥት ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ከጋዜጠኞች ጋር የሊዝ አዋጁን ለማስፈጸም ባረቀቀው ሞዴል ደንብ ላይ በተደረገ ውይይት ነው፡፡

ለውይይት በቀረበው ረቂቅ ደንብ ነባር የከተማ ቦታ አስተዳደርን በተመለከተ ባሰፈረው ዝርዝር ውስጥ፣ ከሕዝብ ጋር ተወያይቶና ዝርዝር ጥናት ተከናውኖ እስከሚወስን ድረስ ነባር ይዞታ ባለበት እንደሚቀጥል በሚገልጸው ሐሳብ ዙሪያ ከተሳታፊዎቹ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡

‹‹የነባር ይዞታን ውዝግብ ይኼ ደንብ ይፈታል ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም በአዋጁ በግልጽ የተቀመጠውና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም በፓርላማ ያረጋገጡት፣ ነባር ይዞታ በሊዝ እንደማይገባ ነው፤›› በማለት ዳርዳሩን ከማለት ‹‹ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ መግባቱ አይቀርም ተብሎ ለምን አይቀመጥም?›› በማለት ጥያቄ ያነሱ ተሳታፊ ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ እሳቸው ስለነባር ይዞታዎች ሲናገሩ የሊዝ አዋጁ እንደማይመለከታቸው መግለጻቸውን አስታውሰው፣ ‹‹መንግሥትን በሆነ ጉዳይ ላይ ወደፊት ሕግ አላወጣም ብለህ ቃል ኪዳን ግባ የሚል ጥያቄ ፍትሐዊ ነው?›› በማለት ጥያቄ ያነሱት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ ናቸው፡፡

ባለቤቶቹ ወይም ባለሚናዎቹ የሚደመር ወይም የሚቀነስ ነገር ካለ መወያየት እንዳለባቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ከባለይዞታዎች ጋር መተማመን፣ መደማመጥና መስማማት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ 
 
በሊዝ አዋጁ ላይ በሁለት፣ በሦስት ወይም በአራት ዓመታት ውስጥ ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ እንደሚገባ የሚገልጽ ሐሳብ እንዳልተቀመጠ የገለጹት አቶ መኩሪያ፣ የተቀመጠው (በረቂቅ ደንቡ) ከባለይዞታዎች ጋር ውይይት ተደርጎ መግባባትና መተማመን ላይ ሲደረስ ወደ ሊዝ ይገባሉ የሚል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደንቡ የአዋጁ ማስፈጸሚያ እንደማይሆን፣ የራሱ ጊዜ እንዳለውና በሰከነ መንገድ እንደሚታይ መቀመጡንም ጠቁመዋል፡፡

የመሬት ኪራይ ዋጋ ክፍያ ሁሌም አስተማማኝ እንዳልሆነ፣ ሊዝን ግን ለየት የሚያደርገው አንዴ ውል ከተፈረመ በኋላ እንደገና መከለስ እንደማይቻል የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ውሉን መከለስ የሊዝ አዋጁን መፃረር ስለሚሆን፣ ለ40፣ ለ60 ወይም ለ99 ዓመታት ውል ከተገባ የማይቀየር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አዲሱ የሊዝ አዋጅ ቀደም ሲል እንደነበረው አለመሆኑንና አንድ አስፈጻሚ ከአዋጁ ውጭ ፈጽሞ ቢገኝ በአዋጁ የተቀመጠው መቀጮ ተፈጻሚ እንደሚሆንበት የገለጹት አቶ መኩሪያ፣ በሒደት ኢኮኖሚው እየተጠናከረና የዋጋ ግሽበት እየተለዋወጠ ሲሄድ፣ አሁን ያለው የገንዘብ ዋጋና ከአሥር ዓመታት በኋላ የሚኖረው የገንዘብ ዋጋ እኩል እንደማይሆን አሳስበዋል፡፡ የመሬት የኪራይ ዋጋም ቢቻል በአንድ ዓመት ወይም በየሁለት ዓመቱ እንደሚከለስ በአዋጁ መደንገጉንም አስታውሰዋል፡፡

ነባር ይዞታ ያላቸው ሰዎች ዛሬ ወደ ሊዝ ቢገቡ የሚከፍሉት የሊዝ ዋጋ 200፣ 250፣ 300 ወይም 350 ብር ነው፤ ‹‹አርቆ አስተዋይ የሆነ ባለይዞታ ዛሬ ወደ ሊዝ ቢገባ ወይም ግባ በማለት በልበ ሙሉነት እመክራለሁ፤›› ካሉ በኋላ፣ ነባር ይዞታ የያዘ ሰው ከ10 ዓመታት በኋላ መንግሥት ግብር ሲከልስ ሁሉንም ስለሚከልስ በካሬ ሜትር የሚከፈለው ዋጋ እንደሚቀያየር በማሳሰብ መክረዋል፡፡

መንግሥት የመሬትን ግብር አይከልስም ብሎ የሚከራከር ሰው እንደሌለና አሁን እየተከፈለ ያለው የመሬት ዋጋ በዚሁ እንደማይቀጥል የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ከ15 እና ከ20 ዓመታት በኋላ የሊዝ መነሻ ዋጋና የመሬት ግብር በአራት እጥፍ ወይም ከዚያ በላይ ሊጨምር ስለሚችል ነባር ይዞታ ያላቸው ‹‹ባለበት ይቀጥል›› የሚል አስተሳሰብ እንደማይኖራቸው ተንብየዋል፡፡ ስለዚህ ነባር ይዞታ ያላቸው አሁኑኑ ወደ ሊዝ ቢገቡ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ደጋግመው በመናገር ገፋፍተዋል፡፡

ነባር ይዞታ ያላቸው የሚያቀርቡት አማራጭ በነበረበት ይቀጥል ቢሆንስ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ አቶ መኩሪያ ‹‹ላይሆን ይችላል›› ካሉ በኋላ፣ ትልቁ ነገር መንግሥት ይዞት የሚቀርበው አማራጭ ሊወስነው ስለሚችል ‹‹በነበረበት ይቀጥል ይላሉ የሚል እምነት የለኝም፤›› ብለዋል፡፡

ከመኖሪያ ቤት ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ማግኘት እንዳለባቸው፣ በተለይ በከተማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ምን ያህል ቦታ ማግኘት እንዳለባቸው ተወስኖ መቀመጥ እንዳለበትና ‹‹ምን ያህል ነው?›› የሚለው ፖሊሲ እስከሚዘጋጅ ክፍት መደረጉን አቶ መኩሪያ ገልጸዋል፡፡

በሊዝ ስለሚያዙ ይዞታዎች የግንባታ ማራዘሚያ ጊዜ ሲወሰን፣ በምን ምክንያት መራዘም እንዳለበትና እንደሌለበት በግልጽ እንዳልተቀመጠ ለተነሳው ጥያቄ፣ ሊራዘምበት የሚችልበት ዋና ዋና ምክንያቶችን ማስቀመጥ ጠቃሚ መሆኑንና ጥሩ ሐሳብ ስለሆነ በመመርያው ውስጥ እንደሚካተት ተናግረዋል፡፡

የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ (ካርታ) ያላቸውንና በተለያዩ (በቢል፣ በደብተር፣ በወረቀት) ሰነዶች የተያዙ ቦታዎችን እንዴት ማቀላቀል እንደሚቻል፣ ሁሉም ከመንግሥት ሹመኞች የተሰጡ ሰነዶች በመሆናቸው ሕጋዊ ይዞታ መሆን እንዳለባቸው እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል ተጠይቀው አቶ መኩሪያ አብራርተዋል፡፡

አንድን ይዞታ ሕጋዊ መሆኑን ለማረጋገጥ ሕጋዊ ሰነድ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ሰነድ አልባ ይዞታዎች የሚስተናገዱበት መመርያ መውጣቱን ጠቁመው፣ ካርታ የሌላቸው በዚያ ካርታ ሲሰጣቸው፣ የሚቀላቀሉበትን መንገድ መነጋገር እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡

አዋጁና ደንቡ የፍርድ ቤትን ሥልጣን መውሰዱን በሚመለከት ለተነሳው ጥያቄ፣ አዋጁ የፍርድ ቤትን ሥልጣን እንዳልወሰደና ሊወስድ እንደማይችል የገለጹት አቶ መኩሪያ፣ በሊዝ አዋጁ ላይ በግልጽ የተቀመጠው ባለይዞታው ከንብረቱ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ካለውና ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ከፈለገ መሄድ እንደሚችል መገለጹን ተናግረዋል፡፡

ሕገወጥ ቦታን በሚመለከት የመነሻ ዋጋው መብዛቱን በሚመለከት ለተነሳ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሩ፣ አንድ ሰው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 100 ካሬ ሜትር ቦታ ቢኖረው፣ ከፍተኛው የመነሻ ዋጋ 200 መቶ ብር ቢሆንና ቅድሚያ ለመክፈል ሁለት ሺሕ ብር ቢጠየቅ የበዛ አለመሆኑን በመግለጽ ዋጋው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በአጠቃላይ የሊዝ አዋጁ ይኼንን ኅብረተሰብ ከችግር ሽክርክሪት የሚያስወጣው መሆኑን አቶ መኩሪያ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ጋዜጠኞችና የመንግሥት ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች፣ በርካታ ጥያቄዎችንና የድጋፍ አስተያየቶችን ሰንዝርዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጴጥሮስ ወልደ ጊዮርጊስ በሰጡት የድጋፍ አስተያየት፣ ‹‹የቀረበው ደንብ ፀረ ልማቶች የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ ሲያራግቡት የነበረውን ውዥንብር መቶ በመቶ ያዳፍናል፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ኅብረተሰቡ ይዞታችንን ተቀማን በማለት ሲጨነቅ የነበረበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የሚፈታ ሞዴል ደንብ ነው፤›› በማለት ለውይይት የቀረበውን ረቂቅ ደንብ አንቆለጳጵሰውታል፡፡

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የ‹‹ዓይናችን ፕሮግራም››ን በማዘጋጀት ይታወቁ የነበሩት ጋዜጠኛ ሳሙኤል ፍቅሬ፣ አዋጁን በተዛባ መልኩ ሪፖርት በማድረግ ትልቅ ውዥንብር የፈጠሩት ሚዲያዎች እንደሆኑ በመግለጽ ሚኒስትሩ ለሰነዘሩት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

‹‹ትክክል ነው ሚዲያዎች ውዥንብር ፈጥረዋል፤ ነገር ግን ሚዲያዎቹ ውዥንብር የፈጠሩት ራሳቸው ተነስተው ባሰራጩት የፈጠራ ወሬ ሳይሆን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቴሌቪዥን መስኮትና በተለያዩ መግለጫዎች የተናገሩትን በመጥቀስ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ለምሳሌ ያህልም ‹‹ነባር ይዞታ በሊዝ ይገባል›› ያሉት ባለሥልጣናቱ ለሕዝብ አዋጁ እንዴት እንደሚጠቅም ማብራሪያ ይሰጥ በነበረበት ወቅት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ 
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment