(Sunday, 06 November 2011, Reporter)--በወርቅ ግብይት የተሰማሩ የጌጣጌጥ አምራቾችና ጌጣጌጥ ለማምረት ማረጋገጫ የተሰጣቸው ወርቅ ቤቶች፣ ለሚሠሯቸው ጌጣጌጦች ግብዓት የሚሆነውን ጥሬ ወርቅ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብቻ ገዝተው እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ መመርያ፣ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ ሊደረግ ነው፡፡
በአገሪቱ ውስጥ በወርቅ የሚሠሩ ጌጣጌጦችን በመሥራት ለገበያ የሚያቀርቡ ወርቅ ቤቶች፣ እስካሁን የሚጠቀሙበት ጥሬ ወርቅ ምንጭ የማይታወቅ በመሆኑና የወርቅ ግብይትን ሥርዓት ለማስያዝ ታስቦ የተዘጋጀው ይህ መመርያ፣ ማዕድን ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ ባንክና ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መሥሪያ ቤቶች በጥምረት የሚያስፈጽሙት ይሆናል፡፡
የማዕድን ሚኒስቴር የባህላዊ ማዕድናት ምርትና ግብይት ማስተባበሪያ ዋና የሥራ ሒደት አቶ ታምራት ሞጆ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መመርያው የወጣው የከበሩ ማዕድናት ግብይትን ለማስፋፋትና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ መሠረት ነው፡፡
በዚህ አዋጅ መሠረት ማንኛውም የወርቅና የጌጣጌጥ አምራች በየዕለቱ በብሔራዊ ባንክ ከሚደረግ ግብይት ላይ ከሚገዛው ወርቅ በተጨማሪ ምንጩ የማይታወቅ ወርቅ መጠቀም አይችልም፡፡ በአዋጁም ሆነ በመመርያው የወርቅ ግብይት ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊዎች ለሆኑት ሦስት አካላት ፈቃዶች ይሰጣሉ፡፡ ይህም የከበሩ ማዕድናት አዘዋዋሪነት ፈቃድ፣ የከበሩ ማዕድናት ዕደ ጥበብ ፈቃድና የከበሩ ማዕድናት ማጣራት ፈቃድ ናቸው፡፡
በዚህ መሠረት የከበሩ ማዕድናት ንግድ የብቃት ማረጋገጫ የተሰጣቸው ወርቅ ቸርቻሪዎች፣ የመጨረሻ ቅርፃቸውን የያዙ ወርቆችን በጅምላ ገዝተው በችርቻሮ በአገር ውስጥ የመሸጥ መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በአገሪቱ በየትኛውም ክልል ውስጥ ያሉ በወርቅ ችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩ ወርቅ ቤቶች፣ የመጨረሻ ቅርፅ የወጣላቸውን የወርቅ ምርቶች የሚገዙትም የከበሩ ማዕድናት ዕደ ጥበብ ፈቃድ ከተሰጣቸው ኩባንያዎችና ለዚህ ሥራ ብቁ ከሆኑ ወርቅ ቤቶች ብቻ ነው፡፡
የከበሩ ማዕድናት ዕደ ጥበባት ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች በአዋጁ መሠረት ከከበሩ ማዕድናት ተሠርተው የተባላሹ ወይም የተሰባበሩ ጌጣጌጦችን መጠገን ወይም በግዥ መሰብሰብ ይችላሉ፡፡ ሆኖም የክንውኑን ሁኔታ በተገቢው መመዝገብና ወቅታዊ ሪፖርት በየሩብ ዓመቱ የማቅረብ ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡ ለከበሩ ማዕድናት ዕደ ጥበባት ፈቃድ የወሰዱ ድርጅቶች ዋና ዋና ድንጋጌዎች መካከል፣ ከብሔራዊ ባንክ የገዙትን ወርቅ ለማኛውም ሰው ማስተላለፍ አለመቻላቸውና በእያንዳንዱ የጌጣጌጥ ምርታቸው ላይ ሊለይ የሚችል የራሳቸው የሆነ ምልክት ማድረግም ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡
የከበሩ ማዕድናት ንግድ ብቃት ማረጋገጫ የተሰጣቸው አካላት ከዕደ ጥበብ አምራቾች የሚረከቧቸው ምርቶች ተገቢው ምልክት እንዳላቸው ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ምልክት የሌላቸውን ጌጣጌጦች መግዛትም አይችሉም፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከዕደ ጥበብ አምራቾች ለችርቻሮ ንግድ የሚረከቧቸውን ምርቶች ይዞታቸውን መቀየር ወይም ከሌላ ማዕድናት ጋር መቀላቀል ካለመቻላቸውም በላይ ጥሬ የከበሩ ማዕድናትን ማዘዋወር አይችሉም፡፡
በዚህ መመርያ መሠረት በወርቅም ሆነ በከበሩ ማዕድናት ግብይት ፈቃድ የተሰጣቸው ሦስቱ አካላት፣ አንዱ የሌላውን ሥራ መሥራት አይችሉም፡፡ እንዲሠሩ ከተፈቀደላቸው ውጪ ሲንቀሳቀሱ ከተገኙ የፈቃድ ማረጋገጫቸው እንደሚሰረዝም ታውቋል፡፡
ይህ መመርያ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በዘርፉ የተሰማሩ ወርቅ ቤቶች በድጋሚ በመመዝገብ ማረጋገጫ እየወሰዱ ሲሆን፣ እስካሁንም በአዲስ አበባ ውስጥ 130 የሚሆኑ ወርቅ ቤቶች ፈቃዱን ወስደዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉትም በተመሳሳይ በየአገልግሎት ዓይነታቸው ማረጋገጫ እየተሰጣቸው ከብሔራዊ ባንክ ከተገዛ ወርቅ ውጪ የሚመረት ጌጣጌጥ መሸጥ አይችሉም፡፡
ብሔራዊ ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአገር ውስጥ ገበያ ወርቅ የመሸጥ ሥራውን በጥቂት ቀናት ውስጥ ሲጀምር፣ አንድ ፈቃድ ያለው ወርቅ ቤትና የዕደ ጥበብ ድርጅት ከብሔራዊ ባንክ የሚገዛው ዝቅተኛ የወርቅ መጠን 250 ግራም ሆኖ፣ በየዕለቱ የወርቅ ግብይቱ ይካሄዳል፡፡ የግብይቱ ዋጋም ግብይቱ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ በዕለቱ ከዋለው የወርቅ ዋጋ 0.5 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ ጨምሮ ይሸጣል፡፡
በመመርያው መሠረት የወርቅ ጌጣጌጥ የሚያመርቱ ዕደ ጥበባትም ሆኑ ወርቅ ቤቶች ምርታቸውን ለቸርቻሪ ሲያከፋፍሉና ሲሸጡ ምርቱን ለማን እንደሸጡ ሪፖርት የማቅረብ ግዴታም ተጥሎባቸዋል፡፡
እንደ አቶ ታምራት ገለጻ፣ ይህ መመርያ ተግባራዊ መደረጉ ከዚህ ቀደም በወርቅ ግብይት ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ያቃልላል፡፡ በተለይ የወርቅ ገዥዎች የሚሸጥላቸውን ካራት መጠን አለማወቃቸው አንድ ችግር ነበር፡፡
ይህንን መመርያ ተግባራዊ ለማድረግ ቀደም ብሎ በተደረገ ዝግጅት ወርቅ ቤቶች በእጃቸው ያለው ወርቅ ሕጋዊ ተደርጐ የተመዘገበላቸው ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ግን ከብሔራዊ ባንክ ከሚገዙት ወርቅ ውጭ ከሌላ ምንጭ በሚገኝ ጥሬ ወርቅ መሥራት እንደማይችሉ ተገልጾላቸዋል፡፡
ሆኖም ዕደ ጥበባት ከግለሰቦች የሚሰበስቡት ወርቅ ካለ ወዲያውኑ ሪፖርት ማቅረብ ግዴታ አለባቸው፡፡ መመርያውን ተግባራዊ ለማድረግ በተደረገ ቅድመ ዝግጅት ወቅት በአንዳንድ ወርቅ ቤቶች የተገኘ ጥሬ ወርቅ በወቅቱ በነበረ የገበያ ዋጋ ለብሔራዊ ባንክ እንዲሸጥ መደረጉም ታውቋል፡፡ እስካሁን በወርቅ ግብይት ውስጥ ያሉ ወርቅ ቤቶች የሚሸጡት ወርቅ ከየት እንደመጣ እንኳን የማይታወቅና ሕጋዊ መሠረት የሌለው እንደነበር የጠቆሙት አቶ ታምራት፣ የያዙት ወርቅ ሕጋዊ ነው እንዳይባል እንኳን ወርቅ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ፈቃድ የወሰደ ኩባንያም የለም፡፡ ስለዚህ በወርቅ ግብይት ውስጥ የታየውን ችግር በዚህ መመርያ መፍታት ይቻላል ይላሉ፡፡
"አዲሱን አሠራር ለመጀመር ሲባል የወርቅ ምንጩ ባይታወቅም በመመርያው ማረጋገጫ የተሰጣቸው በአዲስ አበባ ያሉ ወርቅ ቤቶች በእጃቸው የሚገኘውን ወርቅ መዝግበን ምዝገባው በተደረገበት ዕለት በነበረ የወርቅ ዋጋ መሠረት የባለንብረትነት መብት ተሰጥቷቸዋል፤" ብለዋል፡፡
እስካሁን ባለው መረጃ በዕደ ጥበብ ደረጃ የወርቅ ጌጣጌጥ ለማምረት ፈቃድ የወሰዱና የተዘጋጁ 14 ኩባንያዎች አሉ፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ለአገር ውስጥ ወርቅ ቸርቻሪዎች ከሚያቀርዋቸው የወርቅ ጌጣጌጦች በተጨማሪ፣ ያለቀለት የወርቅ ጌጣጌጥ ወደ ውጭ የመላክ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ ሆኖም ይህንን ለማድረግ ደግሞ ራሱን የቻለ ሌላ ፈቃድ እንደሚያስፈልጋቸው አቶ ታምራት አስረድተዋል፡፡
በአዲሱ መመርያ መሠረት እስካሁን ከማዕድን ሚኒስቴር ማረጋገጫ የተሰጣቸው በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ወርቅ ቤቶች ቁጥር 130 እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
Source: Reporter
No comments:
Post a Comment