Saturday, September 10, 2011

የአዲሱን ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ የተሰናዳ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ተጀመረ

(ጳጉሜን 2 ቀን 2003 (አዲስ አበባ, ኢዜአ) --የአዲሱን ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ የተሰናዳ የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል በብሔራዊ ቲያትር ትናንት ተጀመረ።

ጥበብ ኢትዮጵያ በተባለ ድርጅት ከቲያትር ቤቱ ጋር የተዘጋጀው ፌስቲቫል የኢትዮጵያን ጥበባት የመገምገምና የማሳደግ ዓላማ እንዳለው በፌስቲቫሉ መክፈቻ ላይ ተገልጿል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አሚን አብዱልቃድር በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ፌስቲቫሉ የኢትዮጵያን ባህልና ቱሪዝም በማስተዋወቅ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።

ፌስቲቫሉ የአገሪቱን ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በልዩነታቸው ውስጥ ያላቸውን አንድነት ለማሳየት እንደሚረዳም አመልክተዋል።

እንዲሁም የአገሪቱን ገጽታ ለመገንባት በማስቻል ጥበብ መጫወት ያለባትን በማጉላትም ሚናውን ሊጫወት እንደሚችልም ተወካዩ ተናግረዋል።

የጥበብ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አሰፋ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው ፌስቲቫሉ እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በፌስቲቫሉ የሙዚቃ፣ሲኒማ፣ሥነ ጽሁፍና ፍልስፍና ላይ ያተኮሩ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ከ ኢትዩዽያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment