Saturday, September 10, 2011

ቤተክርስቲያኗ የዝዋይን ገዳም ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል ስምምነት አካሄደች

ጳጉሜን 2 ቀን 2003 (አዲስ አበባ, ኢዜአ) - የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዝዋይ ሐይቅ ደሴት ላይ የተገኘውን ታሪካዊውን የደብረ ጽዮን ገዳም በቅርስነት ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችላትን ስምምነት ከሁለት ድርጅቶች ጋር ተፈራረመች።

ስምምነቱ የተፈረመው የቤተክርስቲያኗ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ ከዓለም አቀፍ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን በጎ አድራጊዎችና ከኢትዮጵያ ዘላቂ የቱሪዝም ቅንጅት ተወካዮች ጋር ነው።

የኮሚሽኑ ተወካይ ዶክተር አግደው ረዴ በዚሁ ወቅት ቱሉ ጉዶ በሚባለው ደሴት ከጥንት ጀምሮ የሚታወቀውን ታሪካዊ ቦታ ጠብቆ ለማቆየት ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል።

ስምምነቱ ታሪካዊ ቅርሶችን በማቆየት አገሪቱን ለማስተዋወቅ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ ኅብረተሰቡን ለማቀራረብና ቱሪስቶችን በመሳብ ረገድ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቀዋል።

በስምምነቱ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት መነደፉን የገለጹት ተወካዩ፣ የቅርሶችን አቀማማጥ አመቺ ለማድረግ፣ ለጎብኚዎች አመቺ በሆነ ሁኔታ ለማሻሻልና ጥበቃውንም ለማጠናከር የሚያስችል ሙዚየም ለመገንባት መታቀዱን ዶክተር አግደው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዘላቂ የቱሪዝም ቅንጅት የበላይ ኃላፊ ወኪል አቶ በድሉ ሸገን በበኩላቸው በቱሪዝም ኅብረተሰቡን በማሳተፍ ከጎብኚዎች በሚገኘው ገቢ በአካባቢ ልማት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ገዳሙ ታሪካዊነት ያለውና በቀጣይ ሬስቶራንት በመገንባት የአካባቢውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም ገልጸዋል።

ለዚህም ተፈፃሚነት የገዳሙን ሃብቶች ጠብቆ ለማቆየት የሚመለከታቸው አካላትና ኅብረተሰቡ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባቸው ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዩዽያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment