Monday, January 03, 2011

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት ቤተሰቦች ለደርግ ባለሥልጣናት ይቅርታ እንደማያደርጉ አስታወቁ

Sunday, 02 January 2011 11:08 
Source reporter: Reporter
በዘካሪያስ ስንታየሁ
በደርግ ባለሥልጣናት የተገደሉት ስድሳዎቹ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት ቤተሰቦች፣ ለደርግ መንግሥት ባለሥልጣናት ይቅርታ እንደማያደርጉ ባለፈው ሐሙስ ባወጡት መግለጫ ለአቡነ ጳውሎስ አስታወቁ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ የስድሳዎቹን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት ቤተሰቦችን በደርግ ባለሥልጣናት የይቅርታ ጉዳይ ላይ ሊያነጋግሯቸው በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ባለፈው ረቡዕ የቀጠሯቸው ቢሆንም፣ አቡኑ ከቁልቢ ገብርኤል ለቀጠሮው መድረስ ባለመቻላቸው፣ የቀጠሮው ቀን ወደ ሐሙስ ሊተላለፍ ችሏል፡፡
የስድሳዎቹ ባለሥልጣናት ቤተሰቦች ግን ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በሚገኘው የባለሥልጣናቱ የመታሰቢያ ሐውልት ተገኝተው ከተወያዩ በኋላ የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ቤተሰቦቹ የተስማሙበትን የአቋም መግለጫ ለአቡነ ጳውሎስ ሐሙስ ዕለት በፓትሪያርኩ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው አንብበውላቸዋል፡፡ በመግለጫው መሠረት፣ የደርግ ባሥልጣናቱን ይቅርታ በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠ ገደብ ስላለ ቤተሰቦቹ ይቅርታ ማድረግ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሕገ መንግሥት ገደብ በመኖሩ የሃይማኖት አባቶቹ እኛን አስማሙም፣ አላስማሙም፣ ገደቡን ማለፍ እስካልተቻለ ድረስ በዚህ ጉዳይ ይቅርታ ልትጠይቁን አትችሉም፤›› ሲሉም በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

‹‹ስለሆነም ለዚህ ጉዳይ ሕጉ ቀዳዳ ስለሌለው ራሱ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ደግሞ ረጅም ጊዜ ከመጠየቁም ባሻገር አስቸጋሪ ነው፤›› ሲሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቤተሰብ አባል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹የሃይማኖት መሪዎቹ የደርግ ባለሥልጣናትን ይቅርታ እንዲደረግላቸው እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን እኛ የሰማነው በጋዜጣ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ተቃውሟችንን በማሰማታችን አቡነ ጳውሎስ ሊያነጋግሩን ችለዋል፤›› ሲሉ ግለሰቡ ገልጸዋል፡፡

የስድሳዎቹ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣናት ቤተሰቦችም ለደርግ ሥርዓት ይቅርታ እንዲያደርጉና ብሔራዊ እርቅ እንዲሆን ከሆነ ሌላ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፣ የደርግ ባለሥልጣናቱ ወንጀለኛ ተብለው ፍርድ እየተፈጸመባቸው ባለበት ሁኔታ ለእነርሱ ይቅርታ ማድረግ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም አቡነ ጳውሎስ የተጎጂዎቹ ቤተሰቦች በእግዚአብሔር ስም ይቅርታ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን እኚሁ ግለሰብ ገልጸዋል፡፡

የባለሥልጣናቱ ቤተሰቦቹ ለአቡነ ጳውሎስ ያስተላለፉትን የአቋም መግለጫ አንብበው ከተወያዩ በኋላ፣ በጉዳዩ ላይ በስፋት ለመወያየት ከጥምቀት በዓል በኋላ ለመገናኘት ተስማምተው ተለያይተዋል፡፡
 

No comments:

Post a Comment