Monday, January 03, 2011

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተሳፈሩበት አውሮፕላን አደጋ አጋጥሞት ነበር

Sunday, 02 January 2011 12:22 
Source reporter:  
በሆቴላቸው ለስድስት ሰዓታት ቆይተዋል
በዘካሪያስ ስንታየሁ
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከቡርኪናፋሶ ዋና ከተማ ኡጋዱጉ ወደ አዲስ አበባ ያመሩበት የነበረው አውሮፕላን አደጋ ገጥሞት እንደነበር ታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ታኅሣሥ 10 ቀን 2003 .. የቡርኪናፋሶ ፕሬዚዳንትን ብሌስ ኮምፖኦሬ በዓለ ሲመት ሊታደሙ ያመሩ ሲሆን፣ የሁለት ቀናት የሥራ ቆይታ ካደረጉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የአውሮፕላኑ የፊት መስታወት በደረሰበት ጉዳት ምክንያት በግዳጅ ሊያርፍ ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 አውሮፕላን የፊት ለፊት መስታወት ሙሉ ለሙሉ በመሰነጣጠቁና ይህም ለጉዞው አደገኛ በመሆኑ፣ አውሮፕላኑ ከተነሳ ከደቂቃዎች በኋላ ተመልሶ አርፏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም አውሮፕላኑ እንዳረፈ ወርደው አርፈውበት ወደነበረው ኡጋዱጉ ሒልተን ሆቴል አምርተዋል፡፡ ከስድስት ሰዓታት ቆይታ በኋላ በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር የነበረ ሌላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 767 የመንገደኞች አውሮፕላን ጠቅላይ ሚኒስትሩን አሳፍሮ አዲስ አበባ በሰላም ገብቷል፡፡

አውሮፕላኑ በፊት መስታወቱ ላይ በተፈጠረ ብልጭታ ምክንያት መስታወቱ እንደተሰነጣጠቀ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አውሮፕላኑ 8000 ጫማ ላይ ይበር የነበረ በመሆኑ አደጋ ሳይገጥመው በሰላም ማረፍ ችሏል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት ወጋየሁ ተረፈን ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው፣ እንደዚህ ዓይነት መረጃ የሌላቸው መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሊገጥሙ ይችላሉ ብለዋል፡፡ ጉዳዩንም አጣርተው ምላሽ እንደሚሰጡን ቢገልጹልንም፣ ሕትመት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ ምላሻቸውን ማግኘት አልቻልንም፡፡ (ለዚህ ዘገባ ይበቃል ጌታሁን አስተዋጽኦ አድርጓል).

No comments:

Post a Comment