(Aug 25, (አዲስ አበባ))--በፖለቲካ ትኩሳት የሚሸፈነው ኢኮኖሚያዊ ችግር በጊዜ መላ ካልተፈለገለት የቀውሶች ሁሉ እናት ሊሆን ይችላል፡፡ ለፖለቲካዊ ጥያቄዎችና አለመግባባቶች በጋራ መፍትሔ እያቀረቡና እየተደራደሩ፣ አገሪቱን ከተቆለለባት የዕዳ ጫና በፍጥነት የሚያላቅቅ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ሥርዓት መዘርጋት የግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ወጣት የሰው ኃይል፣ ለግብርና አመቺ የሆነ መጠነ ሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ አንደኛ የሆነ የእንስሳት ሀብት፣ ክረምት ከበጋ የማይነጥፍ ትልቅ የውኃ ምንጭ፣ ለግብርና አመቺ የሆኑ የተለያዩ የአየር ፀባዮች፣ የቱሪዝም መስህቦችና የተለያዩ ማዕድናት ባለቤት ናት፡፡ በኋላቀርና በብልሹ አሠራሮች ምክንያት ታላቅ የተፈጥሮ ፀጋ ታቅፎ መደህየት ኃጢያት ነው፡፡
መሠረታዊ የሆነ የመዋቅር ለውጥ አድርጎ የአገሪቱን ወጣቶች፣ ምሁራንና ባለሙያዎችን በማንቀሳቀስ ለዘመናት ከተዘፈቁበት ድብርት ውስጥ መውጣት የግድ ነው፡፡ በደካማ ቢሮክራሲና ብቃት በሌላቸው ተሿሚዎች ሳቢያ አገር የድህነትና የልመና ተምሳሌት መሆን የለባትም፡፡ መሥፈርቱና ልኬቱ በማይታወቅ ዕቅድ የሚመሩ የኤክስፖርትም ሆነ የኢንቨስትመንት ተግባራት ተወግደው፣ በበቂ ጥናትና ምርምር የታገዙ አሠራሮች መስፈን አለባቸው፡፡ አሁን በሚታየው አኳኋን መዝለቅ አይቻልም፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣው የአገር ውስጥና የውጭ ብድር ዕዳ ያስጨንቃል፡፡ ይህንን ችግር በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ ፕራይቬታይዜሽን አስፈላጊ በመሆኑ፣ የተወሰኑ የመንግሥት የልማት ድርድቶችን በከፊልና በሙሉ ለሽያጭ ለማቅረብ ዝግጅቱ እየተከናወነ ነው፡፡ ችግር ሲያጋጥም የተወሰነ ንብረት ሸጦ ማገገም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን የፕራይቬታይዜሽኑ ሒደት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ሲሆን፣ የሚያስገኘው ጠቀሜታም የሚያግባባ መሆን አለበት፡፡
አትራፊዎቹን ከአክሳሪዎች በመለየት ጥሩ ዋጋ ማግኘትም የግድ ይሆናል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ንግድና ኢንቨስትመንት በሚገባ እንዲቀላጠፉ የሚያግዙ ዕርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ አስተማማኝ የሆነ ሰላም በማስፈን የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን በራስ የመተማመን ስሜት ማዳበር ተገቢ ነው፡፡ በቢሮክራሲውም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ አደረጃጀቶች በኢንቨስተሮች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችና አሉታዊ ድርጊቶች በፍጥነት መቆም አለባቸው፡፡ ማምረት ያቆሙ ወይም በከፊል የቀነሱ በሙሉ ኃይላቸው እንዲሠሩ ከፍተኛ ዕገዛ መደረግ አለበት፡፡ በተጨማሪም ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ የሚያግዙ ድጋፎች በአግባቡ ሥራ ላይ ሊውሉ ይገባል፡፡ ገንዘብ ስለተመደበ ብቻ ሜዳ ላይ መዝራት ሳይሆን፣ ዕቅዱ በአግባቡ ሥራ መፍጠር ማስቻል አለበት፡፡ ከገጠር እስከ ከተማ ሰዎች ሥራ ላይ እንዲገኙ የሚያስችሉ የልማት ፓኬጆች ተግባራዊ መደረግ አለባቸው፡፡ ይህንን ማድረግ አለመቻል መዘዙ የከፋ ነው፡፡
መንግሥት ባለበት ኃላፊነት መሠረት የንግድና የግብይት ሥርዓቱን መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ይህ ማለት ገበያው ውስጥ ዘው ብሎ ገብቶ ዋጋ ይወስን ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የንግድና የግብይት ሥርዓቱ ተዋንያን (መንግሥት፣ ሸማቹና ነጋዴው) ሊናበቡ ይገባል፡፡ የአገሪቱን ንግድ ጥቂት አምራቾች፣ አስመጪዎችና አከፋፋዮች በቁጥጥር ሥር አውለውት ንግዱ የደላላ መጫወቻ ሲሆን፣ ሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት እየተፈጠረ የዜጎች ሕይወት ይመሰቃቀላል፡፡
በእህል፣ በጥራጥሬ፣ በመሠረታዊ የፍጆቻ ዕቃዎች፣ በእንስሳት ተዋፅኦ፣ በቤት ኪራይ፣ ወዘተ የደላሎች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የዋጋ ግሽበቱ ከሚታገሱት በላይ እየሆነ ነው፡፡ የምርቶችና የአገልግሎቶች የመነሻ ዋጋና የትርፍ ህዳግ ባለመኖሩ ምክንያት ብቻ፣ የግብይት ሥርዓቱ የበላይነቱን በያዙት ነጋዴዎችና ደላላዎች እጅ ወድቋል፡፡ ጠንካራ የሸማቾች ማኅበራትና አስፈጻሚ ተቋማት ባለመኖራቸው ምክንያት፣ ከሚዛን ጀምሮ እስከ ምርት ጥራት ድረስ ያለው ችግር በጣም እየከበደ ነው፡፡ የሸማቾች የመግዛት አቅም ከመቼውም ጊዜ በላይ እየወረደ በመሆኑ፣ ጥራት የሌላቸውና ለጤና አደገኛ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ያሉባቸው አደገኛ ምርቶች ገበያውን ወረውታል፡፡ በአጠቃላይ ይህ አሳሳቢ ሁኔታ የመንግሥትንም ሆነ የሚመለከተውን አካላት ብርቱ ጥረት ይፈልጋል፡፡ ያለ በለዚያ ነገሮች እየከበዱ የማይወጡት ችግር ውስጥ ይከታሉ፡፡
የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮችም ሆኑ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል፡፡ የአስመጪነት ፈቃድ በማውጣት ለቁጥር የሚያታክቱ የውጭ ምርቶችን ለማግበስበስ በቁጥቁጥ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ላይ ከመረባረብ፣ በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የሚያስችሉ ማምረቻዎችን በአክሲዮን ማኅበራት ለማቋቋም መነሳት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም መንግሥት ጉድለት ያለባቸውን ፖሊሲዎቹንና ስትራቴጂዎቹን አስተካክሎ ዝግጁ እንዲሆን፣ በንግድ ምክር ቤቶችና በማኅበራት አማካይነት የሕግ ማዕቀፎች እንዲወጡ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
አገር የምታድገው ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ሳይሆን፣ በአገር ውስጥ ተመርተው ለውጭ ገበያ ጭምር መትረፍ ሲቻል ነው፡፡ ኢትዮጵያን የመሰለች በተፈጥሮ የታደለች አገር ይዞ በስንዴ፣ በስኳር፣ በቅባት እህሎች፣ በቡና፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአበባ፣ በጥራጥሬና በመሳሰሉት ከፍተኛ የሆነ የኤክስፖርት ገቢ ማግኘት እየተቻለ በአስመጪነት ንግድ ፈቃድ መኩራራት ያሳፍራል፡፡ ከግብርና ምርቶች በተጨማሪ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በቀላልና በመካከለኛ የፋብሪካ ምርቶች፣ በግብርና መሣሪያዎች፣ በተሽከርካሪዎች፣ በቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች፣ በዕደ ጥበባትና በመሳሰሉት ጭምር ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህንን በፍጥነት ወደ ተግባር መለወጥ ካልተቻለ መጪው ጊዜ ከባድ ነው፡፡
የኢኮኖሚው ጉዳይ ያሳስባል፡፡ ሥራ ከሌለ ገቢ የለም፡፡ ገቢ ከሌለ አማራጩ ዝርፊያ ውስጥ መግባት ነው፡፡ ዘረፋ የሥርዓተ አልበኝነት መገለጫ ከመሆኑም በላይ፣ ወደ ቀውስ የሚያንደረድር አደገኛ መንገድ ነው፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ ሌሎች የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉ፣ የኢኮኖሚው ሁኔታ ትልቅ ትኩረት እንደሚያስፈልገው መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ወጣቱ ሥራ ያስፈልገዋል፡፡ ኢንቨስተሮች የተረጋጋና ሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ይፈልጋሉ፡፡ በኑሮ ውድነት ምክንያት ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ወገኖች የተሻለ ሕይወት መምራት ይፈልጋሉ፡፡
ልጆቻቸውን ጥሩ መመገብ፣ ጥሩ ቤት ውስጥ ማኖር፣ ጥሩ ትምህርት ቤት አስተምረው ለወግ ማዕረግ ማብቃት የብዙዎች ጉጉት ነው፡፡ ይህ ሊሳካ የሚችለው የፖለቲካው ግለት ቀንሶ ኢኮኖሚው ላይ መረባረብ ሲቻል ነው፡፡ ዕዳ አናት ላይ ተሸክሞ መጨቃጨቅ፣ መጋጨትና ትርምስ ውስጥ መግባት ቀውሱን ያባብሰዋል እንጂ መፍትሔ አያመጣም፡፡ ይልቁንም የሕግ የበላይነት ተከብሮ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የምትመች አገር ለመገንባት በጋራ መነሳት ይሻላል፡፡ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው አገራዊ ጉዳዮች በመጨነቅ፣ ኢትዮጵያ ካለችበት አጣብቂኝ ውስጥ እንድትወጣ ርብርብ ይደረግ፡፡ አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ወደ ቀውስ የሚንደረደረውን ኢኮኖሚ ለመታደግ የሚያስችሉ መላዎችን ወዲህ ይበሉ፡፡ የኢኮኖሚውን ነገር አደራ!
በጋዜጣዉ ሪፓርተር

No comments:
Post a Comment