(Jul 07, (አዲስ አበባ, (ሪፖርተር) ))--የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር የሚያስተናግዳቸው ፓርቲዎችና ስብስቦች በተለያዩ ፈርጆች የሚገለጹ ናቸው፡፡ ለፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ብቃት ይኖራቸዋል ተብለው ከሚታሰቡት ጀምሮ፣ ለዘመኑ አስተሳሰብ የማይመጥኑ ጭምር ታጭቀውበታል፡፡
በቤተሰብ አባላት ከተደራጁት ጀምሮ ጊዜያዊ ዓላማ ያቆራኛቸውም አሉ፡፡ እጅግ በጣም ጥቂት የሚባሉት ካልሆኑ በስተቀር ለአቅመ ፖለቲካ ያልደረሱ፣ ወይም የፖለቲካ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማጋበሻ ለማድረግ የተሠለፉም ይገኛሉ፡፡ የአዋቂ አጥፊ የሚባሉት ደግሞ የዓመታት ቁርሾና ቂማቸውን ይዘው የጎሪጥ እየተያዩ፣ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ያደባሉ፡፡ ይህንን የመሰለ የፖለቲካ ምኅዳር ይዞ በኢትዮጵያ ምድር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እንዴት እንደሚቻል ግራ ያጋባል፡፡
በግለሰቦች ደረጃ በጥርጣሬ፣ በመፈራራትና በመጠፋፋት አባዜ የተወጠረው ግንኙነት ወደ ፓርቲዎቹ እየተጋባ፣ እንኳንስ አብሮ ለመሥራት ይቅርና በቅጡ መተያየት አልተቻለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በአንድ ፓርቲ ውስጥ የሚከሰቱ አሻጥሮችና ሴራዎች በራሳቸው አንጃ እየፈጠሩ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕድሜ በአጭሩ ይቀጫል፡፡ ይህም በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ተሁኖ ተባብሮ አገር መገንባት ከባድ ነው፡፡ ይህንን አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ መዝጋት ያስፈልጋል፡፡
ግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ያስቆጠረውና ዘመናዊ የሚባለው የአገሪቱ ፖለቲካ በበርካታ መስኮች ወደ ኋላ የቀረ ነው፡፡ የየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት በግብታዊነት ከፈነዳ በኋላ የገጠሙ ችግሮች ምስክሮች ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ደርግ፣ መኢሶንና ኢሕአፓ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት አቅቷቸው ለአንድ ትውልድ ዕልቂት፣ እስራት፣ ስደትና ሥቃይ ሰበብ ሆነዋል፡፡ ግራ ዘመም ሆነው ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን በኢትዮጵያ ለማስፈን ተነስተናል ያሉት የዚያ ዘመን ሰዎች፣ ቀጫጭን ልዩነቶችን አጥብበው በሙሉ ኃይል መተባበር ሲገባቸው ተፋጁ፡፡
ሌላውንም አስፈጁ፡፡ በመላ አገሪቱ ድንዛዜ በመፍጠር በፍርኃት ቆፈን ውስጥ የሚኖር ማኅበረሰብ ፈጠሩ፡፡ ኢሕአዴግ በትጥቅ ትግል በ1983 ዓ.ም. ሥልጣነ መንበሩን ሲቆጣጠር በሽግግሩ መንግሥት ተሳታፊ መሆን የሚገባቸውን በማግለሉ፣ ተስፋ የተጣለበትን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውኃ ቸለሰበት፡፡ ይባስ ብሎ በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ የታሰበውን ተስፋ የበለጠ አጨለመው፡፡ አፋኝና አስደንጋጭ ሕጎች በማውጣት ምኅዳሩን ዘጋጋው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ በቀሪዎቹ ምርጫዎች መቶ በመቶ ፓርላማውን ተቆጣጠረ፡፡ ውጤቱ ምን ሆነ ሲባል መልሱ ሕዝባዊ አመፅ ነው፡፡ በሕዝባዊ አመፁ ደም ፈሶ ኢሕአዴግ ውስጥ ባሉ ኃይሎች አማካይነት በከፍተኛ ትግል ለለውጥ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ጉዞው ግን ከብዷል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው አዲሱ አስተዳደር በርካታ ሺሕ እስረኞችን በመፍታት፣ በጎረቤት ኤርትራ ትጥቅ አንስተው የነበሩ ኃይሎችን ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ በማድረግ፣ በተለያዩ አገሮች በስደት የነበሩትን ጭምር በመመለስ፣ ለለውጡ ይረዳሉ የተባሉ በርካታ ሕጎችን በማሻሻል፣ የሐሳብ ነፃነትን ከመቼውም ጊዜ በላይ በማክበር፣ ወዘተ. አዎንታዊ ዕርምጃዎችን ቢወስድም ፈተናው ግን ጨምሯል፡፡ የአገሪቱን የዘመናት ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ የሚገባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅፋት ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሳይቀሩ፣ የተግባርና የዓላማ አንድነት አጥተው ይተነኳኮሳሉ፡፡
በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ደረጃ በጋራ ወስነው ከወጡ በኋላ በየፊናቸው የተለያዩ መግለጫዎች ያወጣሉ፡፡ ከውጭ ከመጡት ውስጥ ደግሞ ትጥቅ ይዘው የሚፎክሩም የሚተኩሱም አሉ፡፡ ለሰላማዊ ትግል ነው ፖለቲካ ውስጥ የገባነው የሚሉት ደግሞ፣ ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውር ውስጥ ያሉ ይመስል በየደረሱበት ሕዝቡን ያስታጥቃሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዓይን ያወጣ አሳፋሪ ድርጊት ሲፈጸም ሰብሰብ ብለው፣ ድርጊቱን በማውገዝ መግለጫ የሚያወጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማየት አይቻልም፡፡ በየጎሬያቸው እያደቡ የወደቀ ሥልጣን ለማግኘት የሚቃትቱ የበዙ ነው የሚመስለው፡፡ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ማሰብ አልተቻለም፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ የፖሊሲ ማመንጫ የክርክር መድረኮች፣ የነጠሩ ሐሳቦች መፍለቂያና የሥልጡን ፖለቲካ ማራመጃ መሆን ሲገባቸው፣ በአገሪቱ ምንም እንዳልተፈጠረ እንቅልፋቸውን ከሚለጥጡት ጀምሮ የሴረኞች መጠለያ ሆነዋል፡፡ በውስጣቸው ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ማስፈን ያልቻሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንኳን የተሻለ አጀንዳ ሊያመነጩ፣ አባሎቻቸውን የአሉባልታና የሴራ ፖለቲካ ትንተና ሰለባ አድርገዋቸዋል፡፡
በሚቀጥለው ዓመት ሊደረግ ይችላል ተብሎ ለሚታሰበው ምርጫ ምን ያህሎቹ እየተዘጋጁ ነው ቢባል፣ ምላሹ እንዲያው ዝም ነው ከማለት የዘለለ አይሆንም፡፡ አክቲቪስት የሚባሉ ግለሰቦችን ሩብ ያህል ተደማጭነት የሌላቸው ከ100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ ተብሎ ሲነገር ቀልድ ይመስላል፡፡ በአገር ላይ መቀለድ፣ በሕዝብ ላይ ማሾፍ ነው፡፡ ድምፃቸውን አጥፍተው እየተዘጋጁ ያሉ በጣም ጥቂት ፓርቲዎች መኖራቸው መዘንጋት ባይኖርበትም፣ የብዙዎቹ ጉዳይ ግን ያንገሸግሻል፡፡ ወይ አይጣመሩ፣ ወይ አይዋሀዱ፣ ወይ በየራሳቸው ጠንካራ ሆነው አይወጡ በሕዝብና በአገር ላይ ይቀልዳሉ፡፡ ለዚህ ነው ግራ ተጋብተው ግራ ከሚያጋቡ ይሰውራችሁ የሚባለው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብና የአገራቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን በማነቃነቅ ይህ የሽግግር ጊዜ በሰላም ተጠናቆ ለነፃ፣ ለዴሞክራሲያዊ፣ ለፍትሐዊና ለእውነተኛ ምርጫ ለመብቃት በቁርጠኝነት መሥራት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰላም እንድትሸጋገር፣ የሕግ የበላይነት የሁሉም ነገር ምሰሶ እንዲሆን፣ ፍትሕ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ተደራሽ እንዲሆን፣ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሴረኝነትና በቀልተኝነት እንዲወገዱና መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን ይህንን የለውጥ ጉዞ ይደግፉ፡፡
ስህተት ሲፈጸም እያረሙ፣ አድልኦ እንዳይኖር እየታገሉ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲመሠረት አርዓያ እየሆኑ፣ ጥቅም የሌላቸው ሥራ አስፈቺ ወሬዎችና አሉባልታዎች ተወግደው የውይይትና የክርክር ባህል እንዲጎለብት ምሳሌ በመሆን፣ ወዘተ. ኃላፊነታቸውን ይወጡ፡፡ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር የሚያስፈልገው ጠመንጃ ሳይሆን፣ የነጠረ የሐሳብ የበላይነት መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡
ሰላማዊው ፖለቲካ የሕገወጦችና የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ እንዳይሆን መተባበር የግድ መሆን አለበት፡፡ ወገን የገዛ ወገኑን እየገደለ የሚኩራራበት፣ ወይም ጠመንጃ ታጣቂ የሚመለክበት ሥርዓት ከኢትዮጵያ መወገድ ይኖርበታል፡፡ አምባገነንነት የሕዝብና የአገር ፀር ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ከመፈራራት ወደ መተባበር ይሸጋገር!
ሪፖርተር

No comments:
Post a Comment