Sunday, December 09, 2018

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሆይ አብሮ መሥራትን ተለማመዱ!

(Dec 09, (Addis Ababa))--የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጡዘት ውጤት የሆነው መከፋፈል፣ መበታተንና እንዳይሆኑ ሆኖ መቅረት ምክንያቱ ጽንፈኝነት ነው፡፡ የተለያዩ ዓላማዎች ይዞ ለጋራ ጉዳይ አብሮ መሥራት ብርቅ የሆነበት የአገሪቱ ፖለቲከኞች ልማድ፣ ለጽንፈኝነት በጣም የተጋለጠ ከመሆኑ የተነሳ ከወዳጅነት ይልቅ ጠላትነትን ያበረታታል፡፡ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ እያስቆጠረ ባለው የአገሪቱ ዘመናዊ ፖለቲካ ውስጥ ተዋናይ የሆኑ ግለሰቦች፣ እንደ ውርስ እየተቀባበሉት ያለው ይህንኑ አጉል ልማድ ነው፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ 14 የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ ፎረም አቋቁመው በጋራ ለመሥራት መወሰናቸው ተሰምቷል፡፡

ቀደም ሲል እነዚህ የፖለቲካ ድርጀቶች በተቻለ መጠን ተቀራርበው እንዲነጋገሩ፣ ከተቻለም የሚመሳሰሉት ተዋህደው ጠንክረው እንዲቀርቡ ማሳሰቢያ የሚሰጡ ነበሩ፡፡ ይህ በሒደት የሚከናወን ጉዳይ እንደ መሆኑ መጠን፣ ክልሉ የግጭት መናኸሪያ ሆኖ ንፁኃን ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉና ንብረት ሲወድም ፖለቲከኞች እንደ እባብ ካብ ለካብ መተያየታቸው ለማንም አይጠቅምም፡፡ እንደተባለው በመደማመጥና በመወያየት ችግሮችን ለመፍታት እዚህ ደረጃ ላይ መደረሱ ሊደገፍ ይገባዋል፡፡ ሌሎችም ይህንኑ ፈለግ ቢከተሉ ይጠቀማሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የገሚባ ጉዳይ ሰላምና መረጋጋት ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ደግሞ ከማንም በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች በግንባር ቀደምትነት መገኘታቸው የግድ ይሆናል፡፡ ሰላምና መረጋጋት የሚሰፍነው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ቁርጠኛ አቋም ኖሯቸው ከፀብ አጫሪ ድርጊቶች ሲታቀቡ ነው፡፡

መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሲንቀሳቀስም በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን ብቻ በመጠቀም መሆን ይኖርበታል፡፡ መጪውን ምርጫ በተሳካ መንገድ ለማከናወን የሚቻለው ሰላም በአስተማማኝነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከል ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ መንገዱን ማመቻቸት፣ የፖለቲካውን የጨዋታ ሕግ ማሳመር፣ ከአመፃና ከሕገወጥነት መራቅ፣ ለብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ተፃራሪ የሆኑ ድርጊቶችን መመከት፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተሟልተው እንዲከበሩ ማድረግና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት አብረው እየሠሩ መፎካከር የሥልጣኔ መገለጫ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከሚያሳስባት ሥጋት ወደ ተስፋ መሸጋገር የምትችለው የፖለቲካ ፓርቲዎችና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት መጣል ሲጀምሩ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከዘመናት ቂምና ጥላቻ ውስጥ በፍጥነት መውጣት ሲቻል ነው፡፡ አንዱ በሌላው ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄደና ጠልፎ የመጣል ሴራ እየተተበተበ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት አይቻልም፡፡ ለሁሉም እኩል የሆነ የፖለቲካ ምኅዳር መኖር የሚችለው ለአገር የጋራ ጉዳይ አብሮ መሥራት ሲቻል ነው፡፡

በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ በጠላትነት እየተፈራረጁ መፈላለግም ሆነ፣ አሰልቺ በሆነ ፕሮፓጋንዳ በነገር እየተቋሰሉ ሕዝብ መበጥበጥና አገር ማተራመስ ሊበቃ ይገባል፡፡ ኋላቀሩና ዘመን ያለፈበት የጠላትነት ፖለቲካ ትርፉ ውድመት ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ እየኖሩ በዘመነ መሳፍንት አስተሳሰብ አገር ማመስ ጤነኝነት አይደለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝብ ፍላጎት ታዛዥ ሆነው ሲንቀሳቀሱ ሴራ፣ አሻጥር፣ ቂም በቀል፣ ጥላቻና የመሳሰሉት ከንቱ ድርጊቶች ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡


በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚስተዋሉ ሰው ሠራሽ ችግሮችን በሰከነ መንገድ ማቃለል ወይም ማስወገድ የሚቻለው፣ ከምንም ነገር በላይ ለሕዝብ ደኅንነትና ለአገር ህልውና ተባብሮ በመሥራት ነው፡፡ ይህንን ዕውን ለማድረግ ደግሞ ቅን መሆን ይገባል፡፡ ይህ ቅንነት ግን አስተዋይነትን የሚሻ በመሆኑ፣ በአጉል ብልጣ ብልጦች በሌላ መንገድ እንዳይተረጎም ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ አገሩ ከሥጋት ወደ ተስፋ እንድትሸጋገር ፅኑ ፍላጎት ስላለው፣ እያንዳንዱ ፖለቲከኛና የፖለቲካ ድርጅት ምን እንደሚያከናውን ያውቃል፡፡

በተለይ የፖለቲካ ድርጅቶችን መልካም ግንኙነት ለማሻከር የሚፈልጉ ወገኖች፣ ቅንነትን እንደ ሞኝነት ሊያዩት ስለሚችሉም ነቃ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ እየተገባ መካረርና ለመጠፋፋት መፈላለግም ሆነ፣ ለፋይዳ ቢስ እልህና ግትርነት ሰፊ ጊዜ መስጠት የሚጎዳው ሕዝብና አገርን ነው፡፡ በብልኃት ክፉ ጊዜን መሻገር ሲቻል አገርን ችግር ውስጥ በመክተት ሕዝብን ለሰቆቃ መዳረግ በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ ለዚህም ሲባል ነው ፖለቲከኞች ከአጓጉል ተግባራት መታቀብ አለባቸው የሚባለው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተለመደው አዙሪት ውስጥ መውጣት አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ፉክክር የሚኖረው ለአቅመ ዴሞክራሲ መብቃት ሲቻል ነው፡፡ ለተፎካካሪ ክብርና ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲከኛ ወይም የፖለቲካ ድርጅት ቅርበቱ ለአምባገነንነት እንጂ፣ ለሥልጡን ፖለቲካና ለነፃ ምርጫ አይደለም፡፡ አሁንም በቅጡ ማሰብ የሚገባው ሌላው ቢቀር እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ አገሪቱ የገጠማትን ፈተና እንዴት በብልኃት ማለፍ እንደሚቻል ነው፡፡

ዴሞክራሲን መለማመድ የሚቻለው ለሰላምና ለመረጋጋት ቅድሚያ በመስጠት ሲሆን፣ በዚያ ቁመና ላይ ለመገኘት ደግሞ ራስን ማብቃት የግድ ይላል፡፡ የሞራልና የሥነ ምግባር ልዕልና ያለው ፖለቲከኛ አይታበይም፣ ለሕዝብና ለተፎካካሪዎቹ ክብር ይሰጣል፣ የዴሞክራሲ መሠረታዊ ምሰሶዎችን ይገነዘባል፣ ለሰላምና ለመረጋጋት ዘብ ይቆማል፣ በአገር ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም አይደራደርም፣ ሰላማዊውን የፖለቲካ ትግል አያደፈርስም፣ ወዘተ. . .፡፡

 ከዚህ በተቃራኒ በሕዝብ ስም እየነገዱ አገርን ቀውስ ውስጥ መክተት የከሰሩ ፖለቲከኞች ሥራ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማሸጋገር የሚቻለው በጉልበት ሳይሆን በሥልጡን ውይይት፣ ክርክርና ድርድር ብቻ ነው፡፡ ሥልጣን ከጠመንጃ አፈሙዝ ለማግኘት የማይቻል ብቻ ሳይሆን የማይታሰብ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ሕግና ሥርዓት እየጣሱ እንዳሻህ ለመሆን መሞከር ያስወግዛል፡፡ ካሁን በኋላ ገድሎ መፎከርም ሆነ ጠመንጃ እየወለወሉ ማስፈራራት አይቻልም፡፡ ለአገር የጋራ ጥቅም እየተመካከሩ በሠለጠነ መንገድ መፎካከር ግን ያስከብራል፡፡ ዘመኑ የሚፈልገው ይህንን ነው፡፡ ስለዚህ ፖለቲከኞች ሆይ አብሮ መሥራትን ከወዲሁ ተለማመዱ! በባዶ ሜዳ አትጠማመዱ!  
ሪፖርተር (ርዕሰ አንቀጽ )

No comments:

Post a Comment