Saturday, May 09, 2015

ሊቢያ የነበሩ 42 ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ገቡ

(ግንቦት 1/2007, (አዲስ አበባ))--በሊቢያ የነበሩ ዜጎች ወደ አገር ቤት በሚመለሱበት ሶስተኛው ዙር ጉዞ 42 ስደተኞች ዛሬ አዲስ አበባ ገቡ። መንግሥት በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ከመመለስ በተጨማሪ ራሳቸውን አደራጅተው ህይወታቸውን መለወጥ እንዲችሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።



ከተመለሾቹ መካከል በርካታውን ቁጥር የያዙት ወጣት ሴቶች ናቸው። አዲሱ ደገፋ ይባላል። ከሶስት ዓመታት በፊት በደላላ አማካኝነት ወደ ሊቢያ እንደሄደና በአሁኑ ወቅት በሊቢያ መረጋጋት እንደሌለ ይናገራል።

ከጉራጌ ዞን የሄደችው ሌላዋ ተመላሽ ጤናዬ ታደሰ ደላሎች አሳስተው ሊቢያ እንዳስገቧትና ለአንድ ባለሃብት በነጻ ስታገለግል መቆየቷንና ለሶስት ወራት መታሰሯንም ትገልጻለች።

"ብዙ መከራና ችግር አሳልፈናል ብዙዎች ሞተዋል፣ እኔም ተገፍቻለሁ እንደ ሰው አልታየም ነበር፣ ፤ አሞኝ እንኳን ሃኪም ቤት ሳልሄድ ለብዙ ቀን ደም እየፈሰሰኝ ህመሜን ችዬ ኖሬያለሁ" በማለት ተናግራለች። ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመላሾች ወደ አገር ቤት ለመመለስ ለሚፈልጉ በሚዲያ የተላለፈውን ስልክ ቁጥር በማግኘትና በፌስቡክ በመፃፃፍ ለዚህ እንደበቁ ገልጸዋል።

ይሁንና አሁንም በርካታ ኢትዮጵያዊያን በአሰሪዎቻቸው ቤት ተቆልፎባቸው መውጣት እንዳልቻሉ ነው የጠቆሙት። መንግሥት እነሱን በመረዳት ያደረገውን ድጋፍ ለእነዚህ ዜጎችም በማድረግ ከችግር እንዲወጡ ጥረት ያድርግ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ መንግሥት ችግር ባለባቸው አገራት የሚኖሩ ዜጎችን ለማስወጣት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል። የዛሬዎቹን ጨምሮ እስካሁን የተመለሱትም በመንግሥት በተደረገው ጥረት መሆኑንና ይኸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ዜጎች ካሉበት ችግር እንዲወጡ ከማድርግ ባሻገር ራሳቸውን አደራጅተው ህይወታቸውን መለወጥ እንዲችሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ነው ያሉት።   የዛሬውን ጨምሮ በሶስት ዙሮች በተደረገው ጉዞ ከ80 በላይ ኢትዮጵያውያን ከሊቢያ ወደ አገራቸው ገብተዋል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

No comments:

Post a Comment