Sunday, April 12, 2015

ትንሳኤን በመተሳሰብና በመረዳዳት ማክበር ይገባል

(ሚያዚያ 3/2007, (አዲስ አበባ))-- ህዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር በመተሳሰብና በመረዳዳት ሊሆን እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

የኢትዮጵያን ሠላም ለማስጠበቅና የጀመረችውን ልማት ለማፋጠን ሁሉም በአንድነት ሊሰለፍ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። የኃይማኖት አባቶቹ የ2007 ዓ.ም የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓልን አስመልተው የእንኳን ደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንዳሉት "ኢትዮጵያ በባህል፣ በመልካም ሥነ-ምግባር፣ በጸና ኃይማኖትና እውነተኛ ትውፊት የምትታወቅ አገር ናት"።

"አገሪቱ ከምትታወቅባቸው ዋነኛው፤ አብሮነት፣ መቻቻል፣ መረዳዳትና መደጋገፍ በመሆኑ የትንሣኤን በዓል ስናከብር የተራበውን በማብላት፣ የተጠማውን በማጠጣት፣ የታረዘውን በማልበስና ስደተኞችን በመቀበል ሊሆን ይገባል" ብለዋል። ለአገር ሰላም፣ ልማትና እድገት መረጋገጥም ሁሉም በአንድነት መተባበር እንደሚገባው ብፁዕነታቸው አሳስበዋል።

ፓትርያርኩ "ይህን ስናደርግ ሠላማችን ተጠብቆ አገሪቱም ለምታ ካደጉት አገራት ተርታ እንድትሰለፍ የዜግነት ግዴታችንን ተወጣን ማለት ነው" ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ በበኩላቸው "በዓሉን ስናከብር አቅመደካሞችና ረዳት የሌላቸውን በመደገፍና በመንከባከብ ሊሆን ይገባል" ነው ያሉት።

በአገሪቱ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና የተጀመረው ልማት ፍሬ እንዲያፈራ ሁሉም በጋራ መሰለፍ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።  "ለአገራችንና ለአፍሪካ ልማትና ዕድገት ሁሉም እንዲረባረብና ሕብረተሰቡም ከዚህ ተጠቃሚ እንዲሆን ቤተ-ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ትሰራለች" ብለዋል።       

በአንዳንድ ዓረብ አገራት በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው ስደት፣ ግፍና አሰቃቂ ግድያ እንዲያበቃ ሁሉም ወደ ፈጣሪው መማፀን እንደሚገባውም ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ጥሪ አቅርበዋል።  "በዓሉ ለዘመናት የዘለቀው የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር እሴት ይበልጥ የሚጎለብትበት መሆን አለበት" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሕዝብ ግንኙነትና ዶኩመንቴሽን መምሪያ ኃላፊ መስዑድ አደም ናቸው።

በአገሪቱ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ሁሉም የኃይማኖት ተቋማት በጸሎት ወደ ፈጣሪያቸው መማፀን ይገባቸዋል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። የኃይማኖት አባቶች በግንቦት የሚካሄደው ምርጫ በሠላም እንዲጠናቀቅ የሁሉም ትብብር አስፈላጊ በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ መንግሥት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሕዝቡ በጋራ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ነገ ሚያዝያ 4 ቀን 2007 ዓ.ም በመላ ሕዝበ-ክርስቲያኑ ዘንድ የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል የሰላምና የደስታ እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።
ምንጭ:  ኢዜአ

No comments:

Post a Comment