Tuesday, March 03, 2015

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ታዳጊ ትምህርት ቤት ልታስገነባ ነው

(Mar 03, ((አዲስ አበባ))-- በአውስትራሊያ ሜልቦርን ከተማ ነዋሪዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት ታዳጊ በሽልማት ያገኘችውን 20ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ኢትዮጵያ ውስጥ ለትምህርት ቤት ግንባታ ለማዋል መወሰኗን አስታወቀች። የትምህርት ቤቱ ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር ገልጻለች፡፡


የ14 ዓመት እድሜ ታዳጊ ብሪቱ ጃለታ ሽልማቷንና የምትገነባውን ትምህርት ቤት አስመልክታ ትናንት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠችው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጸችው፤ በሽልማት ባገኘችው የ20ሚሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ትምህርት ቤት ለመገንባት ያቀደችው በምሥራቅ ሐረርጌ ጋራሙለታ በሚባለው አካባቢ ነው። ትምህርት ቤቱም ከሙዋዕለ ህፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያለ ነው፡፡

ታዳጊዋ ትምህርት ቤት ለመገንባት ያነሳሳትንም ምክንያት እንዳስረዳችው፤ ከሁለት ዓመት በፊት ታናሽ ወንድሟ ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት ወቅት በእርሱ እድሜ ያሉ ተማሪዎችን አስመልክቶ ያየውን ክፍተት ከተነጋገሩ በኋላ ያገኘችውን ሽልማት በኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት ቤት ለመገንባት ወስናለች፡፡ ለሽልማት ያበቃት ውድድርም እንደ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋማት ያሉ ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ፕሮጀክት በማቅረቧ እንደሆነ ገልጻለች፡፡ «በሽልማቱ ምን ታደርጋላቸሁ?» የሚለውን በማሟላቷም ለሽልማት እንደበቃች አመልክታለች፡፡ ትምህርት ቤቱን ለመገንባት የተቀረጸው ፕሮጀክት የሁለት ዓመት መሆኑንና በዚሁ ዓመት እንደሚጀመር አስታውቃለች፡፡

ታዳጊ ብሪቱ የምታስገነባው ትምህርት ቤት ትውልድ የሚቀረጽበት መሆኑን አስታውሳ፤ እርሷም ለዚህ አስተዋጽኦ ማድረጓ እንዳስደሰታት ገልጻለች፡፡ ወደፊትም በስሟ ፋውንዴሽን በማቋቋም በተመሳሳይ በአፍሪካ ውስጥ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ማቀዷን አስታውቃለች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ እንዳስታወቁት፤ ታዳጊዋ ለመሥራት ያቀደችው ፕሮጀክት ከፍተኛ መሆኑንና ተግባሯም በእርሷ እድሜ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም አረአያነት አለው፡፡የትምህርት እድል ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑም ታዳጊዋን ያስመሰግናታል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለታዳጊዋ የሚያስፈልጋትን የትብብር ድጋፍ በማድረግ ከጎኗ ይሆናል፡፡

ታዳጊ ብሪቱ በተለያዩ ክበባት ውስጥ እንደምትሳተፍና ከእነዚህ መካከልም አንዱ የሰብአዊ አገልግሎት መሆኑንና እርሷም የዚሁ ክበብ መሪ መሆኗም ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶከተር ቴድሮስ አድሓኖም ታዳጊዋን አበረታትተዋታል፡፡
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment