Tuesday, January 06, 2015

ምዕመናን የገና በዕልን አቅመ ደካሞችንና ለችግር ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖችን በመመገብና በመደገፍ ሊያከብሩ ይገባል

(ታህሳስ 28/2007 (አዲስ አበባ))--የክርስትና እምነት ተከታዮች  የገና በዕልን ሲያከብሩ አቅመ ደካሞችንና ለችግር ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖችን በመመገብና በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች አሳሰቡ።

(ENA)


የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ልደትበዓል ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ  በመልክታቸው የእምነቱ ተከታዮች የገናን በዓል ሲያከብሩ በጤና ችግር፣ በልዩ ልዩ አካላዊ፣ስነ ልቦናዊና ድህነት ከደረሰባቸው የህብረሰብ ክፍሎች ጋር በጋራ መሆን አለበት።

በአገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፣በህመም ምክንያት በሆስፒታል ለሚገኙ ዜጎች፣በህግ ጥላ ስር ላሉና ለአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በዓሉ የሰላምና የፍቅር እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የተጀመሩ ፈጣን የልማት መስኮችን ከግብ ለማድረስ ሁሉም በትብብር መስራት እንደሚገባ ፓትርያርኩ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ብርሃነየሱስሱራፌል ህዝበ ክርስቲያኑ የገናን በዓል ሲያከብር ለችግር የተጋለጡና አቅመ ደካሞች በመርዳት መሆን እንዳለበትአሳስበዋል። ሊቀ ጳጳሱ በዚሁ ወቅት “የሰው እውነተኛ ሀብቱ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች መኖሩና መስጠቱ ነው” ያሉ ሲሆን ክርስቲያኖች በዓሉን ሲያከብሩ የተቸገሩትንና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን በመርዳትና በመመገብ መሆን እንዳለበትም መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአገሪቱ የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርንም ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አኳያ መንግስት፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት በጋራ መከላከል ይገባል ብለዋል። ህብረተሰቡ የተጣለበትን አገራዊ ሃላፊነት ከሙስና በጸዳ መልኩ በማከናወን የተጀመረውን የልማትና የእድገት እንቅስቃሴ ማስቀጠል እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።

ሊቀ ጳጳሱ እንደሚሉት ቤተክርስቲያኗ ከስነ-ምግባርና ሃይማኖት ውጪ የሆኑትን ጾታዊ ጥቃትና ኢሰብአዊ ድርጊቶችን አጥብቃ ታወግዛለች። በመሆኑም ችግሩን ለማስቆም የእምነቱ ተከታዮችን በመንፈሳዊ ትምህርቶች በመኮትኮት ቤተ ክርስቲያኗ የራሷን ሃላፊነት እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል።

በማረሚያ ቤቶች፣በተለያዩ ሆስፒታሎችና ቤታቸው በህመም ላይ ለሚገኙ ዜጎችና ለመከላከያ ሰራዊት አባላትና አጠቃላይ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ መልካም የገና በዓል እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል። በሌላ ዜና ብጹዕ አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል በዓለም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ  ጳጳሳት አማካኝነት የካርዲናልነት ሹመት ማግኝታቸው ተገልጿል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ብርሃነየሱስ ይህንን ሹመት መቀበላቸው ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን በጎ ገጽታና ተቀባይነት የሚያሳይ መሆኑን ከቤተክርቲያኗ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። እንደመረጃው ከሆነ ሊቀ ጳጳሱ ለሹመት የበቁት ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ መንፈሳዊ ስራዎች እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ነው።

በዚህም ከአለም የካቶሊክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለመላው ዓለም የሰላም፣የፍትህና የሞራል ድምጽ በመሆን ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የሚያገለግሉበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር ተገልጿል። የካርዲናልነት ሹመቱ የታወጀው አቡነ ብርሃነየሱስን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት ለተውጣጡ ለ15 ሊቀ ጳጳሳት ነው።
ምንጭ:  ኢዜአ

No comments:

Post a Comment