Sunday, December 28, 2014

«ዴሞክራሲ እንዲያብብ የመጫወቻ ሜዳዎች በሕግና ሥርዓት መመራት አለባቸው»

(Dec 28, 2014, (አዲስ አበባ))--ሰሞኑን ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ የነበራቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ «የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዢው ፓርቲ ጋር ለመነጋገር እንፈልጋለን ካሉ መንገዱ በሕግ ተቀምጧል» ማለታቸው የሚታወስ ነው። ለውይይቱ ግን በምርጫ ሥነ ምግባር ደንቡ መሰረት ሕጋዊ ሆኖ መንቀሳቀስ ቀዳሚ መሆኑን በማስታወስ። «በሕጉ መሰረት ችግሮችን ለመፍታት አሁንም በሩ ክፍት ነው» ብለው፤ በምክር ቤቱ የማይሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር በዚህ ጉዳይ በግል በቢሮዋቸው መወያየታቸውን አንስተዋል። ነገር ግን ከውይይቱ በኋላ መሪዎቹ ለመሳተፍ ወስነው ይሄዱና ሌሎቹ ስለማይቀበሏቸው «ምንም ማድረግ አልቻልንም» ብለው እንደሚቀሩ አንስተዋል። 

«ሁሉም ፓርቲዎች እኩል ለዚች አገር አስተዋጾኦ ማበርከት ይችላሉ፤ ይገባቸዋልም» የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ «እገሌ ፓርቲ ባለበት እኔ አልቀመጥም» የሚሉ ከሆነ ግን የገዢው ፓርቲ ሥራ ተቃዋሚዎችን ማነጋገር ብቻ መሆን የለበትም። ምክንያቱም 91 ፓርቲ 91 ቀን ማነጋገር ስለማይቻል አንድ ላይ እንወያይ ሲሉም ጥሪ ያቀርባሉ። «ይች አገር የጋራ አገር ናት» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጋራ ችግራችንን በጋራ ተወያይተን በጋራ እንፍታ የሚል አስተሳሰብ መያዙን ያሰምሩበታል። ስለዚህ «ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመልሰው ወደ ጋራ ምክር ቤት መጥተው ለሥነ ምግባር ደንቡ ተገዥ በመሆን ምርጫውን ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ እና ነፃ ለማድረግ እንድንሰራ ጥሪ አቀርባለው» ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በአግባቡ እየተወዳደሩ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲያድግ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። «በየትኛውም አገር ዴሞክራሲ እንዲያብብ የመጫወቻ ሜዳዎች በሕግና ሥርዓት መመራት አለባቸው» የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ «ዳኛና ሕግ የሌለበት እግር ኳስ፤ እግር ኳስ ስለማይሆን ዳኛና ሥርዓት ይበጅለታል» ብለዋል። የዴሞክራሲም ተመሳሳይ ነው። ፓርቲዎች ከሕገ መንግስቱ በተቀዳ ሕግ ይዳኛሉ። በመሆኑም ፖለቲካ ፓርቲዎች ፍላጎቶቻቸውን ለሚወክሏቸውና ለአጠቃላይ ህዝብ የሚያቀርቡበት ሂደት በመሰራት ላይ ነው። ነገር ግን «ከዚህ ሕግና ሥርዓት ውጪ እንሰራለን የሚሉ ፓርቲዎች ሲኖሩ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት አንዳንዴ ቢጫ፤ አንዳንዴም ቀይ ካርድ የሚሰጥበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል» ነው ያሉት።

«ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሦስት ከፍለን ነው የምናያቸው» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፤ ጨዋታውን በአግባቡ መጫወት የሚፈልጉ እና መጫወት የጀመሩት በዚሁ መቀጠል አለባቸው። ወጣ ገባ የሚሉት ደግሞ በጫወታው ሕግ መሰረት መንቀሳቀስ አለባቸው። ምክንያቱም ይሄ ለሁሉም ይጠቅማልና። በአገራችን ዴሞክራሲ እንዲያብብ ከተፈለገ የመንግስት ኃላፊነት ብቻ መሆን የለበትም። የሁሉም ፓርቲዎችና ኃላፊነት እንጂ። በሶስተኛ ደረጃ የሚቀመጡት ደግሞ የፕሮፖጋንዳ መሳሪያቸው በውጭ አገር የሆነ፣ አመፅና ብጥብጥ የሚያደርጉ፣ ለአገሪቱ ፖለቲካ ፋይዳ የሌለው ጉዞ የሚጓዙት ናቸው። 

ይሄን ድርጊት በሚተባበሩት ላይ መንግስት ሕግ የማስከበር ግዴታው ነው። ምክንያቱም የሕግ የበላይነት መከበር አለበትና። በመሆኑም የተቃዋሚ ፓርቲ አካላት «መሪዎቻችን ታሰሩ» ከማለት ይልቅ «ለምን ታሰሩማለትን እንዲጀምሩ መጠየቅ እንደሚገባ መክረዋል። ሕገወጥ መንገድ እየተከተሉ ያሉትም ፓርቲዎች ሳይሆኑ በፓርቲ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች መሆናቸውን በመጥቀስ።

ቀጣዩን ምርጫ የሚታዘቡ አካላት አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ የአውሮፓ ህብረት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል «የተለያዩ ቦታዎች መታዘባችንን ተከትሎ የሎጂስቲክ ችግር ስላለብን የዘንድሮውን ምርጫ መታዘብ አንችልም» ማለቱን ተናግረዋል። ነገር ግን የምርጫው ዋና ባለቤቶች የምርጫ ተፎካካሪዎች እና የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሆነ ህብረቱ ታዘበም አልታዘበም ወሳኙ ጉዳይ ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ ታማኒነት ያለው እና ነፃ ለማድረግ መንግስት ከህዝቡ ጋር ጠንክሮ መስራቱ ወሳኝ ነው። ከዚህ ባለፈ የአፍሪካ ኅብረት ምርጫውን ለመታዘብ ከተለያዩ አካላትና ተቋማት የተወከሉ ታዛቢዎች እንደሚልክ መግለጹን ተናግረዋል።

በሬ ወለደ
አምንስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት በተለያየ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ የተዛቡ መረጃዎችን ሲያወጡ ይታያል። ከእነዚህ ዘገባዎች ውስጥ ደግሞ በተለይም በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች «መሬት ለኢንቨስተር የሚሰጠው አርሶ አደሩ እየተፈናቀለ ነው» የሚል ይገኝበታል። ይሄን አስመልክቶ በአገሪቱ የግብርና ልማት ስትራቴጂ መሰረት አንደኛው በአርሶ አደሮች እና በአርብቶ አደሮች የሚካሄደው ግብርና መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሌላው በግል ባለሀብቶች የሚከናወነው ነው። እንደ አገር የግብርና ምርታማነት አሟጥጦ ለመጠቀም ካስፈለገ የአርሶ እና አርብቶ አደሩ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከፍተኛ ደረጃ ማድረስ ይገባል።

አገሪቱ ሰፊ የሚለማ መሬት ባለቤት በመሆኗ በሰፋፊ አካባቢዎች የግል ባለሀብቱ በሰፊው እንዲሰማራ ይደረጋል። በከፊል ወይና ደጋ፣ ወይና ደጋ እና ደጋ አካባቢዎች ዘመናዊ የሆኑና ብዙ መሬት የማይጠይቁ የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶች ላይ ማሰማራት ነው ። ከጊዜ ወደ ጊዜ በግሉም ሆነ በአርሶ አደሩ አካባቢ የሚታየው ልማት ማደጉንም ጠቁመዋል። ሦስተኛው የግብርና ልማት ደግሞ ሰፋፊ መሬት ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ያተኮረ ልማት ነው የሚካሄደው። «መንግስት መሬቱ በማንም ያልተያዘ፣ የአካባቢ ጥበቃን መሰረት ያደረገ፣ የደን ምንጠራ በስፋት የማይካሄድበት፣ አካባቢን ሊጎዳ በማይችል መልኩ ብቁና አስተማማኝ መሬት ሲገኝ ከልሎ በማስቀመጥ ለግል ባለሀብቶች የሚያስተላልፍበት የሊዝ ሥርዓት አዘጋጅተናል» ብለዋል።

በመሆኑም ሥርዓቱ ማንኛውንም አርሶ አደር የማያፈናቅል፣ አካባቢን የማይበክል እና ኃላፊነት የተሞላበት መሆኑን አረጋግጠዋል። በሰፋፊ እርሻዎች ዙሪያ ያለው የግብርና ስራ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂውን መስፈርት የሚያሟላ መሆኑን አንስተዋል። ይሄን ደግሞ የሌሎች አገሮች ዲፕሎማቶች ሳይቀር የመሰከሩት ነው። መፈናቀልን አስመልክቶ «ከአርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ ጋር በቂ ውይይት ተደርጓል» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዋናነት የአካባቢ ልማትን መሰረት ያደረገ ግብርና እንደሚካሄድ በሚገባ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ነገር ግን በኢትዮጵያ ላይ የሚቀርበው የተቋማቱ ሪፖርት ረጀም ጊዜ ያስቆጠረና ከእውነት የራቀ በመሆኑ «ውሾቹ ይጮሃሉ ግመሉ ግን ጉዞውን ቀጥሏል» ብለዋል።

«ኢትዮጵያ ምዕራባውያን አገራት እንደፈለጉ የሚያሽከረክሯት አገር አይደለችም» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ አገራቱ መንግስታትን ለማንበርከክ የሚጠቀሙት ይሄን መረብ እንደሆነ አንስተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ግን ለዚህ እንደማይንበረከክ በተደጋጋሚ ገልጿል። ስለሆነም ምዕራባውያኑ የራሳቸውን ርዕዮተ ዓለም በኢትዮጵያ ለማስገባት ከመሞከር በተነሳ የሚያደርጉት እኩይ ተግባር ነው ብለዋል። አገራችን ከልማታዊ ዴሞክራሲ አቅጣጫ ውጪ በፍጥነት አትለማም የሚል ፅኑ እምነት መኖሩን በማስታወስ። ለዚህ አሳባቸው ማጠናከሪያም «ምዕራባውያን የኒዮ ሊበራሊዝም መድሃኒት ርዕዮት ያስዋጧቸው በርካታ አገሮች ለሞት ተዳርገዋል፤ ስለዚህ እኛም እሱን ውጠን መሞት አንፈልግም» ። ነገር ግን ይሄ «ከነሱ ጋር ጥላቻ ስላለን ሳይሆን፤ የአገር ህልውና በመሆኑ ነው» ብለዋል።

የእነዚህን ወገኖች ተፅህኖ መታገል እንደሚገባ አንስተው፤ በተለይም ከተደራጁ አካላት ጋር በመሆን መንግስትን ለማንበርከክ የሚጥሩ በመሆናቸው የተለያዩ አካሄዶችን ይከተላሉ ብለዋል። በማሳያነት የጠቀሱት ደግሞ ከአስር ዓመት በፊት የተከናወነውን ምርጫ ተከትሎ የፈጠሩትን እንቅስቃሴ ነው። አሁንም በተመሳሳይ ምርጫን ጠብቀው የምርጫው እንቅስቃሴ ሰላማዊ እንዳይሆን ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል። «ሰሞኑን እየሰጡ ያሉት መግለጫም የዚሁ አካል ነው» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሞቀ ነገር ተከትሎ መነሳት ባህሪያቸው ነው። «ነገር ግን የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚወስነው የኢትዮጵያ ህዝብ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ነው» ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም፣ ልማት፣ ዕድገት እና ዴሞክራሲ ፈላጊ ነው። በመሆኑም ይሄ ፍላጎት እንዲሟላ መንግስት ጠንክሮ ይሰራል ብለዋል። ከተቋማቱ ጋር የሚኖረው ትግልም ሊሰምር የሚችለው በውስጥ ልማት ብቻ ነው። ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እና ኦሮሚያ ክልሎች ሰፋፊ መሬቶች ያሉባቸው አካባቢዎች ናቸው። ነገር ግን የእነዚህ አካባቢ ህዝብ እውነታውን በአግባቡ መረዳቱን ጠቁመው፤ በተደጋጋሚ «እኛ አልተፈናቀልንም፤ በእኛ ስም አትነግዱ፤ ልማቱን እንፈልጋለን» ማለታቸውን ጠቁመዋል። ነገር ግን የተቋማቱ የመረጃ ምንጮች በራሱ የተሳሳተ መሆኑን አንስተዋል።

መፍትሄ ይሻሉ
ከሕብረተሰቡ ተደጋግመው ከሚነሱት ውስጥ የመብራት፣ ውሃ እና ኔትዎርክ ችግር ቅድሚያውን ይይዛል። በመሆኑም እነዚህ ችግሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው ይታያሉ። «ሕዝብ ያልረካባቸው የአገልግሎቶች ዘርፎች እንዳሉ ከህዝቡ ጋር ስንወያይ አውቀናል» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በርካታ ውይይቶች ተደርገው በርካታ ግብዓት ተገኝቶባቸዋል። ከኃይል መቆራረጥ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ ችግር ምክንያት በአብዛኛው ከአዲስ አበባ ዘመናዊነት ጋር ተያይዞ አብዛኛው ሰው የኤሌክትሪክ ምድጃ መጠቀሙ መሆኑን አንስተዋል። ለአብነት ያነሱት ደግሞ እስከ አራት መቶ ሺ የሚገመተውን የኮንዶሚኒየም ነዋሪ ቁጥር ነው። 

ይሄን የኃይል ፍላጎት ሊሸከም የሚችል ንዑስ ማስተላለፊያ ቀድሞ ባለመዘጋጀቱ የማስተላለፍ ሂደቱ ላይ መሰናክል መሆኑን አንስተዋል። ኃይል ሲበዛባቸው ይቃጠላሉ። ጊዜያዊው መፍትሄ ትራንስፎርመር መቀየር ሲሆን በመካከለኛ ዕቅድ ደግሞ ንዑስ ማስተላለፊያውን አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑ ማምጣት ነው። ለዚህ የውጭ ኩባንያዎች እንዲሰሩ ጨረታ ወጥቷል። ስለዚህ ችግሩ በሂደት እንደሚፈታ ጠቁመዋል። የውሃም ተመሳሳይ ነው። መቶ ሺ ሜትር ኩብ ወደ አዲስ አበባ እየገባ ይገኛል። እስከ መጋቢት ደግሞ ተጨማሪ 130 ሺ ሜትር ኩብ ውሃ ይገኛል። ስለዚህ የውሃ ችግሩም በቅርቡ ይፈታል ብለዋል። «የስልክ ጉዳይ ቴክኒካል ጉዳይ ነው» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ዓመት መጨረሻ መፍትሄ ያገኛል ባይ ናቸው።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ 

No comments:

Post a Comment