Thursday, April 26, 2012

መንግሥት በኢትዮጵያ የፌስቱላ ሆስፒታል መስራች ለሆኑት ዶክተር ካትሪን የክብር ዜግነት ሰጠ

(ሚያዝያ 18 ቀን 2004 (አዲስ አበባ)--መንግሥት በኢትዮጵያ የፌስቱላ ሆስፒታል መስራችና ባለቤት ለሆኑት ዶክተር ካትሪን ሐምሊን ላበረከቱት የላቀ የሰብዓዊና የሕክምና አገልግሎት የክብር ዜግነት ሰጠ፡፡

የተሰጠው የክብር ዜግነትም ዶክተር ካትሪን በኢትዮጵያ የፌስቱላ ሆስፒታሎችን በመመሰረት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በሰጡት የሕክምና እንዲሁም የሰብዓዊ አገልግሎት በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እናቶችን ሕይወት በመታደጋቸው ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለዶክተር ካትሪን የኢትዮጵያ ፓስፖርትና የክብር ዜግነት የምስክር ወረቀት ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው በሰጡበት ወቅት እንዳሉት ዶክተር ካትሪን ከኢትዮጵያውያን አንዷ መሆን መቻላቸው የሚያኮራ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን የክብር ዜግነት ሲሰጥም ዶክተር ካትሪን በአገሪቱ ለ53 ዓመታት የሰጡትን የሰብዓዊና የሕክምና ግልጋሎት ዕውቅና እንዲያገኝ ታስቦ ነው ማለታቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ አመልክቷል፡፡ ዶክተር ካትሪን በኢትዮጵያ የፌስቱላ ሕመም ሰለባ ለሆኑ ሴቶችና እናቶች የተለየ ፍቅርና ሕክምና በመሰጠት ለረጅም ዓመታት የሚደነቅ ተግባራ መፈጸማቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ይህን የላቀ ሥራ ለሰሩ ታላቅ የሕክምና ሰው የክብር ዜግነት መስጠቱ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም በበኩላቸው አንዲት የውጭ አገር ሰው የኢትዮጵያውያን ሴቶችና እናቶች የጤና ችግርን ለማስወገድ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በቁርጠኛነት መሥራታቸው ለኢትዮጵያውያን ያላቸውን ፍቅር እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡  ዶክተር ካትሪን የፌስቱላ ሕሙማንን ለመርዳት ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ባከናወኑት ሥራ በበርካታ ኢትዮጵያውያን እናቶችና ሴቶች ልብ ውስጥ የተለየ ቦታ እንዲይዙ አድርጓቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፌስቱላ ሆስፒታል መስራችና ባለቤት ዶክተር ካትሪን በዚሁ ወቅት በሰጡት አስተያየት "ኢትዮጵያ ባልወለድባትም ፤ከትውልድ አገሬ ይበልጥ እወዳታለሁ" ብለዋል፡፡ "አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለአገሪቱና ለሕዝቧ ያለኝን ፍቅርና አክብሮት ተገንዝቦ የክብር ዜጋ እንደሆን ስለፈቀደልኝ ከምንም ነገር በላይ ደስተኛ እንድሆን አድርጎኛል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደማንኛውመ ታዳጊ አገር በፌስቱላ በሽታ ተጠቂ የሆኑ ሴቶችና እናቶች ያሏት አገር ስትሆን፤ በሆስፒታል ደረጃ የተቀናጀ የፌስቱላ ሕክምና በመስጠት ግን ብቸኛዋ አገር እንደሚያደርጋት ገልጸዋል፡፡  ከዚህ አንፃር በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ተወስኖ የነበረው የፌስቱላ የሕክምና አገልግሎትም አብዛኛው የበሽታው ተጠቂዎች ወደሚገኝባቸው ክልሎች ለማድረስ ያደረጉት ጥረትም የሚያበረታታ ውጤት ማስገኘቱን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም የፌስቱላ ሕክምና ለአብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ሴቶችና እናቶች ተደራሽ ለማድረግም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሐረር፣ ባህር ዳር፣ መቀለና ይርጋዓለም ከተሞች የሆስፒታል አገልግሎት በመሰጠት ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ዕድሜያቸው 88 ዓመት እንደ ደረሰ የተናገሩት ዶክተር ካትሪን፣ የተሰጣቸው የክብር ዜግነት የጀመሩትን የሰብዓዊና የሕክምና አገልግሎት ዘላቂነት እንዲኖረው የሚያደርግ ኃላፊነት እንደጣለባቸው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም በቀሪ የዕድሜ ዘመናቸው የተጀመረውን በጎ ሥራ ዳር ለማድረስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ብሎም የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያደርጉላቸው ድጋፍ በመታገዝ ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡  ዶክተር ካተሪን የፅንስና የማህጸን ስፔሻሊስት ሲሆኑ፣ በፌስቱላ ቀዶ ጥገና ፋና ወጊ የሕክምና ቴክኒክ ሥራቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ-ሕዝብ ፈንድ ዕውቅና አግኝተዋል፡፡

በተመሳሳይም በዚህ ዓመት ከእንግሊዝ ንግሥት ከዳግማዊት ኤልሳቤጥ ከፍተኛ የሰብዓዊ አገልግሎት የክብር ሽልማት በትውልድ አገራቸው አውስትራሊያ ካንቤራ ከተማ መቀበላቸውን ከሐምሊን የፌስቱላ ሆስፒታል የሕዝብ ግንኙነት ክፍል የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡  ዶክተር በፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የተሰጣቸውን በኢትዮጵያ ምርጥ የሰብዓዊና የማዕበራዊ አገልግሎት ሽልማት በተጨማሪ 23 ያህል ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘት የቻሉ ታላቅ ባለሙያ ናቸው፡፡

ዶክተር ካትሪን ሐምሊን በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ የተወለዱ ሲሆን አዲስ አበባ በሚገኘው በቀድሞ የልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል በአሁኑ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ሆስፒታል የአዋላጅነት ትምህርት ቤት ለመምህርነት በኢትዮጵያ መንግሥት የወጣውን የሥራ ማስታወቂያ ተከትለው ነበር እኤአ በ1959 አዲስ አበባ መግባታቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ከዚያን ጊዜ አንስተው በሞት ከተለያቸው ባለቤታቸው ከዶክተር ሬግ ሐምሊን ጋር በመሆን ከ34 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የፌስቱላ ታማሚ ኢትዮጵያውያን ሴቶችና እናቶች የሕክምና አገልግሎት መስጠታቸው የታሪክ ድርሳናትን ዋቢ አድርጎ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡
Source: Ethipian News Agency

No comments:

Post a Comment