Tuesday, April 17, 2012

የአንበሳ ፓርክ አሁን ካለበት ስፍራ ቦሌ ወደ ሚገኘው ፒኮክ መናፈሻ ሊዛወር ነው

(ሚያዝያ 8 ቀን 2004 (አዲስ አበባ) --የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርስድስት ኪሎ አካባቢ የሚገኘውና በተለምዶ አንበሳ ግቢ እየተባለ የሚጠራው የአንበሳ ፓርክ አሁን ካለበት ስፍራ ቦሌ ወደ ሚገኘው ፒኮክ መናፈሻ ሊዛወር ነው።
አስተዳደሩ ለ16 አናብስት ማቆያ ፓርክ ለማስገንባት ከመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ጋር በ30 ሚሊዮን ብር የግንባታ ስምምነት ዛሬ ተፈራረመ።

የአንበሳ ግቢ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙህዲን አብዱልአዚዝ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት በ1940 የተቋቋመው የአንበሳ ግቢ በአሁኑ ወቅት ስምንት ሴትና ስምንት ወንድ አናብስትን ጨምሮ አስር አይነት የአናብስት ዝርያዎችን ይዟል። አዲሱ የፒኮክ ፓርክ ላለፉት 64 አመታት ምቹ ባልሆነ በተጨናነቀ ጠባብ ስፍራ በመጠለያው ውስጥ የኖሩትን እነዚህኑ የአናብስት ወደ ተሻለ ስፍራ በማዘዋወር እየተመናመነ የመጣውን የአናብስት ቁጥር ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት አካል ነው ብለዋል።

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ 1ነጥብ 2 ሄክታር ስፋት ያለው የአንበሳ ግቢ እጅግ ጠባብ በመሆኑ የጎብኚዎች ምቾትም ሆነ ለፓርኩ እድገት እብዛም ተስማሚ ሳይሆን ቆይቷል።  በፓርኩ ጠባብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም አናብስቱ እንዳይራቡ ሲደረግ መቆየቱንና ሌሎች ዝርያዎችን በማምጣት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢም ለማሳዳግ አዳጋች ሆኖ እንደነበር አመልክተዋል። ፓርኩን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ፓርኩን ከጎበኙ 786ሺህ ሰዎች ከ1 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገቢ መገሸቱን ጠቁመው፣ የተገኘው ገቢ ግን ፓርኩ ለአናብስቱ ቀለብና ለአስተዳደራዊ ስራዎች ከሚያወጣው ጋር ፈጽሞ የማይጣጣ እንደሆነ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ወንድማገኝ ተሰማ በበኩላቸው በፒኮክ መናፈሻ ውስጥ የሚገነባው አዲሱ የእንስሳት ማቆያ ፓርኩ አስቸጋሪ ሁኔታ ያሉ የአናብስት ዝርያዎች ችግር የሚያቃል መሆኑን ገልጸዋል። እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመ የመጣውን የአናብስት ዝርያዎች ጠብቆ ለማቆዬት ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።

አዲሱ ፓርክ የከተማዋ ህዝብ ስለአናብስቱ እንዲያውቅና እንዲዝናና ከሚሰጠው ዕድል በሻገር ለከተማዋ የቱሪስት መስህብ ስፍራ በመሆን የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና ለገጽታ ግንባታው የድርሻውን እንደሚያበረክ ይጠበቃል። በተጨማሪም ለከተማዋ ነዋሪዎችም መጠነኛ የስራ እድል እንደሚፈጥር አቶ ወንድማገኝ አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፒኮክ መናፈሻ ውስጥ ለሚገነባው አዲሱ የእንስሳት ማቆያ ፓር 30 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን ጠቁመው፣ አስተዳደሩ የግንባታውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ለማስጀመርም 15 ሚሊዮን ብር መመደቡንም አመልክተዋል።

በአዲሱ ፓርክ ውስጥ አናብስቱና ሌሎች እንስሳት በመስታውት ውስጥ ሆነው ለጎብኚዎች እይታ የሚቀርቡ ሲሆን፣ የፓርኩ ዲዛይን ጎብኚዎች በእንስሳቱ አደጋ እንዳይደርሰባቸው ለመከላከል ልዩ የደህንነት ጥበቃ እንዲኖረው ተደርጓል ብለዋል።
ምክትል ሃላፊው ማብራሪያ አዲሱ ፓርክ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ የከተማዋ ትልቁ የቱሪት መስህብ ስፍራም እንደሚሆን ይጠበቃል።


ጀርመን አገር ከሚገኝ የእንስሳት ማቆያ ፓርክ አርክቴክት ጋር በመተባበር ወደ 475 ሚሊዮን ብር በሚገመት ወጪ የተዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ የእንስሳት ማቆያ ማስተር ፕላን ለ25 አመት አገልግሎት እንደሚሰጥ የከንቲባው የመሰረተ ልማትና የፓርኩ አማካሪ አቶ ፈለቀ ይመር ገልጸዋል።

አዲሱ ፓርክ ተፈጥሯዊ ይዘቱን የጠበቀ ለማድረግና ለየት ያለ ዲዛይን ለማሰራት ረዥም ጊዜና ብዙ ጥረት እንደተደረጉበትም ጠቅሰዋል። ማስተር ፕላኑ የአገራችንን ኢኮሎጂካል ዞንና ጂኦግራፊያዊ ቀጠናዎች ውስጥ የሚገኙ እንስሳትንና አጽዋትን ሊወክል የሚችል ሆኖ የተዘጋጀ ነው ብለዋል። አማካሪው እንዳሉት በኦሞ ሸለቆና በሰሜን ተራሮች ያሉ እንደ ዋሊያ አይቤክስና ቀይ ቀበሮ የመሳሰሉ እንስሳትን ወደ ፓርኩ ለማምትም ታስቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ መካከል ዛሬ የተፈረመው ስምምነት በ26 ሄክታር መሬት ላይ በአራት ዙሮች ተከፍሎ የሚካሄደው ግንባታ አንድ አካል እንደሆነ ጠቁመዋል።
የፓርኩ ግንባታ ፈጥኖ እንደሚጀመር አማካሪው ጠቅሰው፣ የአናብሰቱ ማቆያ አስተዳደሩ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱንም አብራርተዋል።

የመጀመሪያ ዙር ግንባታ በሚካሄድበት አካባቢ ከሰፈሩ አስራ አራት ነዋሪዎች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት መደረጉንና ነዋሪቹ ምትክ ቦታና የኪይ ቤት ተሰጥቷ ከቦታው መነሳታቸውን አቶ ፈለቀ ገልጸዋል። የፓርኩን ግንባታ የሚያከናውነው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ወልዳይ ሃይሌ ግንባታውን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ በሚፈለገው ጥራትና ደረጃ ገንብተው እንደሚያስረክቡ ማረጋገጣቸው ኢዜአ ዘግቧል።
Source: ENA

No comments:

Post a Comment