Wednesday, January 12, 2011

የትውልደ ኢትዮጵያዊው አሜሪካዊ ግድያ በፖሊስ እየተጣራ ነው




Wednesday, 12 January 2011 09:35 
Source: Reporter
- አስከሬኑ ትናንት ምሽት ላይ ወደ አሜሪካ ተልኳል
በታምሩ ጽጌ
የገና በዓልን ከቤተሰቦቹ ጋር ለማክበር ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አሜሪካዊ ወጣት አረፈዓይኔ ቦብ ዊን ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ሕይወቱ ማለፉን ቤተሰቦቹ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር አውሎ ጉዳዩን እየመረመረው እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
የሟች ቤተሰቦች በአረፈዓይኔ ላይ ግድያ ተፈጸመ የሚሉት ባለፈው እሑድ ጥር 1 ቀን 2003 ዓ.ም. ሌሊት ለሰኞ አጥቢያ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 03/05 ክልል ልዩ ቦታው ከቦሌ መድኃኔዓለም ወደ አያት ሆስፒታል በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው የምሽት ክለብ አካባቢ ነው፡፡

ሟች በምሽት ክበቡ ውስጥ ከቤተሰቦቹ ጋር በሚዝናናበት ወቅት ረብሻ ሲፈጠር መዝናናታቸውን አቁመው በመውጣት በያዙት ተሽከርካሪ ለመጓዝ ሲንቀሳቀሱ፣ ፖሊስ ደርሶ ‹‹ቁሙ›› ሲላቸው ዝም ብለው ሲሄዱ የተኩስ ድምፅ እንደሰሙ ቤተሰቦቹ ተናግረዋል፡፡

ተሽከርከሪያቸው ተንቀሳቅሶ ትንሽ እንደሄዱ ሟች ባንደኛው ልጅ ላይ መደገፉን የገለጹት ቤተሰቦቹ፣ ወዲያው ባፉ ደም በመፍሰሱ ወደ ቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል ይዘውት ቢሄዱም ሆስፒታል ሲደርሱ ሕይወቱ ማለፉን ተናግረዋል፡፡

ሟች በተተኮሰው ጥይት በግራ ጐኑ ተመትቶ በቀኝ ጡቱ አካባቢ ጥይቱ መውጣቱንና ለሞት መዳረጉንም ቤተሰቦቹ አስታውቀዋል፡፡

ዓረፈዓይኔ እናቱ ኢትዮጵያዊት ስትሆን አባቱ ጥቁር አሜሪካዊ መሆኑን፣ ለቤተሰቦቹ የመጀመሪያ ልጅና በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ከተማ በሳንሆሴ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ እንደነበር ቤተሰቦቹ መስክረዋል፡፡

የ20 ዓመት ወጣት የነበረው ሟች ከአያቱ (ከእናቱ እናት) ጋር የገና በዓልን ለማክበር መምጣቱን የገለጹት ቤተሰቦቹ፣ ትናንትና ምሽት ላይ አያቱ አስከሬኑን በኤምሬትስ አየር መንገድ አውሮፕላን ጭነው ወደ ትውልድ አገሩ አሜሪካ ይዘው መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ከሌሊቱ 7፡45 ሰዓት አካባቢ በተፈጠረው ድንገተኛ አደጋ የወንድማቸው ሕይወት ማለፉ በጣም እንዳሳዘናቸው የተናገሩት ቤተሰቦቹ፣ ሟች ወጣት በመሆኑ ችግር እንኳን ቢያደርስ ከመግደል ይልቅ ወደ ላይ ተኩሶ ማስቆም ሲቻል መገደሉ የሚያሳዝን መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥትም ጉዳዩን ተከታትሎ የወንድማቸውን ደም እንዲወጣላቸው ጠይቀዋል፡፡

ሟች ዜግነቱ አሜሪካዊ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የአሜሪካ ኤምባሲ ማሳወቃቸውንና ኤምባሲውም ጉዳዩን እንደሚከታተለው እንደገለጸላቸው ቤተሰቦቹ ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል በቁጥር 2970/44/03 ጥር 2 ቀን 2003 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ባደረገው የአስከሬን ምርመራ፣ ሟች በጥይት ተመትቶ መሞቱን ሲያረጋግጥ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም በቁጥር አፓወም /01/8247/03 ጥር 3 ቀን 2003 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ሟች በጥይት ተመትቶ መሞቱን ሪፖርት ተደርጐለት ምርመራ እያከናወነ መሆኑን ገልጿል፡፡

ፖሊስ ህትመት እስከገባንበት ድረስ የደረሰበትን የምርመራ ውጤት ጠይቀነው፣ ተጠርጣሪው የፖሊስ አባል መሆኑን አረጋግጦ፣ በቁጥጥር ሥር መዋሉንና ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ የሰው መግደል ወንጀል ምርመራ ኃላፊ ኢንስፔክተር ፀጋዬ ባልቻ ተናግረዋል፡፡

1 comment:

Anonymous said...

very sad new. RIP..

Post a Comment