Tuesday, January 25, 2011

መንግሥት ዳያስፖራው በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ እንዲሳተፍ ሊፈቅድ ነው

(Sunday, 23 January 2011, Reporter)--በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በባንክና ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚከለክለውን ሕግ ለማሻሻል መንግሥት ዕቅድ እንዳለው አስታወቀ፡፡
የዳያስፖራው የቀረጥ ነፃና የማበረታቻ ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ፡፡

ከትናንት በስቲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ለመወያየት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ እንዳስታወቁት፣ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተከልክሎ በቆየው የባንክና የኢንሹራንስ ዘርፍ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያስችል ጥናት ተጀምሯል፡፡

እስካሁን ክልከላ የተደረገበት የራሱ የሆነ ምክንያት ነበረው ያሉት የባንኩ ገዢ፣ ይኼው ምክንያት በየዓመቱ ከዲያስፖራው ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ሲገለጽ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

እንደ አቶ ተክለ ወልድ፣ ‹‹ፖሊሲው ሲወጣ ዳያስፖራውን ለመከልከል አልነበረም፡፡ ዋነኛ ዓላማው ትላልቅ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ገብተው የአገር ውስጥ ባንኮችን እንዳያዳክሙና የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ለማድረግ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በተለይም የአገር ውስጥ ባንኮች እስኪደራጁና እስኪጠናከሩ ድረስ መጠበቅ ስለሚያስፈልግ ክልከላው መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ የነበሩት ዳያስፖራዎች ግን፣ ‹‹እኛ እያልን ያለነው በግለሰብ ደረጃ የባንክ አክሲዮን እንድንገዛ መፈቀድ አለበት፤›› የሚለውን መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡

አቶ ተክለ ወልድም፣ ‹‹የውጭ ባንኮቹም ቢሆኑ የግለሰብ ውጤቶች ናቸው፤›› ብለው የውጭ ባንኮች እጅ የሌለበት ወይም ተወካይ ስላለመሆናችሁ ምን ማረጋገጫ አለ?›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሆኖም አሁን ባለንበት ደረጃ ዳያስፖራው እስካሁን ተከልክሎ የቆየውን በፋይናንስ ዘርፍ ላይ መሠማራት የሚከለክለውን ሕግ ሊያሻሽል የሚችል ጥናት እየተደረገ ነው፡፡ በምን ዓይነት ሁኔታ ይፈቀድ የሚለው ውሳኔ ግን ጥናቱ ካለቀ በኋላ ይፋ የሚደረግ ይሆናል፤›› አረጋግጠዋል፡፡

ይህ የመንግሥት አቋም ለዓመታት በዳያስፖራው በተደጋጋሚ ሲቀርብ የነበረውን ጥያቄ በተወሰነ ደረጃ መልስ የሰጠ በመሆኑ ዕቅዱን በጎለቱ የተገኙ የዳያስፖራ አባላት ደግፈውታል፡፡

ከአሜሪካ ዳላስ የመጣው የስብሰባው ተሳታፊ ወጣት ዳዊት ታዬ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ መንግሥት የውጭ ባንኮች ቢገቡ ወይም ዳያስፖራው ባንክ ውስጥ አክሲዮን እንዲገዛ መፍቀድ ሊያስከትል ይችላል የሚባለውን ስጋት ቢጋራም፣ የተሰጠውን ምክንያት ሙሉ ለሙሉ አይቀበልም፡፡

‹‹ፍቃደኝነቱ ቢኖር ዳያስፖራው በግል ይህንን ያህል የባንክ ወይም የኢንሹራንስ አክሲዮን ሊገዛ ይችላል የሚል ገደብ በመጣል ዳያስፖራው በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ተሳታፊ ማድረግ ይችላል ነበር፤›› የሚል እምነት አለው፡፡

ዳያስፖራው ወደ አገር ውስጥ የሚልከውን ገንዘብ በሕጋዊ መንገድ በማስገባት ተባባሪ መሆን እንዳለበት የተጠቀሰ ሲሆን፣ እስካሁንም ከዳያስፖራው የሚገባው የውጭ ምንዛሪ ቡና ከሚያስገኘው ገቢ በሦስት እጅ ይልቃል ተብሏል፡፡

ከውጭ ወደ አገር ውስጥ በዳያስፖራው በኩል የገባውን ገቢ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ተክለ ወልድ፣ ባሳለፍነው ዓመት ብቻ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አረጋግጠዋል፡፡ ከቡና የተገኘው ገቢ ደግሞ 600 ሚሊዮን ዶላር አይሞላም ብለው፣ ይህ አኅዝ ዳያስፖራው በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ከቡና የሚልቅ እንደሆነ ያሳያል ብለዋል፡፡

የውይይቱ መድረክ ዋነኛ አጀንዳ እንዲሆን የተፈለገው በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ማድረግ ቢሆንም፣ አብዛኛው ተሳታፊ ግን በግል ደረሰቡኝ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ ከዳያስፖራው ጥያቄዎች መካከል ዳያስፖራው ኢንቨስት ለማድረግ የታክስ ቅናሽ ወይም ማበረታቻ ይሰጠው የሚለው ጥያቄ ተጠቃሽ ነው፡፡

የቤት፣ የቦታ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት መጓደልና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ የውይይት መድረኮች  የተነሱ ናቸው፡፡ በየዓመቱም ከዳያስፖራው ሲቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎች በመሆናቸውም አንዳንድ የዳያስፖራው አባላት ለዓመታት ስንጠይቅ የነበረው ጥያቄ አሁንም በድጋሚ መቅረቡ መንግሥት ለጥያቄዎቹ መልስ ለመስጠት አለመፈለጉን ያሳያል ብለዋል፡፡

ከዳያስፖራው ጋር በየዓመቱ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ሲሳተፉ እንደነበር የሚገልጹት ከአሜሪካ የመጡ አንድ ኢትዮጵያዊ፣ ከዚህ ውይይት በኋላ መልሰን የምንገናኘው በቀጣዩ ስብሰባ ነው፡፡ ቢያንስ ዳያስፖራው መረጃ የሚለዋወጥበት መድረክ የለም ይላሉ፡፡ ዛሬም ኮሚቴ በማዋቀር ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ውሳኔ ላይ መደረስ አለመቻሉንም አስረድተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ በበኩላቸው፣ ዳያስፖራው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቤቱ ነው ብለው ከኤምባሲዎች ጋር ግንኙነት በማጠናከር ብዙ ሥራ ሊሠራ እንደሚችልና የተለየ አመለካከት ቢኖርም በአገር ጉዳይ ላይ አንድ መሆን እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው በቅርቡ በተለያዩ አገሮች ከዳያስፖራው ጋር ለሚያደርገው ውይይት ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁም አሳስበዋል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ዳይሬክተር ጄነራል / መብራት በየነ እንደገለጹት፣ ዳያስፖራው መደራጀቱ ለአሠራር ምቹ ነው፡፡ መሥሪያ ቤታቸውም ተደራጅተው ለሚመጡ እገዛ ይሰጣል፡፡ በአገር ውስጥ ያሉትም ተደራጅተው ለመንቀሳቀስ እንቅስቃሴ እያደረጉ በመሆኑ ይህንንም እናግዛለን ብለዋል፡፡

በዚህ ስብሰባ ላይ ጐልቶ ከተነሱት አስተያየቶች መካከል አንዱ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው፡፡ ብዙዎቹ አስተያየት ሰጪዎች እንደጠቆሙት በተለይ በወረዳ ደረጃ የቢሮክራሲ ችግር አሁን በተግባር ላይ ለማዋል ለታቀደው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ እንቅፋት ይሆናል ብለዋል፡፡

በተለይ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ አንድ አስተያየት ሰጪ፣ እስከወረዳ ድረስ ባሉ የሥራ መስኮች በአብዛኛው የገዥው ፓርቲ አባላት መሆናቸውን ጠቁመው፣ እነዚህ ሰዎች እላይ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት በማያውቁት መንገድ የመልካም አስተዳደርን የሚያደፈርስ ሥራ ይሠራሉ በማለት የታዘቡትን ተናግረዋል፡፡

መልካም አስተዳደር እስከሌለ ድረስም የታሰበውን ዕቅድ ማሳካት ይቻላል ብለው እንደሚያምኑም አስረድተዋል፡፡ ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር በተያያዘ ለተነሱት ጥያቄዎች በውይይቱ ላይ የተገኙ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡

በተለይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ አንዱ ዕቅድ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ማስወገድ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ሌሎች አሉ የተባሉ ችግሮችን በተመለከተ ለማስተካከል ዝግጁ መሆናቸውንና ከተሰብሳቢውው የቀረቡትን አስተያየቶች በየደረጃው ለመመልከት የሚቻል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
Source: Reporter

No comments:

Post a Comment