Wednesday, December 15, 2010

የደርግ ባለሥልጣናትን ሕዝቡ ይቅርታ እንዲያደርግላቸው የሃይማኖት መሪዎች ሊለምኑ ነው

Sunday, 12 December 2010 11:31
(በታምሩ ጽጌ)
በሞት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸው ቅጣታቸውን በመጠባበቅ ላይ ያሉትን የደርግ መንግሥት ባለሥልጣናትን፤ ጉዳት የደረሰበትም ይሁን ድርጊታቸውን በታሪክ የሚያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ እንዲያደርግላቸው፣ አራት የሃይማኖት መሪዎች ታህሣሥ 16 ቀን 2003 ዓ.ም. ሕዝቡን በይፋ ሊለምኑ መሆኑን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
የቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት ይቅርታ ለመጠየቅ የሃይማኖት መሪዎቹንና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በደብዳቤ በጠየቁት መሠረት፣ የሃይማኖት መሪዎቹ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሰፊ ሥራ ሲሠሩ መቆየታቸውን ምንጮቹ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የመካነ ኢየሱስና የእስልምና ሃይማኖት መሪዎች በጋራ በመሰባሰብና ዓብይ ኮሚቴ በማቋቋም፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከክልል ባለሥልጣናትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲወያዩ መክረማቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ቤተሰቦችን ለማነጋገርና ለማሳመን የሃይማኖት መሪዎቹ ያደረጉት ጥረት ይሁንታ በማግኘቱ የሃይማኖት መሪዎቹ መደሰታቸውን የገለጹት ምንጮቹ፣ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማዳረስ ብዙ ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ፣ ዋና ዋና ተጠቂዎችንና ሰለባ የሆኑትን ቤተሰቦች በአካል ቀርቦ ከማነጋገር ጐን ለጐን የሃይማኖት መሪዎቹ ታኅሣሥ 16 ቀን 2003 ዓ.ም. በአገር አቀፍ ደረጃ ሽፋን በሚሰጡ ሚዲያዎች ቀርበው መንፈሳዊ ልመና እንደሚያደርጉና ቀኑም ‹‹የይሁንታ ቀን›› ተብሎ እንደሚሰየም ጠቁመዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዓቢይ ኮሚቴው አባል እንደገለጹት፤ የሃይማኖት መሪዎቹ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም በማረሚያ ቤት የሚገኙትን እስረኞች ሊጠይቁ በሄዱበት ወቅት፣ ‹‹እኛ በሠራነው፣ ባጠፋነውና መቀጣት ይገባቸዋል በተባለው ነገር ሁሉ የመጨረሻውን የሞት ቅጣት ተወስኖብናል፡፡ ውሳኔው ተፈፃሚ ከመሆኑ በፊት ግን ባጠፋነው ጥፋት የድርጊቱ ሰለባ ቤተሰቦች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብንና መንግሥትን ይቅርታ እንድንል፤ አዲሱ ትውልድም ወደፊት ምን ማድረግ እንዳለበት የበኩላችንን መልዕክት የምናስተላልፍበት መንገድ አዘጋጁልን፤›› በማለት በእስር ላይ የሚገኙት የደርግ ባለሥልጣናት ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው አስታውሰዋል፡፡

በመሆኑም ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገ ጥረት በተለይ የተጠቂዎች ቤተሰቦችንና መንግሥትን ለማሳመን ከፍተኛ ችግር ገጥሟቸው እንደነበር አልሸሸጉም፡፡ በተለይ ተጐጂዎቹን ለማሳመን እጅግ በጣም አስቸጋሪ የነበረውን ወቅት ቢያሳልፉም፣ በመጨረሻ ግን ይሁንታን ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው እኝሁ የኮሚቴ አባል ተናግረዋል፡፡

ይቅርታውና እርቁ ‹‹ብሔራዊ›› እንዲሆን ከኅዳር 25 ቀን 2003 ጀምሮ በየክልሉ በተለይ ጉዳቱ በብዛት በደረሰባቸው አካባቢዎች የሃይማኖት መሪዎቹ ተሰማርተው በማነጋገር ላይ መሆናቸውን የገለጹት እኝሁ የኮሚቴ አባል፤ ቀሪዎቹ የሃይማኖት መሪዎች በትናንትናው ምሽት አዲስ አበባ ውስጥ ለጋዜጠኞች ሊሰጡት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ለዓቢይ ኮሚቴው በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሰው ከውጭ ይገባሉ ተብለው ሲጠበቁ ባለመምጣታቸው ለሌላ ጊዜ መተላለፉን ተናግረዋል፡፡

ኢሕአዴግ ደርግን ደምስሶ ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ጀምሮ አገሪቱን ማስተዳደር ሲጀምር፣ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውና ለሕግ ያቀረባቸው የደርግ ባለሥልጣናት በጣም በርካታ የነበሩ ቢሆኑም፣ የተወሰኑት በሞት ሲለዩ፣ የተወሰኑት በነፃ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው በመለቀቃቸው፣ በአሁኑ ጊዜ 113 ባለሥልጣናት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡  

ከእነዚህ ባለሥልጣናት መካከል በስደት ላይ ዚምባቡዌ የሚገኙት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ከ1967-1969 ዓ.ም. የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር፣ ከ1969-1979 የኅብረሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበር፣ ከ1980 - 1983 ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ፕሬዚዳንትና የኢሠፓ ዋና ፀሐፊ ፈጽመዋል በተባሉት የዘር ማጥፋት ወንጀል የሞት ፍርድ በሌሉበት እንደተፈረደባቸው ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ ካሉት የቀድሞ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ የደርግ ዋና ፀሐፊና በኋላም የኢሕዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ሌተና ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ የቀድሞ የደርግ ረዳት ዋና ፀሐፊና በኋላም የኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ሻምበል ለገሰ አስፋው የደርግ ቋሚ ኮሚቴ አባል፣ የኢሠፓ የፖሊት ቢሮ አባልና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ እንዲሁም የትግራይ ራስ ገዝ የአስቸኳይ ጊዜ የበላይ አስተዳዳሪና ሌሎችም ከፍተኛ የደርግ መንግሥት ባለሥልጣናት ይገኙበታል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግንቦት 18 ቀን 2000 ዓ.ም. በቀድሞ የደርግ ባለሥልጣናት ላይ በሞት፣ በዕድሜ ልክና በተለያዩ የእስራት ዘመናት ውሳኔ መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ባለሥልጣናቱ የተከሰሱትና የተፈረደባቸው በ17 ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው በፈጸሙት የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው፡፡

No comments:

Post a Comment