Monday, December 13, 2010

ዊኪሊክስ ስለ ኢትዮጵያ መረጃና ደኅንነት ኃላፊ ሚስጥራዊ መረጃ ይፋ አደረገ

(13/12/10,በዘካሪያስ ስንታየሁ, ሪፓርተር)--ዊኪሊክስ ስለ ኢትዮጵያ መረጃና ደኅንነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ሚስጥራዊ መረጃ ባለፈው ረቡዕ ይፋ አድርጓል፡፡ ዊኪሊክስ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው በዚህ መረጃ አቶ ጌታቸው ድብቅና ብዙ ሰዎች የማያውቋቸው መሆኑን ገልጿል፡፡

ዊኪሊክስ ሰሞኑን ይፋ እያደረጋቸው ያሉት መረጃዎች በዓለማችን የዲፕሎማሲ 9/11 ፈጥረዋል እየተባለ ሲሆን፣ የአሜሪካንንም ዲፕሎማሲ ከባድ ፈተና ውስጥ ጥሎታል፡፡ ባለፈው ሐሙስ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ፀሐፊ ጆኒ ካርሰን በቴሌኮንፈረንስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሰሞኑ የዊኪሊክስ ክስተት በአሜሪካና በአፍሪካ ወዳጅነት ላይ ችግር አይፈጥርም፡፡

ካርሰን አክለውም፣ ከዊኪሊክስ የሚወጡት መረጃዎችም የአፍሪካና የአሜሪካንን ግንኙነት አይወክልም ብለዋል፡፡ ሆኖም ዊኪሊክስ ይህን ሁሉ ሚስጥራዊ መረጃ እንዴት ማግኘት እንደቻለ ሳይመልሱ ቀርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ የቀድሞ አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ፣ አቶ ጌታቸው በኢሕአዴግ ውስጥ ቁልፍና ወሳኝ ሰው ሲሉ እንደገለጿቸው መረጃው ያሳያል፡፡ እንደ ዊኪሊክስ መረጃ አቶ ጌታቸው ከአምባሳደሩ ጋር በግል ለአራት ሰዓታት የተወያዩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች ላይ በተለይም የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን (ኦነግ) እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባርን (ኦብነግ) በተመለከተ ኢትዮጵያ የአሜሪካንን እገዛ እንደምትፈልግ በመረጃው ተመልክቷል፡፡

አቶ ጌታቸው፣ በተቃዋሚዎች ዘንድ የአቶ ስዬ አብርሃ ተሰሚነትም እየጨመረ ስለመምጣቱ፣ በኢትዮጵያ ስላለው ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት፣ ስለ ኤርትራ ጉዳይ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ባሉ ጉዳዮች በተለይም ስለ ሶማሊያና ሱዳን ከአምባሳደሩ ጋር ተወያይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከኦነግ እና ከኦብነግ ጋር ንግግር እያደረገች መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ የአገር ሽማግሌዎች ከቡድኖቹ ጋር ያለውን ግጭት ለማቆም እየጣሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ በመሆኑ በኢትዮጵያውያን የሚመራና በኢትዮጵያውያን ትብብር የሚፈጸም መሆን እንዳለበት አቶ ጌታቸው አስታውቀዋል፡፡

በመረጃው መሠረትም፣ የአሜሪካ መንግሥት ከኦብነግ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደማያደርጉ የገለጹት አምባሳደሩ፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በኦብነግ እና በኦነግ ላይ ያላቸውን ምልከታ በቅርበት እንደሚያጠኑት ተናግረዋል፡፡ የአገር ሽማግሌዎቹ ግጭቱን ለማስቆም የሚያደርጉትንም ጥረት አሜሪካ እንደምትደግፍ አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ከአምባሳደሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ‹‹ሰማዕት ያልሆነው›› በማለት ሲገልጹዋቸው፣ ራሳቸውንም በምሥራቅ አፍሪካ ኃይለኛ መሪ አድርገው ይቆጥራሉ ማለታቸውን መረጃው ያሳያል፡፡
የኢሳይያስ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያን በመከፋፈልና በሽብር ማዳከም በመሆኑ፣ ኢትዮጵያም ይህንን ትጋፈጠዋለች ብለዋል፡፡ አቶ ጌታቸው አክለውም፣ የኢሳይያስ ጠባቂ ከዱባይ ሸሽቶ ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል፡፡ ጠባቂውም ኢሳይያስን ብቸኛና ብዙውን ሰዓታቸውን በአናጢነት ሥራዎች የሚያጠፉ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ ኢሳይያስም ከአማካሪዎቻቸው ጋር ሳይወያዩ በርካታ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፉ ጠባቂው ገልጿል፡፡ ኢሳይያስም በየቀኑ ፀባያቸው ስለሚለዋወጥ አስቸጋሪ መሆናቸውን መረጃው ያሳያል፡፡

አቶ ጌታቸው አክለውም፣ በሱዳን ጠረፍ አካባቢ በሚገኘው የሳዋ ካምፕ ውስጥ ኤርትራ 30 አማፂ ቡድኖችን የምታሰለጥን ሲሆን፣ ሲመረቁም ወደ ሱዳን፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ እየገቡ በኢትዮጵያ መረጋጋት እንዳይኖር ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

ሶማሊያን በተመለከተ አቶ ጌታቸው በአገሪቱ መረጋጋት ለማምጣት ያለው አማራጭ በብዙ ጐሳዎች ተቀባይነት ያለውን የሙስሊም ድርጅትን (ኤኤስደብሊውጄ) መርዳት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሱዳንም ከሶማሊያ ይልቅ ለአካባቢው ያለመረጋጋት ስጋት እንደሆነች አቶ ጌታቸው ገልጸው፣ በአካባቢው የእርስ በርስ ጦርነት ቢነሳ ጉዳቱ ከፍተኛ ከመሆኑም ባሻገር ተጠቃሚ የምትሆነው ኤርትራ ብቻ ትሆናለች ብለዋል፡፡

አምባሳደር ያማማቶ፣ አቶ ጌታቸው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስን የገለጹበት መንገድ ትክክል ቢሆንም፣ አቶ ጌታቸው እራሳቸው ኢሳያስን ይመስላሉ ሲሉ መግለጻቸውን ይፋ የሆነው መረጃ ያሳያል፡፡

እንደ ያማማቶ ገለጻ፣ አቶ ጌታቸው ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ውስን ሲሆን፣ ብዙ ውሳኔዎችንም በራሳቸው ይወስናሉ ብለዋል፡፡

ያማማቶ በላኩት መረጃ ላይ እንደተመለከተው፣ አቶ ጌታቸው ቁጡና ብቸኛ ሲሆኑ፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት አስቸጋሪ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ ሌሎች የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ከአቶ ጌታቸው ጋር መወያየት አስቸጋሪ መሆኑን እንደተነገራቸው አምባሳደሩ ለስቴት ዲፓርትመንቱ በላኩት መረጃ ላይ ይታያል፡፡

አሜሪካ በዊኪሊክስ ይፋ በሚሆኑ መረጃዎች ሳቢያ ከዓለም አገሮች ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን ያሻከረው ቢሆንም፣ ካርሰን በ20 የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ለሚገኙ ጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ የአፍሪካ አገሮች ያላቸውን ጥንካሬ ቀጥለው በአሜሪካና በአፍሪካ መካከል የተጀመሩ የስትራቴጂክ ምክክሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

ካርሰንም ከጋዜጠኞች ጋር ለአንድ ሰዓት የፈጀ ቴሌኮንፈረንስ ባደረጉበት ወቅት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጠን ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ሪፓርተር

2 comments:

Anonymous said...

“አቶ ጌታቸው ከ ኢሳያስ ይመሳሰላሉ”!!! ወፍራም ውሽት ነው!! ምክንያቱም ከ ኢሳያስ ሊመሳሰል የሚችለው ዲያብሎስ ብቻ ነው!!፡፡

Anonymous said...

“አቶ ጌታቸው ከ ኢሳያስ ይመሳሰላሉ”!!! ወፍራም ውሽት ነው!! ምክንያቱም ከ ኢሳያስ ሊመሳሰል የሚችለው ዲያብሎስ ብቻ ነው!!፡፡

Post a Comment