Wednesday, December 15, 2010

ከ146 ሺሕ ብር በላይ ይዛ ልትወጣ ስትል በተያዘች አሜሪካዊ ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ

Sunday, 05 December 2010 11:28
(በሚኪያስ ሰብስቤ)
የፌዴራሉ አንደኛ ደረጃ ልደታ ምድብ ችሎት ገደብና ቁጥጥር የተደረገበትን 146,683 የኢትዮጵያ ብር ይዛ ልትወጣ ስትል ተይዛለች በሚል፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባት ጥፋተኛነቷ በፍርድ ቤቱ የተረጋገጠባት አንዲት አሜሪካዊ በሦስት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ወሰነ፡፡
የ57 ዓመት እድሜ ያላት ወ/ሮ ቤኪ ሊን ብላክ ባለፈው ዓመት ሐምሌ 8 ቀን  2002 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ይዛው በነበረው ቦርሳ በተደረገው የኤክስሬይና ዝርዝር ፍተሻ በቁጥጥር ሥር መዋሏ የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

የባለስልጣኑ ዓቃቤ ሕግ የኢትዮጵን ሕጋዊ ገንዘብ በሕገወጥ መንገድ ከአገር ይዞ በመውጣት ወንጀል በፍርድ ቤቱ 10ኛ ወንጀል ችሎት ክስ መስርቶ የዋስትና መብቷ ተጠብቆ የተለቀቀችው ተከሣሽ፣ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት እንድትቀርብ ቢታዘዝም ልትቀርብ አልቻለችም፡፡ በመሆኑም ፍ/ቤቱ ጉዳዩ በሌለችበት እንዲታይ ጥቅምት 5 ቀን 2003 ዓ.ም. ትእዛዝ አስተላልፎ፣ የዓቃቤ ሕግን የሰውና የሰነድ ማስረጃ በማገናዘብ አሜሪካዊቷን በተከሰሰችበት ወንጀል ጥፋተኛ መሆኗን ህዳር 6 ቀን 2003 ዓ.ም. ውሳኔ አስተላልፎአል፡፡ ባለፈው ሳምንትም የቅጣት ውሳኔውን ሰጥቷል፡፡ ፍ/ቤቱ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተከሳሽን አፈላልገው ቅጣቷን እንድትፈጽም ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክቧት አዟል፡፡ ቤኪ ሊን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተመሳሳይ ወንጀል ጥፋተኛ የተባለች ሁለተኛ አሜሪካዊ ስትሆን፣ ከአራት ወራት በፊት ማይክል ኔሜዝ የተባለ አሜሪካዊ 100,000 የኢትዮጵያ ብር ይዞ ሊወጣ ሲል በመያዙ በ1 ዓመት ከሁለት ወር እስራት እንዲቀጣ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ሳምንት ይኸው ፍርድ ቤት ሁሴን አደም የተባለ ኢትዮጵያዊ ስድስት  ሺሕ ብር ይዞ ሊወጣ ሲል ተይዟል በሚል ክስ ተመስርቶበት ጥፋተኛ ሆኖ በመግኘቱ፣ በአንድ ዓመት ከሁለት ወር እስራት አንዲቀጣ ወስኗል፡፡ ሁሴን አደም ጥፋተኝነቱን ለፍርድ ቤቱ በማመኑ፣ ከዚህ ቀደም የጥፋተኝነት ሪከርድ ያልነበረበት በመሆኑና በቅርቡም በውጪ አገር የሩጫ ውድድር ስላለበት የቅጣት ውሳኔው በሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ እንዲገደብ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

በአገሪቱ ሕግ መሠረት የጉምሩክ ሥርዓት ያልተፈጸመበትን ከሁለት መቶ ብር በላይ ይዞ ከአገሪቱ 15 ኪሎ ሜትር ወሰን ውጭ መገኘት በወንጀል የሚያስጠይቅ ጥፋት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment