Friday, September 16, 2011

በቅርቡ በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች የአገሪቱን ሰላምና ጸጥታ ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ የተደረሰባቸው ናቸው

(መስከረም 5 ቀን 2004 (አዲስ አበባ, ኢዜአ)--በቅርቡ በፌዴራል ፖሊስና በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የጋራ ጸረ ሽብር ግብረ ኃይል በቁጥጥር ሥር የዋሉት አምስት ግለሰቦች የአገሪቱን ሰላምና ጸጥታ ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ በተጨባጭ ማስረጃ ስለተደረሳቸው እንጂ፤ በፖለቲካ ፓርቲ አባልነታቸው አለመሆኑ የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

በፌዴራል ፖሊስ የማዕከላዊ መረጃና የወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክተርና ረዳት ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል እንዳሉት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች የአገሪቱን ሰላምና ጸጥታ በማደፍረስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ በፌዴራል ፖሊስና በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የጋራ ጸረ ሽብር ግብረ ኃይል ስለተደረሰባቸው ነው።

ተጠርጣሪዎቹ የፖለቲካ መሥመራቸውን በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለማራመድ በይፋ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመጠቀም በህቡዕ ለሚያከናውኑት ሕገ ወጥ የሽብር ሴራ ሽፋን በማድረግ ሲጠቀሙ እንደቆዩም ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ ግንቦት 7 ከተባለው አሸባሪ ቡድን ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንደነበራቸውና አገሪቱን የሽብርና የሁከት ቀጣና ለማድረግ ከሚዶልቱ የውጭ ኃይሎች ቀጥተኛ እገዛና ድጋፍ እያገኙ እንደነበርም የተሰባሰቡ የስለላ ማስረጃዎች በግልጽ ማረጋገጣቸውን ረዳት ኮሚሽነር ደመላሽ አመልክተዋል።

ረዳት ኮሚሽነሩ እንዳሉት ግለሰቦቹ በአዲሱ ዓመት መላ አገሪቱን ተከታታይ ሽብርና ትርምስ ውስጥ ለመክተት ሲያቅዱ እንደቆዩም በተደረገው ክትትል ተደርሶባቸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በሽብር ተግባራት ለሚተባበሯቸው የውጭ ኃይሎችም መረጃ በማቀበል የስለላ ሥራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውንም መረጃዎች እንደሚያሳዩ ረዳት ተናግረዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው በሽብር ሴራ ተጠርጥረው የተያዙት ግለሰቦችን በተመለከተ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥት የሚወስዳቸውን የወንጀል ክትትልና መከላከል እርምጃዎችን ያለ አግባብ ማውገዛቸው አሳዛኝ ነው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያወጧቸው የመግለጫ ጋጋታዎች ፋይዳ ቢስና አላስፈላጊ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ፖርቲዎቹ ዓላማቸውን በነጻነት ለማራመድ ዋስትና የሰጣቸውን ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት ሕልውና አደጋ ላይ ለመጣል ከሚጥሩ ኃይሎች ራሳቸውን ማጥራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

የፌዴራል ፖሊስና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የጋራ ጸረ ሽብር ግብር ኃይል ወደፊትም የኅብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ የሚያከናውናቸው ተግባሮች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በወንጀሉ ተጠርጥረው በጋራ ጸረ-ሽብር ግብረ ኃይሉ በቁጥጥር ሥር የዋሉት አንዱዓለም አራጌ፣ዘመኑ ሞላ፣ናትናኤል መኮንን፣አሳምነው ብርሃኑና እስክንደር ነጋ የተባሉት መሆናቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  


Related topics:

No comments:

Post a Comment