Friday, September 16, 2011

‹‹ኢትዮጵያ በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባትም ሆነ ከሌሎች ጣልቃ ገቦች ጋር የመተባበር አቋም የላትም» - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት

(2011-09-16, አዲስ አበባ, ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባትም ሆነ ከሌሎች ጣልቃ ገቦች ጋር የመተባበር አቋም እንደሌለው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

ጽሕፈት ቤቱ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የሰጠውን የተሳሳተ መረጃና በዊክሊክስ የተሠራጨውን ሪፖርት በሚመለከት ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከመልካም ጉርብትና ባሻገር በአጐራባች አገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባትም ሆነ ከሌሎች ጣልቃ ገቦች ጋር የመተባበር አቋም የለውም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓለም ግልፅ ባደረገው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው አንድን ሉዓላዊ መንግሥት በሌላ የመተካት ኃላፊነት የአገሩ ሕዝብ እንጂ የማንም የውጫዊ ኃይል ተልዕኮ እንዳልሆነ በግልፅ ማስቀመጡን ያስገነዘበው መግለጫው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሐምሌ 2 ቀን 2001 . ለአሜሪካኖች «የበሽርን መንግሥት አስወግዱ» የሚል ምክር እንደሰጧቸው በማስመሰል ዊክሊክስ ኤምባሲውን ዋቢ በማድረግ መግለጹን ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጥን ወይም የመንግሥት ግልበጣን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው አንድ አካል አድርጐ ከሚመለከተው የአሜሪካ መንግሥት ጋር መሠረታዊ ልዩነት እንዳለው መግለጫው አብራርቷል።

በቅርቡ በተለቀቀው የዊክሊክስ መረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከአሜሪካ መንግሥት አምባሳደሮችና በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ኃላፊዎች ጋር በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ አደረጉት የተባለውን ውይይት አዲስ አበባ ተቀማጭ የነበሩ አምባሳደሮች እንዴት ሪፖርት ያደርጉ እንደነበር ማቅረቡን ጠቁሞ፤ ሪፖርቱ ዶክተር መረራን አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ አድርጐ ካቀረበው ወሬ ጀምሮ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮቹ አገኘሁት የሚለውን መሠረተ ቢስ መረጃ ይዞ መቅረቡን አትቷል።
የኢትዩጵያ ፕሬስ ድርጅት
 

No comments:

Post a Comment