Friday, September 16, 2011

ከመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

(መስከረም 4 ቀን 2004 (አዲስ አበባ ,ኢዜአ)--ከመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የሰጠውን የተሳሳተ መረጃ በማስመልከት የተሰጠ መግለጫ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአለም ዙሪያ የሚገኙ የተባበረው የአሜሪካ መንግሥት ኤምባሲዎች ለአገራቸው ያስተላለፏቸው ልዩ ልዩ መረጃዎች ዊክሊክስ በተባለው ተቋም በስፋት እየተናኙ ይገኛሉ።

በቅርቡ በተለቀቀው የዊክሊክስ መረጃ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ከአሜሪካን መንግሥት አምባሳደሮችና በየጊዜው ወደ ኢትዮጰያ ከመጡ ኃላፊዎች ጋር በልዩ ልዩ ጉዳዩች ላይ አደረጉት የተባለው ውይይት አዲስ አበባ ተቀማጭ በነበሩ አምባሳደሮች እንዴት ሪፖርት ይደረግ እንደነበር ቀርቧል።

ሪፖርቱ አዲስ አበባ የሚገኝው የአሜሪካን ኤምባሲ ዶክተር መራራን አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ አድርጎ '' የኢትዮጵያ መንግሥት እራሱ ከገደላቸው በኋላ ለአሸባሪነት ስራ ያዘጋጁት ፈንጂ በእጃቸው ላይ እያለ ፈንድቶ የሞቱ በማስመሰል ለማደናገር ሞክሮዋል በማለት '' ካቀረበው ወሬ ጀምሮ በተለያዩ የመረጃ ምንጮቹ አገኙሁት የሚለውን መሰረተቢስ መረጃ ይዞ የቀረበ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ዜናዊ ሐምሌ 2 ቀን 2001 . ለአሜሪካኖች '' የበሽርን መንግሥት አስወግዱ''የሚል ምክር እንደሰጣቸው በማስመሰል በዚሁ የዊክሊክስ ህትመት ላይ ኤምባሲው ዋቢ ተደርጎ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩለ ደግሞ ኤምባሲው ወደ አገሩ ባስተላለፈው በዚያው መልዕክት ላይ በአንድ እራስ ሁለት ምላስ እንዲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'የበሸርን መንግሥት የማስወገድ አማራጭ የማይሰራ እንደሆነ'' ማውሳታቸውን ገልጿል፡፡

ከዚህም በመነሳት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለአሜሪካን መንግሥት ተወካዮች መንግሥታቸው ''የሱዳን መንግሥት በደቡብ ሱዳንና በዳርፉር ጉዳይ ላይ ሊያከብረው የሚገባውን ግልጽ መዳረሻ በማስቀመጥ የሱዳን መንግሥት የመከበብ መንፈስ እንዳይሰማው ማድረግ እንዳለበት'' መምከራቸውን ያወሳል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓለም ግልጽ ባደረገው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው የአንድን ሉዓላዊ አገር መንግሥት በሌላ የመተካት ኃላፊነት የየአገሩ ሕዝብ እንጂ የማንም ውጫዊ ኃይል ተልእኮ እንዳልሆነ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ በዚህ ጥያቄ ላይ የመንግሥት ለውጥን ወይም ግልበጣን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው አንድ አካል አድርጎ ከሚመለከተው የአሜሪካ መንግሥትም ጋር መሰረታዊው ልዩነት አለው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ዜናዊ በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በተወያዩበት ጊዜ ያቀረቡት ይህንኑ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ፖሊሲና አቋም ብቻ ነው።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ''አሜሪካኖች በሱዳን ህዝቡን ተክተው የበሽርን መንግሥት የማሰወገድ ሚና ሊጫወቱ እንደማይገባ'' አጥብቀው ከማውሳታቸውም በላይ የመንግሥት ለውጥ ወይም ግልበጣ ፖሊሲን ኢትዮጵያ እንደምትቃወም ደጋግመው ግልጽ አድርገዋል።

ከውጭ የሚደረግ ማንኛውም የመንግሥት ግልበጣ ሱዳንን ብቻ ሳይሆን አካባቢያችንን የማተራመስ ዉጤት እንደሚኖረው ጭምር የሚገነዘበው የኢትዮጵያ መንግሥት ከመልካም ጉርብትና ባሻገር በአጎራባች አገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባትም ሆነ ከሌሎች ጣልቃ ገቦች ጋር የመተባበር አቋም የለውም፡፡

ኢትዮጵያም ሆነች ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ዜናዊ የውጭ ኃይሎች ፕሬዚዳንት ኡመር አልሸርን በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ከሰው ለማስቀጣት ያደረጉትን የተሳሳተ እንቅስቃሴ በጥብቅ ተቃውመዋል፡፡

በዚህም ሳይወሰኑ በአፍሪካ ላይ ማንኛውንም ዓይነት የውጭ ሞዴል ለመጫን የሚደረገውን ጥረት እንማይቀበሉ ደጋግመው አስታውቀዋል፡፡

በዊክሊክስ በተለቀቀው ሪፖርት መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ከአሜሪካን መንግሥት ተወካዩች ጋር ዴሞክራሲን በተመለከተ ሐምሌ 2 ቀን 2001 . ላይ ባደረጉት ውይይት ያላቸውን አቋም ሲያብራሩ '' የምእራቡ ዓለም ዴሞክራሲና የልማት አቅጣጫ ከውጭ መጥቶ በሌሎች አገሮች ላይ በግድ ሊጫን የማይችልና የማይገባው ነው'' በማለት በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪ በዚሁ በዊክሊክስ ላይ ሪፖርት እንደተደረገው'' የተባበረው የአሜሪካ መንግሥት የቆየ አቅጣጫ የተሳሳተና በአፍሪካ ውስጥ አገር በቀል ዴሞክራሲ እንዳይፋፋ እድል የሚከለክል ነው '' ፡፡ በማለት ለአምባሳደሮቹ እንደገለጹት ኢትዮጵያ መቼም ይሁን የትም ከውጭ የሚገፋን የመንግሥት ለውጥና ግልበጣን ደግፋ እንደማትቆም ያላትን አቋም ግልጽ ታደርጋለች፡፡

ይህን የመሰለ አቋም ያለው መንግሥት የአሜሪከንን የመንግሥት ለውጥ ወይም ግልበጣ አቅጣጫ ከመቃወም በመለስ የመደገፍ ቅኝትም ሆነ ሙከራ ሊኖረው ይችላል ተብሎ አይጠበቅም፡፡

ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ እንደሚባለው በወቅቱ ሪፖርቱን ለአገራቸው መንግሥት ለማሳለፍ የቸኮሉትና የተጣደፉት አምባሳደር ለመንግሥት ቅየራ ፖሊሲያቸው በጥድፊያ አጋር ሲያፈላልጉ የተነገረውን በደንብ ስላልተገነዘቡ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ የሱዳንንም ሆነ የየትኛውንም የጎረቤት አገር ህዝብ በመተካት የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት አስባ አታውቅም፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  

Related topics:

No comments:

Post a Comment