Saturday, July 14, 2018

የቀን ጅቦች የትም አሉ

(July 07(አጀንዳ ))--በየዕለቱ በፍጥነት የሚለዋወጠው የፖለቲካችን ሁኔታ በመሰረታዊ ለውጦች እየታጀበ ይገኛል፡፡ ለመጣው ለውጥና ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም እንዲሁም ለተፈጠረውም ሀገራዊ መግባባት የኢሕአዴግ ጥልቅ ተሀድሶ የድርሻውን አበርክቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድም የመሪነት ሚናውን በብቃት በመወጣት ከጎረቤት አገራት ጋር ሰላም ለመፍጠር ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር፤ ለጉብኝት ሲሄዱ በተለያየ ምክንያት ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲፈቱ ማድረጋቸው ለዜጎች የተሰጠውን ክብር ያመላከተ ነው፡፡

በውጭ ሀገራት በፖለቲካ ስደት የሚገኙ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች የጠብመንጃ ትግል ውስጥ የነበሩትንም ጨምሮ ወደሀገራቸው ገብተው በሰላም እንዲኖሩ፣ እንዲሠሩና ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲያራምዱ እንዲሁም አላማቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያራምዱ የተመቻቸው ዕድል የኢህአዴግ የተሀድሶ ውጤት ነው፡፡ በውጭ የሚገኙ የተለያዩ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ተቃዋሚ ሚዲያዎች ወደሀገራቸው ገብተው እንዲሠሩ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ይህም በሀገራችን የሰለጠነ ዴሞክራሲያው ባሕል እንዲያብብና እንዲገነባ ኢሕአዴግ በጥልቅ ገምግሞ በወሰነው ውሳኔ መሰረት የተከናወነ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በመሪነት በቆዩባቸው አጭር ጊዜያት በሀገር ውስጥ የሚጠቀሱ ለውጦችን ያስከተሉ፤ ሰላምና መረጋጋትን ያመጡ፤ ኢትዮጵያዊ መተሳሰብ መከባበርና አንድነትን ያጎለብቱ ሥራዎች ሠርተዋል፡፡ ሕዝቡም የመከፋፈልንና የመበታተን ስጋትን ሙሉ በሙሉ አውግዞ በመደመር የለውጡን ሂደት ለማስቀጠል በአንድነት ጸንቶ ቆሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩትን የለውጥ ሂደት ለማስቀጠል በርካታ ሕዝብ በራሱ ተነሳሽነት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም አደባባይ ወጥቶ ለመሪው ያለውን ድጋፍና አድናቆት ገልጿል፡፡ በዚያው ስነስርዓት ላይ የቦንብ አደጋ ለማድረስ በጥናትና እቅድ ተቀነባብሮ የነበረው ሴራ በዜጎች ርብርብና መስዋእትነት ከሽፏል፡፡ ብዙዎች በቦምብ ፍንዳታው ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ የተወጠነ መሆኑን ሕዝቡ በሚገባ ተረድቶታል፡፡

ድርጊቱ በምርመራ እየተጣራ ሲሆን፤ ተጠርጣሪ ግለሰቦች ለአደጋው መፈጸም ክፍተት ፈጥረዋል የተባሉ የፖሊስ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየት ጀምሯል፡፡ በየትኛው መልኩ ቢሆን የተጀመረውን ሕዝባዊ ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ማቆምም ሆነ መግታት አይቻልም፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ የሚያደረጉት ተመሳሳይ ታላላቅ ሕዝባዊ ሰልፎች በባሕርዳር የተደረገውን በሺዎች ያሳተፈ ግዙፍ ሕዝባዊ ሰልፎች ጨምሮ በክልሉ ውስጥም በሌሎች ክልሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጥለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድም ለሕዝቡ ያላቸውን አክብሮትና ድጋፍ አስተላልፈዋል፡፡ የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ እየተራወጡ ያሉት ኃይሎች ዛሬም ከሴራቸው አልታቀቡም፡፡ ሕዝቡ ነቅቶ እንዲጠብቅና እንዲከላከል መንግሥት ጥሪ አስተላልፏል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ፀጉረ ልውጥ ሰዎች ሰርገው በመግባት ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሩጫ ላይ መሆናቸው ስለታወቀ መላው ዜጋ እንግዳ ሰዎችን በአካባቢው ሲያይ ነቅቶ እንዲከታተል ጉዳዩንም ለጸጥታ አካላት ፈጥኖ እንዲያሳውቅ ጥሪ የተላለፈ ሲሆን፤ ይህን አገራዊ ግዴታ መወጣት ለውጡን ለማስቀጠል ጉልህ ሚና ያበረክታል፡፡

በአገሪቱ ትርምስ የመፍጠር ሴራና ደባ የሚከናወነው በሀብት ዘረፋና በሙስና ተሰማርቶ የነበረውና ተጠያቂነት ይመጣብኛል ባለው አካል እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚያ በፊት ሀገር ላተራምስ፤ ሕዝቡንም በጎሳ በሃይማኖት እርስ በእርስ በማጋጨት በአራቱም ማእዘናት እሳት በመለኮስ ሀገሪቱን የማትወጣው ቀውስ ውስጥ መክተት አለብኝ ብሎ የወሰነ አካል ርዝራዥ አሁንም እንደሚኖር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እነዚህን ትርምሱ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች የቀን ጅቦች ያሏቸው ሲሆን፤ በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የተሰገሰጉ የተፈጠሩበትንና የተወለዱበትን ሕዝብ የማይወክሉ ናቸው፡፡ በተለይ ድርጅታቸውና መንግሥት ለሕዝብ እንዲሠሩ የሰጣቸውን የኃላፊነት ወንበር በመጠቀም በዘረፋ ውስጥ ተሰማርተው የኖሩ ሕገወጥ ሀብት ያካባቱ ሰዎች የኢሕአዴግ አባል ድርጅት በሆኑት ብአዴን፣ኦሕዴድ፣ ደኢህዴንና ሕውሐት ውስጥ የነበሩ ግለሰቦችን ያካተተ ነው፡፡ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጀምሮ በየደረጃው እስከ ዝቅተኛው ኃላፊነት ድረስ በመረብ የተሳሰረውን በቡድን የደራጀ ኃይል ይመለከታል፡፡

ለዚህ ነው የቀን ጅቦቹ ሕዝብን አይወክሉም፤ በግለሰቦች ወንጀልና ጥፋት ሕዝብ ስሙ ሊነሳ በጅምላ ሊወነጀል አይገባም የምንለው፡፡ የቀን ጅቦች በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ አሉ፡፡ የተፈጥሮው ጅብ በሁሉም ክልሎች እንዳለ ሁሉ፤ በዘራፊነትና በበልቶ አይጠግቤነት የሚታወቁት የቀን ጅቦችም በሁሉም ክልል ይገኛሉ፡፡ ይህ በውል ሊታወቅ ጥንቃቄ ሊደረግበትም የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

በጅምላ መወንጀል በስሜታዊነት ጥላቻ ውስጥ በመዘፈቅ መኮነን ሊቆም ይገባዋል፡፡ ለሀገር የለፉ የደከሙ ዛሬ ለተደረሰበት ልማትና ዕድገት ሳይታክቱ የሠሩ ሰዎችን ማመስገን ድካማቸውን መሬት አለመጣል ጥፋተኞችን እንደግለሰብነታቸው በተጨባጭ ማስረጃ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት መንግሥት በጥንቃቄ እየሠራ ይገኛል፡፡

በጥላቻ ስሜት ተዘፍቀው በየሶሾል ሚዲያው የከፋ የስም ማጥፋትና የዘር ጥላቻ የሚረጩ ግለሰቦች ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና ጥፋት እንዲከሰት ለማድረግ በመሮጥ የመደመርን፣ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የሰላምና የይቅርታ መንፈስ የሀገራዊ መቻቻልን መልካም ጅምር ከማደፍረስ ቢታቀቡ ይመረጣል፡፡ የመደመር መንፈስ ጥላቻን በቀልን ጥፋትን የሀሰት ውንጀላን በጎሳና በዘር ላይ የሚደረግ ዘመቻና ማነሳሳትን አያስተናግድም፡፡ አይቀበልም፡፡

ከጥንትም ሆነ ከቅርቡ አስከፊ ታሪካችን በጠላትነትና በጥላቻ ከመተያየት፣ ከመጠፋፋት፣ ከመባላላት፣ ከመናቆር፣ ከመገዳደል ወጥተንና ተላቀን በፍቅር፣ በሰላም፣ በይቅርታ ተደምረን ሀገራችንን በአዲስ መንፈስ በጋራ እንለውጣት፣ እንገንባት፣ ተሳስበን፣ ተዋደን፣ ተከባብረን እናሳድጋት በሰላም እንኑር ነው የመደመር መንፈስ መርሕ፡፡ ዛሬም ጥላቻን መከፋፈልን የዘረኝነትና የጎጠኝነት እኩይ በሽታን የሚያራምዱ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨትና ለማጣላት የሚንቀሳቀሱ የሀሰት ፈጠራ ወሬ የሚነዙ ከሰላምና ከአብሮነት ይልቅ በቀል አግተው ለጥፋት የሚያሴሩት ሁሉ ከመደመር ሂደት ውጪ ናቸው፡፡

የአለፈውን ሁሉ እንርሳ በአዲስ መንፈስ እንነሳ ማለት ቂም እያሰላን ቁስሉን እያከክን መቆዘም አይደለም፡፡ በመደመር መንፈስ ታድመን ወደፊት ሀገራዊ ተስፋን ሰንቀን ነገን ብሩህ አድርገን ማየትና ለዚህም መሥራት መረባረብ መትጋት ማለት ነው፡፡ ኋላቀር ከሆነ ትውልድና ሀገርን ከገደለ አስተሳሰብ በመላቀቅ ወደፊት መትመም ነው መደመር፡፡ መልሶ ጨለማ ውስጥ ከሚከት አስከፊ አስተሳሰብ መፅዳትም ነው፡፡ መደመርን የሚያደናቀፍ ከመደመር የሚቀንስ የመደመርም እንቅፋት የሆነ እሳቤ እስከወዲያኛው እንደ አረም ተነቅሎ ሊጠፋ ይገባል፡፡

የዜጎች ዴሞክራሲዊ መብቶች እንዲከበሩ የፖለቲካ ምሕዳሩ እንዲሰፋ ኢሕአዴግ እየሠራ ያለው የተሻለች ሀገር ለመፍጠር ነው፡፡ ይህን በየደረጃው ለመከወን ሕግና ስርዓት የግድ መከበር አለበት፡፡ የለውጡ ሂደት ወደፊት እንዲራመድ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንዲሸጋገር የሚያደርገው ሕዝብ ነው፡፡ በየሰፈሩ በየመንደሩ በሥራ ቦታ በአደባባዮች በየትኛውም ቦታ ሕግና ስርዓት ሲከበር ለውጡ መሬት የሚረግጠው፡፡

በስፋት የጥበቃዎች መላላት፣ ጸጥታ አስከባሪዎች ሕገወጥ ድርጊት ዘረፋና የመሳሰለውን እያዩ እንዳላዩ ማለፍ፣ የነጣቂዎችና የማጅራት መቺዎች መበራከት፣ በአንዳንድ ቦታዎች ዘረፋ ማካሄድ በስፋት እየታየ ሲሆን፤ መንግሥት የዜጎቹን ሕይወትና ንብረት የመጠበቅ ግዴታና ኃላፊነቱን እንደማይወጣ ተደርጎ እንዲታይ ሆን ተብሎ እየተሠራ ያለውን አሻጥር ሕዝብ ተረድቶ እርስበእርሱ በመተባበር በየአካባቢው ጥበቃውን ማጠናከር፣ ወንጀለኞችንም አድኖ ለሕግ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ የቀን ጅቦቹ አንዱ ሴራ ይኸው ነውና ሕዝቡ ሊያከሽፈው ይገባል፡፡ የለውጡ ሂደት ጠባቂና ከግብ አድራሹ ሕዝብ ነው፡፡ ኢሕእዴግ የጀመረውን የስኬት ጉዞ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (መሐመድ አማን )

No comments:

Post a Comment