Saturday, July 14, 2018

ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ያደረገ ኢትዮጵያዊ መሪ

(July 14, (አጀንዳ ))--አንዳንድ አንደበተ-ርቱዕ ግለሰቦች በንግግራቸው የሚያስተላልፉት ጣፋጭ መልዕክት የሰዎችን ህሊና እንደ መድኃኒት የሚፈውሱ ናቸው፡፡ የሚፈውሱ ብቻ ሳይሆኑ የዘወትር የህሊና ስንቅ ሆነው የሚያገለግሉና አብረው የሚዘልቁም ናቸው፡፡ እነዚህንም በአዕምሯችን የተቀረጹ መልዕክቶችን እንርሳ እንኳን ብንል ፈጽሞ የማይረሱ፣ ደግሞም ሊረሱ የማይገቡ ቁም ነገሮች ስለሆኑ የትዝታ ሐውልቶችን በህሊናችን ተክለው ያልፋሉ፡፡

የመልዕክቶቹ ባለቤቶች ምድራዊ የህይወት ዘመናቸውን አጠናቀው «ለወዲያኛው ዓለም ሲታጩም» ከነመልዕክቶቻቸው በቀጣዩ ትውልድ ዘንድ (የነርሱ ፍላጎት ባይሆንም) ሲወደሱና ሲከበሩ ይኖራሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም መልዕክቶቻቸው ሰዎች ሲከፋቸው ብቻ ሳይሆን በጥላቻ በደስታና በእርቅ ዘመን ሁሉ ሳይቀር ስማቸውን እየጠሩ ለጥንካሬ፣ ለይቅርታ፣ ለሰላም የሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡

ለዚህም አብነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን በጥቂቱ ብናነሳ አብርሃም ሊንከን፣ ማሪያ ቴሬዛ፣ ማህተመ ጋንዲ፣ ኒልስን ማንዴላ፣ … ወዘተን ማውሳት ይቻላል፡፡ የእነዚህ ታዋቂ ሰዎች ስም በየዘመናቱ ከሌሎች ገዝፎ እየተነገረ ያለው ያለ ምንም ምክንያት አይደለም፡፡ በራሳቸው የራሳቸውን ሙገሳና ዕውቅና ፈልገውም ወይም ዝናችን ይነገርልን ብለው ለደጋፊዎቻቸው የቅስቀሳ ገጸ-በረከት አዝንበው አይደለም፡፡ አንዱን ጠቅመው ሌላውን ለመጉዳት አስበውና አቅደው በመንቀሳቀሳቸውም አይደለም፡፡ እንደ ማንኛችንም ፍጡራን ሰው ሆነው ተወልደው፣እንደ ማንኛችንም የሰብዓዊ ሰውነት ሰብዕና ተላብሰው ነገር ግን በሰዎች መካከል ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከጠላትነት ይልቅ ወዳጅነትን፣ ከቅርብ አሳቢነት ይልቅ እሩቅ አሳቢነትን፣ ከጠባብነት ይልቅ አብሮነትን፣ ከበቀል ይልቅ ይቅርታን፣ ከመጠራጠር ይልቅ መተማመንን ለወዳጆቻቸው ብቻ ሳይሆን ለጠላቶቻቸው ጭምር የህይወት መስዋዕትነትን በሚያስከፍል ሁኔታ በቆራጥነት ማስተማር በመቻላቸው ነው፡፡

አስተምህሮዎቻቸው ለሰው ልጆች ዘላቂ ህይወት ድንበር ዘለል መልዕክቶችና አስፈላጊ እንዲሆኑ ሳይታክቱ ስለሠሩ ነው፡፡
እነዚህም ተናጋሪዎች የሀገር መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ባለሀብቶች፣ ምሑራን፣ ወይም ሌሎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታሰባል፡፡ ከእነዚህም ታዋቂ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እንደ ማህበራዊ አመጣጣቸው ሲታዩ በተፈጥሮ የተሰጣቸው ልዩ ችሎታ ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ሲታመን ሌሎቹ ደግሞ ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች (ከአስተዳደግ፣ ከትምህርት ቤት፣ ከሚኖሩበት ማህበረሰብ፣ በግል ከሚያደርጉት አታካች ጥረት፣…. ወዘተ) ከሚያገኟቸው ውሎ አደር ክንዋኔዎች ወይም ከሚዳስሷቸው ክስተቶች ይህንኑ አቅምና ችሎታ እንዳገኙ ይታመናል፡፡

ይህንኑ ችሎታና አጋጣሚ አንዳንዶቹ የራሳቸውን ዝናና ክብር ማግዘፊያ አድርገው ሲጠቀሙ ቀሪዎቹ ደግሞ ይህንኑ «ዝና» ሌሎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲቀበሉና እንዲታዘዙላቸው ወይም እነርሱ የምሉትን ብቻ አምነው ሲሰብኩ እንዲኖሩ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ይህንን ለማድረግም የማይፈነቅሉት ድንጋይ፣ የማይወጡት ዳገትና የማይወርዱት ቁልቁለት የለም፡፡ የሚገርመው ግን ይህ ክብርና ዝና ጊዜያዊ እንጂ ዘላለማዊ መሆኑን በአግባቡ ባለመረዳት እዚያው «ተሰቅለው» የቀሩ ስለመኖራቸው በርካታዎችን ስም እየጠቀሱ ዋቢ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በጥቂቱ ስለ መልካም ሰዎችና ስለ መልካም ሥራዎቻቸው የዚህን ያህል ካወሳሁ ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳዬ ልመለስ፡፡

የአሜሪካ ዝነኛ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን በዘመናቸው የሚከተለውን አባባል ተናግረው ነበር ይባላል «የአንድ ሀገርና መንግሥት ባህል በህዝቡ ልብና ህይወት አብሮ ይዘልቃል፡፡» እኚሁ ፕሬዚዳንት በመቀጠልም «ስለሚኖርባት ሀገሩ ኩሩ የሆነ ዜጋ ማየት እፈልጋለሁ፣ የሚኖርባት ሀገሩ የምትኮራበትን ሰው ማየት እፈልጋለሁ፡፡» እርሳቸው አሜሪካዊ ቢሆኑም ይኸው አባባላቸው ለኛም ለኢትዮጵያውያን ጠንካራ መልዕክት አለው፡፡ ሀገራችን በኛ እንድትኮራ፣ እኛም በሀገራችን እንድንኮራ ማድረግ የሁላችንም የዘወትር ጥረት ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ የሁላችንም የዜግነት ኃላፊነትም ግዴታም ይመስለኛል፡፡ ነውም፡፡ ለዚህም ሀገራዊ ተልዕኮ ሁላችንም በሁሉም ስፍራና ጊዜ ቁርጠኛ ሆነን መሥራት የሚጠበቅብን ይሆናል፡፡

በበኩሌ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚኮሩበትን መሪ በእርግጠኝነት አግኝተናል ማለት እችላለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ያደመቀ ኢትዮጵያዊ መሪ ብቅ ብለውልናል፡፡ እኚህ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ናቸው፡፡ ለራሴ ስለ ዶ/ር አብይ አንዳንድ ነገር መጻፍ ስፈልግ የቱን ጽፌ የቱን መተው እንዳለብኝ ብዙ ጊዜ ግራ ይገባኛል፡፡ የቱን አስቀድሜ የቱን ማስከተል እንዳለብኝም እንዲሁ፡፡ በየጊዜውና በየመድረኩ ከአንደበታቸው እንደ ጅረት ውኃ የሚፈልቁ ጣፋጭና አስተማሪ ሀገራዊ ይዘት ያላቸው መልዕክቶች ከተፈጥሮ የተገኙ ወይስ በአጭር ጊዜ በራስ ጥረት የሚሉ ጥያቄዎችን እንድንጠይቅ የሚያስገድዱ ናቸው፡፡ ለማንኛውም ግን ኮርቼባቸዋለሁ፡፡ ኧረ ምን እኔ ብቻ! የሁላችንም ኩራት እንጂ፡፡

እያንዳንዱን መድረክ በሚመጥን ቋንቋ የሚናገሩት ቃላት፣ የሚያስተላልፉት መልዕክት አዕምሯችንን እየጠገነና እየፈወሰ፣ እያፋቀረንና እያቀራረበ ነው፡፡ ያለፉ ዓመታትን ቁርሾ ብቻ ሳይሆን የዘመናት አኗኗራችንን ፈትሸን ወደፊት እንዴት በአብሮነት መጓዝ እንዳለብን ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ሀገር ዜጎች እያሳዩን ነው፡፡ በእርግጠኝነት አሳይተዋልም፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ተበጣጥሳና ተሸራርፋ ልትወቅድ ምንም ያህል ያልቀራትን ክቡርና ውድ ሀገራችንን ከገደል አፋፍ አድነው አንድ አድርገዋታል፡፡ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ዓለም ተቃዋሚዎችን ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ እንዲህ ሀገራዊ ሁኔታው ፈጣንና ተለዋዋጭ የፖለቲካ ትኩሳት ባለበት ወቅት ከአንደበታቸው በሚፈልቁ ህያው አባባሎች ብቻ ከሁሉም በሁሉም አቅጣጫ እንዲህ ዓይነቱን ልባዊ ድጋፍ ማግኘት ዕድለኛ ናቸው ያሰኛል፣ ዕድለኞች ነን ከማለት ሌላ ምን ሊባል ነው! የሚጠቅመንና የሚሻለን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ዕድሜ ይስጣቸው፣ያዝልቅልን ማለት ነው፡፡

ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚወዷቸውና የሚያከብሯቸው ማህተመ ጋንዲ በአንድ ወቅት እንደተናገሩት «ከሁሉም ነገር የተሻለ ነው የሚባለው ለራስ ጥቅም ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል መስዋዕት መሆን ነው» ይላሉ፡፡ እኚሁ አባት አክለውም «ነገ ሟች መሆንህን አውቀህ ኑር፣ እስከ ወዲያኛው ነዋሪ መሆንህን አውቀህ ተማር» ብለዋል፡፡ እኚህ መሪችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ሙስናን አጥብቀው ይፀየፋሉ፣ጠባብነትንና ዘረኝነትንም አምርረው ይታገላሉ፣ ኢትዮጵያዊነት ደምቆና ተውቦ እንዲታይ ይፈልጋሉ፣ ሀገራዊና አህጉራዊ የጋራ ተጠቃሚነት ጎልቶ እንዲወጣ ይመኛሉ፡፡ በሙስሊሙና በክርስቲያኑ፣ በደኃውና በሀብታሙ፣ በነጩና በጥቁሩ፣ በወንዱና በሴቱ፣ በከተሜውና በገጠሬው ኢትዮጵያዊነት ደምቆ እንዲታይ ይፈልጋሉ፡፡ ታዲያ እኚህን መሪ በተግባር ያልደገፈ ስብዕና ለመቼ ሊሆን ነው? ነገን መጀመር የምንችለው እኮ ከዛሬ አንድ ብለን ነውና የየራሳችንን ድጋፍና አክብሮት እንስጣቸው፡፡ ከዚያም የጋራ ፍሬ እንለቅማለን፣ እንመገባለን፣ ለተከታዩ ትውልድ እንሰንቃለን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታንና ምህረትን ይዘምራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝብ የሚጠላውንና ህዝብ የሚጎዳበትን ነገር እንዳንሠራ ይመክራሉ፡፡ ሁላችንንም ከአንድ እናት ማህጸን የወጣን ሰብዓዊ ፍጡሮች አድርገው እያዩን ነው፡፡ የርስ በርስ ጥላቻና ዘለፋ እንዲቆም እያስተማሩንና እያበቁን ነው፡፡ ጨርሶ ወደኋላ መመለስ እንደማንችል በማረጋገጥም ተከተሉኝ ብቻ ሳይሆን አብረን፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ወደፊት እንንቀሳቀስ እያሉ ነው- ዶ/ር አብይ፡፡


የኃያሏ ሀገር አሜሪካ ተወዳጅ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን በዘመናቸው እንዲህ ብለው ነበር ይባላል፡- «አሜሪካ በውጭው ዓለም ምክንያት ፈጽሞ አትጠፋም፣ አሜሪካ የምትጠፋው እኛ አሜሪካውያን እርስ በርስ በተደነቃቀፍንና ነፃነታችንን በራሳችን ባጣን ጊዜ ነው፡፡» ለሀገራችንና ህዝቦቿም በፍቅርና በይቅርታ ኑሩ ብሎ ጥሪ ከማድረግ በላይ ምን ትልቅ ነገር አለ፣ የአንዲት ታላቅ ሀገር ህዝቦች ስለሆንን እርስ በርስ ነባርና አዳዲስ ቅሬታዎች እያስታረቅን እንኑር ከማለት ሌላ ምን ታላቅ መልዕክት ይኖራል፡፡ ከተበታተነ ኢትዮጵያዊነት ህብረ ብሔራዊነት ይሻላል ከማለት ሌላ ምን ትልቅ ነገር አለ፡፡ የታላቅነት ምስጢርም አንድነት ነውና ወደዚህ ኢትዮጵያዊነት እንመለስ እያሉን ነው፡፡ እንደ ቀድሞዋ ደቡብ አፍሪካ ወይም ሌሎች የዘረኝነት አቀንቃኞች እንደነበሩ ሀገሮች ወደዚህ ሠፈር መግባት አትችሉም ብለው ገደብ አላበጁም፡፡ ጥሪው ለሁሉም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊያት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን በጋራና በተናጥል እያዳመቅን መኖርን እያደስን እንምጣ ነው የሚሉት፡፡


አንድ የነበርነውን ህዝቦችና አንድ የነበረችውን ሀገራችንን የተለያየን ዜጎች የሚያደርገውን አካሄድ ሁሉ ካሁን ወዲያ በጥብቅ ልናወግዝ ይገባናል፡፡ የኖርነው፣ ያደግነው፣ እስከ ዛሬ የዘለቅነው ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያገናኙን መልካም እሴቶች በመካከላችን ስለነበሩና አሁንም ስላሉን ነው፡፡ ወደፊትም አብረውን ይዘልቃሉ፡፡ እነዚህ እሴቶች በጊዜያዊ ጥቅሞችና በስልጣን ጥማት ሊደበዝዙ አይገባም፡፡ እነዚህን የጋራ ያልሆኑና ሊሆኑም የማይገቡ ፍላጎቶችን ልንፈቅድም አይገባንም፡፡ ለአንድታችንና ለአብሮነታችን ደንቃራ የሚሆኑ አስተሳሰቦች ሁሉ ወደኋላ የሚጎትቱን እንጂ ወደፊት የማያራምዱን ስለሆኑ መክሰም አለባቸውና አንከተላቸው፡፡

የሚከተሉትን ሁሉ አግባብተንና አሳምነን እንመልሳቸው፡፡ ባረጀ ጨርቅ ላይ አዲስ ስፌት መስፋት የሚፈልጉትን ዘመኑ እንዳልሆነ እንንገራቸው፡፡ አዲስና ሀገራዊ ጠቀሜታ ያለውን አስተሳሰብ ይዘው የመጡትን ኢትዮጵያዊ መሪ በፍቅርና በአክብሮት እንቀበላቸው፡፡ መበለጥም ሆነ ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ መራመድ ችሎታ እንጂ ሽንፈት አይደለም፡፡ መሸነፍን የማይቀበል አንደበት ለማሸነፍም ዝግጁ አይደለም፡፡ አይሆንምም፡፡ ፖለቲከኛም አይደለም፡፡

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ቀደም ሲል ስለነበርንበት ታሪካዊ ሁኔታ መልካም ጅምሮችን ሲያደንቅ ያለፉ ታሪኮች የዛሬ ሀብቶች ናቸውና ተገቢውን ቦታ ይሰጣል እንጂ አያጣጥልም፡፡ ብዙዎችን ያደንቃል፡፡ ያ ድንቅ እሴት የበለጠ ድንቅ የሚሆነው ግን ብዙ ስንሆን እንጂ ስንነጣጠል ያለመሆኑን አጥብቆ ያምናል፡፡ የዛሬ 242 ዓመት እንደተመሠረተች የሚነገርላት ኃያሏ አሜሪካ ኃያል ከሆነችባቸው ምስጢሮች አንዱና ዋንኛው ስሟ ራሱ እንደሚያመለክተው የተባበረች አሜሪካ በመሆኗ እንጂ አንዳንዴም ወደ መፈራረስ የሚያዘነብሉ አጀንዳዎች ሳይኖሩባት ቀርተው አይደለም፡፡ በአንድነትና በሀገር ጉዳይ ላይ ተደራዳሪ ስላልሆኑ ነው፡፡ ሀብታሙም፣ ደኃውም፣ መካከለኛ ገቢ ያለውም መብቱ እንዲከበርለት በወልስትሪት አደባባይ ላይ ጎላ አድርጎ ይጮኃል፣ ይታገላል እንጂ ሀገሩ እንድትጎዳና እንድትፈራርስ አይደራደርም፡፡

በመረጃ የተደገፈና በዕውቀት የተመራ «ተቃውሞ» ያደርጋሉ እንጂ በአሜሪካና በአሜሪካውያን ዙሪያ ቀልድ የላቸውም፡፡ ጊዜያቸውንና ሀብታቸውን ለሀገራቸው ዘላቂ ዕድገት ይጠቀማሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ዜጎች በመሆናቸውም ለአሜሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ ለሌሎች ሀገሮች ዜጎችም የተስፋ ምድር ሆነውላቸዋል፡፡ በየጊዜው እንደ ዶናልድ ትራምፕ (ፕሬዚዳንት) ያሉ አወዛጋቢ መሪዎች ቢመጡባቸውም መናገር የሚገባቸውን ነገር ሁሉ መናገር በሚገባቸው አግባብ እየተናገሩ አርአያ ሆነዋል፡፡ በአርአያነታቸው ለኛም ተርፈዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አባባል «እዚህ ግባ በማይባሉ ምክንያቶች» የሀገርን ራዕይና ተስፋ የሚያጨናግፉ ተግባራትን አንፈጽም፡፡ ብንራብም ብንጠማም ኢትዮጵያዊነታችን ይሻላልና በኢትዮጵ ያዊነታችን እንዝለቅ፡፡ ውኃ በማቆርና በመሰብሰብ ጦም ያድሩ የነበሩ መሬቶችን እንዳለማን ሁሉ ሰላምን በመነጋገርና በመመካከር እናልማ፡፡ የርስ በርስ ግጭቶችን በወንድማማችነት ብቻ ሳይሆን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር እያሰብንና እየተሳሰብን እናስወግድ፡፡ ለጊዜያዊ ስልጣንና ጥቅም ብለን በወንድማማች ህዝቦች መካከል የማያባራ ቅራኔና ጥላቻ አናቆይ፡፡ መገዳደል፣ ማቁሰል፣ በጥላቻ ዓይን መተያየት ትርፍ የሌለው ቢዚነስ ነውና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እናብቃ፡፡ በመደመር ችግራችንን በመፍታት የወደፊቷን ኢትዮጵያ በእርግጥ መገንባት እንችላለን፡፡ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎችና በተለያዩ ምክንያቶች በሌሎች የዓለም ክፍሎች ተበትነው የሚገኙ ዜጎቻችን ሁሉ በኢትዮጵያዊነት ፍቅር ይኑሩ፡፡ አናሳፍራቸው፡፡

እኛም እንደ ዜጋም ፣ እንደየሙያችንም፣ እንደየአካባቢያችንም በዶ/ር አብይ መሪነት በሀገራችን የተለኮሰውን የለውጥ ማዕበል ሳይቀዘቅዝ የምንመራ ኃይሎች እንሁን፡፡ ከመጥፎ ድርጊትና ጊዜ ካለፈበት ዘረኝነት የራቅን ህዝቦች እንሁን፡፡ ያኔ ኢትዮጵያዊነት ይደምቃል፣ከኢትዮጵያዊው መሪያችንና ከህዝባችን ጋር አብረን መጓዝ እንችላለን፡፡ የሰላም ሀገርና ሰላማዊ ህዝቦች መሆናችንን ለዘላቄታው ከፍ እያደረግን እንዘልቃለን፡፡

በመጨረሻም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የኤርትራ ጉብኝት በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች መካከል የነበረው ወንድማማችነት ምን እንደሚመስልና እንዴት መቀጠል እንዳለበት ወደር በሌለው ሁኔታ ያመላከተ መሆኑን በገሃድ አሳይቷል፡፡

የአሥመራ ከተማ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ በደስታና በደስታ በታጀበ ዕንባ ሲቀበላቸው ስናይ ለሃያ ዓመታት ተለያይተን የነበርነውን ያህል እያነባን እንድንከታተል አድርጎናል፡፡ አቀባበሉም ሆነ መስተንግዶው ፍቅር የተራቡ የሁለቱንም ሀገር ህዝቦች ከልብ ያስደሰተ ከመሆኑም በላይ መነጣጠሉ እንደማይጠቅም የማይረሳ ትዝታ ተክሎ ያለፈ ታሪክ ሆኖ አልፏል፡፡ በዚህ ወንድማዊና የሰላምን ጣፋጭነት አጣጥሞ ለሚያውቀው የኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ሁኔታ ራሱን ችሎ መጻፍ ያለበት ስለሆነ ወደ ዋናው ርዕስ ስመለስ አልጃዝራ ሰሞኑን በድረ ገጹ አስነብቦት በነበረው አስተያየቱ « የኢትዮጵያዊው አብይ አህመድ ወደ ሌላው የአፍሪካ ጠንካራ መሪነት ይሸጋገር ይሆን?» ማለቱ ትክክለኛ ትንበያ ይመስለኛል፡፡

እንደ አንድ የሀገር መሪ ለራሳቸው ምንም ነገር ሳይጎድልባቸው ለሌሎች እንደ ሻማ መቅለጥ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊ መሪ ናቸውና አብረን እንሁን፡፡ የዕውቀት ድህነት የሌባቸውምና ኢትጵያዊነትን ካደመቁ መሪ ጋር እንቀላቀል፡፡ ሁሉም ዜጋ በፍቅር፣ በወንድማማችነትና በአብሮነት መኖር ከቻለ የሀገሪቷ ሀብት የናንተው ነው የሚሉን መሪ ናቸውና እንከተላቸው፡፡

«የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስታት ስለ ሰላም መነጋገር መጀመራቸው በአፍሪካ ቀንድ ለሚገኙ ሁለቱ አገሮች፣ ባጠቃላይም ለመላው አፍሪካ የተስፋ ብርሀን ሊፈነጥቅ የሚችል አጋጣሚ ነው፡፡» ብለዋል የዓለም ካቶሊካውያን ሊቀነ ጳጳስ ፍራንስስ ሮም በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ባደረጉት ንግግር፡፡ ስለሆነም እኚህን ኢትዮጵያዊነትን ያደመቁ መሪ እንከተላቸው፡፡ መልካሙን ለራሳችንም ሆነ ለሀገራችን እንመኝ፡፡ ለዛሬው በዚሁ ላብቃ፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (አጀንዳ)

No comments:

Post a Comment